መነሻ ገጽ ሀምበሪቾ ድራሜ ” የመሀል ተከላካይ ሆኜ የቡድኑ ሶስተኛ ግብ አስቆጣሪ ነበርኩ “ትዕግስቱ አበራ /ሀምበሪቾ ዱራሜ/
ሀምበሪቾ ድራሜዜናዎችየኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ

” የመሀል ተከላካይ ሆኜ የቡድኑ ሶስተኛ ግብ አስቆጣሪ ነበርኩ “ትዕግስቱ አበራ /ሀምበሪቾ ዱራሜ/

አጋራ
አጋራ

” የመሀል ተከላካይ ሆኜ የቡድኑ ሶስተኛ ግብ አስቆጣሪ ነበርኩ “

” ዋና አምበል ባልሆንኩባቸው ክለቦችም ላይ ሁለተኛ እና ሶስተኛ አምበል ሆኜ ማሳለፍ ችያለሁ “

” በከፍተኛ ሊጉ ከፕሪምየር ሊጉ የተሻለ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ አለ “

” ከበርካታ አሰልጣኞች ጥያቄዎችም መጥተውልኝ ነበር ” ትዕግስቱ አበራ /ሀምበሪቾ ዱራሜ/

የመሀል ተከላካይ ተጫዋች ነው …….ሀድያ ሆሳዕና ወደ ፕሪምየር ሊጉ ሲያድግ የቡድኑ አባል ከነበሩት ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነበረ በተጨማሪም በኢትዮጵያ ቡና እና አዳማ ከተማ ጥሩ እንቅስቃሴን አድርጎ ማሳለፍ ችሏል እንዲሁም በከፍተኛ ሊጉም ላይ ተጫውቶ አሳልፏል እያሳለፈም ይገኛል ። ትዕግስቱ አበራ !!

ቡድኑ የተሸነፈበትን ጨዋታ ምርጡ ጨዋታዬ ነው ብሎታል…. ለምን ? በሶስት ክለቦችም አምበል ሆኖ አገልግሏል…. እንዴት ? በተጨማሪም ተጫዋች ሆኖም እስከ ብሄራዊ ቡድን ድረስ የደረሱ ሌሎች ተጫዋቾችን ማፍራት ችሏል……… በነዚህ እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ከሀትሪክ ስፖርት ድህረ ገፅ ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል ።

ሀትሪክ :- እስኪ በቅድሚያ ራስህን አስተዋውቀን ?

ትዕግስቱ :- ትዕግስቱ አበራ እባላለሁ ። የዱራሜ ልጅ ነኝ ። በአሁን ሰአት የሀምበሪቾ ዱራሜ እግር ኳስ ክለብ ተጫዋች እና አምበል ነኝ ።

ሀትሪክ :- እግር ኳስን እንዴት ጀመርክ ?

ትዕግስቱ :- እግርኳስን በሙገር ታዳጊ ቡድን ነው የጀመርኩት ። ከዛሬ ዘጠኝ እና አስር አመት በፊት አካባቢ ድሬዳዋ ከተማ ላይ በተካሄደ የኢትዮጵያ የክለቦች ሻምፕዮና ላይ ዱራሜን ወክዬ መጫወት ችዬ ነበር እና እዛ ላይ ባሳየሁት አቋም ወደ ሙገር ታዳጊ ቡድን ገብቼ እስከ ዋናው ቡድን ድረስ ተጫውቼ ማሳለፍ ችያለሁ ።ሀትሪክ :- ከዛስ ?

ትዕግስቱ :- በሙገር ታዳጊ ቡድን ሁለት አመት ከተጫወትኩ በኋላ ወደ ዋናው ቡድን አድጌ ልምድ እንዳገኝ በውሰት ወደ አዳማ ሪፍት ቫሊ ሄድኩ ከዛ በሼር ኢትዮጵያ ፤ ሀላባ ከተማ ፤ ኢትዮጵያ ቡና ፤ ሀድያ ሆሳዕና ፤ አዳማ ከተማ ከዛ አሁን ደግሞ በሀምበሪቾ ዱራሜ በመጫወት ላይ እገኛለሁ ።

ሀትሪክ :- በርካታ ክለቦች ላይ በፕሪሚየር ሊግም ጭምር ተጫውተህ አሳልፈሀል እሰኪ በየክለቦቹ ስለነበረክ ቆይታ ትንሽ በለኝ እስኪ ?

ትዕግስቱ :- ከሀላባ ስጀምር በሀላባ እያለሁ ጥሩ ቡድን እና ጥሩ ውጤትም ነበረን ደስ የሚል ጊዜም ማሳለፍ ችያለሁ ። በኢትዮጵያ ቡናም ጥሩ ጊዜ ነበረኝ በተለይ በፓፓዲች ጊዜ የሱ ተወዳጁ ተጫዋችም ነበርኩኝ ። ከዛ በኋላም ፓፒች የሚባል አሰልጣኝም መጥቶ ነበር ለሱም ጥሩ ተመራጩም ነበርኩ ከዛ ባለፈ ለዲዴር ጎሜዝም በተመሳሳይ ጥሩ ተመራጭ ተጫዋች መሆን ችዬ ነበር ። በአጋጣሚ ሆኖ የቡድኑ ውጤት ማጣት እና ከአንዳንድ ተጫዋቾች ጋር የነበረ አለመግባባት ክለቡን ለቅቄ ወደ ሀድያ ሆሳዕና ልሄድ ችያለሁ ።
በነገራችን ላይ ሀድያ ሆሳዕና ወደ ፕሪሚየር ሊግ ሲያድግ አምበሉ እኔ ነበርኩኝ የሚገርምክ ቡድኑን ወደ ፕሪሚየር ላግ ስናሳድገው የመሀል ተከላካይ ሆኜ የቡድኑ ሶስተኛ ግብ አስቆጣሪ ነበርኩ ። ከዛም በ2013 አዳማ ከተማ ላይ ጥሩ ጊዜን አሳልፌ ነበር ግን ወደ መጨረሻ ላይ የትከሻ ጉዳት አጋጥሞኝ ለአራት ወራት በጉዳት ርቄ ነበር ። እግዚአብሔር ይመስገን አሁን ሙሉ ለሙሉ አገግሜ ወደ ቀድሞ አቋሜ ተመልሼ ሙሉ የውድድር አመት እያሳለፍኩ እገኛለሁ ።

ሀትሪክ :- በሀላባ ከተማ ፤ በሀድያ ሆሳዕና አምበል ነበርክ በተመሳሳይ አሁንም በሀምበሪቾ በአምበልነት እያገለገልክ ትገኛለክ ይህን ዕድል ደጋግሜ እንዳገኝ አስችሎኛል የምትለው ነገር ምንድነው ?

ትዕግስቱ :- አዎ የሚገርምክ በሌሎቹ ዋና አምበል ባልሆንኩባቸው ክለቦችም ላይ ሁለተኛ እና ሶስተኛ አምበል ሆኔ ማሳለፍ ችያለሁ ። ለዚህም አብቅቶኛል የምለው ደግሞ በወጣቶች እና በስፖርተኞች ጥሩ ተወዳጅ ነን በጥሩ ሁኔታም በየሄድኩበት ያከብሩኛል በተጨማሪም ይመስለኛል ካለኝ ሀቀኝነት ፤ ትክክለኛነት እና ብዙ ጊዜም መካሪ ስለሆንኩ ነው ብዬ አስባለሁ ።

ሀትሪክ :- ከአዳማ ከተማ ወደ ሀምበሪቾ የተዘዋወርክበት ሂደት ምን ይመሰል ነበር ?

ትዕግስቱ :- እንዳልኩህ ወደ መጨረሻ ላይ ጉዳት ላይ ነበርኩ ከአዳማ ከተማ ጋር የነበረኝ ኮንትራትም በዛ መሀል ነበር የተጠናቀቀው ። ከጉዳት ባገገምኩበት ወቅት ደግሞ የፕሪሚየር ሊግ የዝውውር መስኮት በመዘጋቱ ምክንያት ወደ ሌላ የሊጉ ክለብ መሄድ አልቻሉኩም ። በአጋጣሚ በወቅቱ የከፍተኛ ሊግ የዝውውር መስኮት ክፍት ስለነበረ ወደ ሀምበሪቾ ልመጣ ችያለሁ ።

ሀትሪክ :- በዘንድሮው የከፍተኛ ሊግ የውድድር ዓመት ከሀምበሪቾ ጋር እያሳለፍክ ያለውን ጊዜ እንዴት ትገልፀዋለክ ?

ትዕግስቱ :- በዘንድሮው የውድድር አመት እንደ ቡድን ጠንካራ ቡድን ሰርተን ነበር ያው የኳስ ነገር ሆኖ በውጤት ደረጃ ጥሩ ባይሆንም እንደ ግል ግን ጥሩ ነበርኩኝ ማለት እችላለሁ ። በተለይም ሁለተኛ ዙር ላይ በጣም ጥሩ ነበርን ከሰባት ጨዋታዎች አምስት አሸንፈን በሁለት አቻ ነበር የወጣነው ። ከኢትዮጵያ መድኅን ጋር በነበረን ጨዋታ ላይ ገና በ20ኛ ደቂቃ ላይ ተጎድቼ ያለፉት ሁለት ጨወታዎች አምልጠውኛል ።

ሀትሪክ :- ፕሪምየር ሊጉ ላይም ሆነ ከፍተኛ ሊጉ ተጫውተህ አሳልፈሀል ። ባንተ እይታ በሁለቱ ሊጎች መካከል ያለው ልዩነት ምንድነው ?

ትዕግስቱ :- ፕሪሚየር ሊጉ ላይ በጣም ልትታያበት የምትችልበት እና ራስህንም ማሳደግ የምትችልበት ብዙ ነገሮች አሉ ። ፕሮፌሽናሊዝም የሚባለውን ነገር ትማርበታለህ አላማም ይኖርሀል ግብም ይኖርሀል ፕሪሚየር ሊጉ ላይ ስትሆን ። ከፍተኛ ሊጉ ላይም ያ ነገር በተወሰነ መልኩ ይኖራል ግን በጣም ፍትጊያ ይበዛበታል ፤ በጣም ከባድ ፈተና አለው ፤ እያንዳንዱ ቡድን ለመውጣት እና እያንዳንዱ ተጫዋችም ራሱን አሳይቶ የተሻለ ደረጃ ለመድረስ ስለሆነ ከባድ ነው በጣም ።

ሀትሪክ :- በብዙዎች ዘንድ ሁለቱ ሊጎች ሲነፃፀሩ አንድ የሚነሳ ነገር አለ እኔም አንድታነሳልኝ የፈለኩት ስለሆነ ነው ። በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ እና በፉክክር ደረጃ ከፍተኛ ሊጉ ላይ ከፕሪሚየር ሊጉ የተሻለ ነገር አለ ይባላል ምን ያህል ትስማማለህ ?

ትዕግስቱ :- ይሄንን ሀሳብ እኔም እጋራለሁ ከፍተኛ ሊጉ ፍጥነት አለው ጉልበት አለው ከዛም አንፃር ከፕሪምየር ሊጉ የተሻለ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ አለ ማለት ይቻላል ።

ሀትሪክ :- ተጫውተህ ባሳለፍክባቸው ክለቦች ውስጥ ላንተ ምርጡ ተጫዋች እና ምርጡ አሰልጣኝ ማነው ?

ትዕግስቱ :- ከተጫዋች አብሬ ከተጫወትኩ ምርጡ ተጫዋች መስዑድ መሀመድ ነው ። ከመስዑድ ባላፈ ኤፍሬም ወንድወሰን በጣም መካሪዬም ነበር እንዲሁም መሀመድ ናስር ምርጡ ተጫዋች ነበር ያው ብዙ ተጫዋቾች አሉ ግን ለጊዜው እነዚህ ናቸው ።
ከአሰልጣኞች ለኔ ለየት የሚልብኝ ከስራው አንፃር ፓፒች ነው ። ከዛም ባለፈ ነገሮችን ተቆጣጥሮ ያለንን አቅም አውጥተን እንድንጫወት በማድረግ ፤ ከተጫዋች ጋር ግልፅ የሆነ ግንኙነትን በማሳለፍ ፤ በመምከርም ፤ በማጠንከርም ፤ አዕምሮን በማነፅ ረገድ አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ነው ።

ሀትሪክ :- እስኪ ምርጥ የውድድር አመት አሳለፍኩ የምትልበት ዓመተ ምህረት የትኛው ነበር ክለቡስ ?

ትዕግስቱ :- ምርጥ የውድድር አመት አሳለፍኩ የምለው ሀድያ ሆሳዕና ላይ በነበረኝ ቆይታ ክለቡን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ያሳደግንበት አመት እና አምና ደግሞ አዳማ ከተማ ምንም እንኳን በውጤት ደረጃ ያሽቆለቆለበት ቢሆንም እኔ በግል ጥሩ እንቅስቃሴ ያደረኩበት ነበር ። ከኋላም ሆኜ ቡድኑንም ስለምመራ ሀላፊነቶችም ነበሩ በተጨማሪም ከበርካታ አሰልጣኞች ጥያቄዎችም መተውልኝ ነበር ግን ያጋጠመኝ ጉዳት ነገሮችን አበላሽቶብኛል ።

ሀትሪክ :- ጥሩውን እንዲህ ከገለፅክልኝ መጥፎ የውድድር አመት አሳለፍኩ የምትልበትስ ?

ትዕግስቱ :- ለኔ መጥፎ የውድድር አመት ያሳለፍኩበት የምለው በሀድያ ሆሳዕና ሁለተኛ አመት ያሳለፍኩበት ላይ ኮቪድ የገባበት ( 2012 ) አመት ነበር ። ከዛ ግን ፈጣሪ ይመስገን ራሴንም አሻሽዬ በ2013 በአዳማ ከተማ ጥሩ አመትን አሳልፌያለሁ ።

ሀትሪክ :- ከተጫዋችነት ባለፈ ሌሎች ተጫዋቾችን በማፍራት ደረጃ ስራዎችን እየሰራህ እንደሆነ ሰምቼ ነበር እስኪ ስለሱ ጉዳይ የተወሰነ ንገረኝ ?

ትዕግስቱ :- ልጆችን በማብቃት ረገድ ጥሩ ጥሩ ስራዎችን በመስራት ላይ እገኛለሁ አሁን ላይ ብሄራዊ ቡድን ድረስ እየተጫወተ ያለ እንደ ሚሊዮን ሰለሞን አይነት ተጫዋች በኔ ፕሮጀክት ውስጥ ያለፈ ተጫዋች ነው ከዛ ባለፈ በዚሁ መንገድ ሀምበሪቾ ላይ አራት እና አምሰት ልጆች አሉ ሺንሺቾ ላይ አንድ ልጅ አለ ዱራሜ ከተማ ላይ ደግሞ አራት ልጆች አሉ ክብሩ ይስፋ ከተማዬ ላይም እንደዚህ አይነት ስራዎችንም እሰራለሁ ።

ሀትሪክ :- አርአያዬ የምትለው ከሀገር ውስጥም ከውጪም ሊሆን ይችላል ።

ትዕግስቱ :- ከሀገር ውስጥ እንደ አርአያ ደጉ ደበበን ነው ። ደጉ በጣም የማደንቀው የማከብረው ተጫዋች ነው ፤ ከውጪ ደግሞ ራሞስ ።

ሀትሪክ :- ትዕግስቱ እግር ኳስ ተጫዋች ባይሆን ኖሮ በምን አይነት ስራ ላይ ይሰማራ ነበር ?

ትዕግስቱ :- እግር ኳስ ተጫዋች ባልሆን ነጋዴ ነበር የምሆነው ።

ሀትሪክ :- ይዋጣልኛል ብለክ ታስባለክ ?

ትዕግስቱ :- በጣም

ሀትሪክ :- እግር ኳስ ካቆምክ በኋላ ወደ ንግዱ ዓለም የመሰማራት ሀሳቡ አለክ ማለት ይቻላል ?

ትዕግስቱ :- አዎ በደንብ ከዛም ባለፈ በእግር ኳሱ አካባቢ ወደ አሰልጣኝነቱ የመሄድ ሀሳቡም አለኝ ።

ሀትሪክ :- ከእግር ኳስ ውጪ ያለህን ጊዜ በምን ታሳልፋለክ ?

ትዕግስቱ :- ከእግር ኳስ ውጪ ብዙ አነባለሁ ። በነገራችን ላይ በዋቸሞ ዩኒቨርስቲ በስፖርት ማናጅመንት ማስተርሴን እየተማርኩ እገኛለሁ እና ከቤተሰብ ጋር ሰፊ ጊዜዬን አሳልፋለሁ ።

ሀትሪክ :- ቅፅል ስም አለክ ?

ትዕግስቱ :- ቅፅል ስም አለኝ አዎ ራሞስ ይሉኛል ብዙዎች ። ያው ቅድም እንዳልኩህ ራሞስ ለኔ አርአያዬም በጣም የምወደውም ተጫዋች ነው ነገር ግን የሱን ስም በሰጡኝ ጊዜ ለሱ ያለኝን ነገር እንኳን አያወቁም ነበር ።

ሀትሪክ :- የማትረሳው ጨዋታ ?

ትዕግስቱ :- በእግር ኳስ ህይወቴ የማልረሳው ጨዋታ 2010 ላይ በኢትዮጵያ ቡና እያለሁ በደደቢት 1 ለ 0 የተሸነፍንበት ነበር ። ምንም እንኳን ደደቢት ቢያሸንፈንም እንደ ቡድን በጣም አስደናቂ ነበርን ። አንድ ቡድን ተሸንፎ እየተጨበጨበለት ሲወጣ ያየሁበትም የመጀመሪያ ጊዜዬ ነበር ።

ሀትሪክ :- እስኪ በአጭሩ ትዕግስቱ ምን አይነት ባህሪ ያለው ሰው ነው ?

ትዕግስቱ :- ሀቀኛ ነኝ ፤ ከሰዎች ቅደሚያ እኔን ማድረግ እወዳለሁ ፤ ትንሽ ታጋይ ቢጤም ነኝ ፤ በነገሮች መተላለፍ አልወድም ፤ የታየኝን ግልፅ ነው የማወራው ሰው እና ሲጨቆን ማየት አልወድም ።

ሀትሪክ :- በመጨረሻ ማለት የምትፈልገው ነገር ካለ ?

ትዕግስቱ :- ብዙም የምለው የለኝም ግን ታዳጊዎች ላይ መስራት ታዳጊዎችን ማብቃት እፈልጋለሁ ። ቀደም ብዬም እንደገለፅኩልህ ከዚህ በፊትም የሰራዋቸው ስራዎች አሉ በቀጣይም በተጠናከረ መልኩ የመስራት ሀሳቡ አለኝ ።

ሀትሪክ :- በመጨረሻ ማመስገን የምተፈልጋቸው አካላት ካሉ ዕድሉን ልስጥክ ?

ትዕግስቱ :- በቅድሚያ ፈጣሪያችን እግዚአብሔር እዚህ ያደረሰንን ማመስገን እፈልጋለሁ በመቀጠል በህይወቴ ትልቅ ስራ ለሰራችልኝ ለእናቴ እንዲሁም ለመላ ቤተሰቦቼ ከፍተኛ አክብሮት እና ምስጋና ማቅረብ እፈልጋለሁ ። እንዲሁም በእግር ኳስ ህይወቴ ወደ ሙገር እንድገባ ላደረጉኝ የሙገር መልማይ ለነበሩት አቶ ግርማ አሁን ላይ በጣም ተራርቀናል የት እንዳሉም ባላውቅም በጣም ትልቅ አክብሮት አለኝ ምስጋናዬ ባሉበት ይድረስልኝ ። በተጨማሪም በሙገር ከገባሁ በኋላ በታዳጊ ቡድኑ አሰልጣኜ ለነበሩት አሰልጣኝ በቀለ አሁን ላይ አርፈዋል ትልቅ አክብሮት አለኝ አሁን ለደረስኩበት ደረጃ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከቱልኝ አሰልጣኜ ብቻ ሳይሆን መካሪዬም ነበሩ ። በመጨረሻ አሜሪካ የሚገኘው ጓደኛዬ በፍቃዱ ወንድአየሁ በጣም ብዙ ምክንያት አለኝ እሱን ለማመስገን ግን በአጭሩ አመሰግናለሁ ማለት እፈልጋለሁ ።

አጋራ

አስተያየት ይስጡ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ተዛማጅ ጽሑፎች
ሽረ ምድረገነትዜናዎችየኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ

ምድረ ገነት ሽረ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር ውጭ ሆነ!

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሲሳተፍ የነበረው እና በተጠናቀቀው የውድድር አመት ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ...

መቻልኢትዮጵያ ቡናዜናዎችየዝውውር ዜናዎች

ሁለቱን ተጫዋቾች ሁለቱ ክለቦች ተካፈሉ

ለሁለት ክለብ በመፈረማቸው ቅጣት ላይ የነበሩት ተጫዋቾች ለመቻል እና ለኢትዮጲያ ቡና እንዲጫወቱ...

ካፍዜናዎች

የኒጀር እና ሞሮኮ ጨዋታ በኢትዮዽያዊያን ዳኞች ሊመራ ነው

ራቫት ላይ የሚደረገው ወሳኙ የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ በኢትዮዽያዊያን ዳኞች ይመራል። ኬኒያ...

ዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ

በ5 ሳምንታት 39 ጨዋታዎች፣ 72 ጎሎችና ከ22.6 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተመዘገበ!

በአቤኔዘር አበበ በ2019 ዓ.ም የሲቢኢ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያዎቹ አምስት የውድድር ሳምንታት...