በዕለቱ የመጀመሪያ ጨዋታ የተገናኙት ኢትዮጵያ ቡና እና ሰበታ ከተማ ሳይሸናነፉ እንዲሁም ምንም ግብ ሳያስቆጥሩ ጨዋታቸውን 0 ለ 0 በሆነ ውጤት አጠናቀዋል ። በጨዋታው በሰበታ ከተማ በኩል በርካታ ግብ የማስቆጠር አጋጣሚዎችን ቢያገኙም አንዱንም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል ።
ኢትዮጵያ ቡና በሁለተኛው ሳምንት ጨዋታ የነበረውን ምርጥ 11 ሙሉ ለሙሉ የተጠቀመው ሲሆን በሰበታ ከተማ ግን ካለፈው ጨዋታ ሶስት ቅያሪዎችን በማድረግ ነበር ጨዋታቸውን የጀመሩት ።

በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ በኢትዮጵያ ቡና በኩል በተለመደው ኳስን ከኋላ መስርተው በመጫወት ወደ ፊት መሄድ ቢችሉም ወደ ሰበታ ከተማ የግብ ክልል ሲደርሱ ግን ሲከብዳቸው ተመልክተናል ። በሰበታ ከተማ በኩል ረጃጅም ኳሶች ወደ አጥቂ መስመር ተጨዋቾች በማድረስ በመልሶ ማጥቃት ግቦችን ለማስቅጠር ጥረቶችን አድርገዋል ።
በጨዋታው 2ኛ ደቂቃ ሲቃረብ ሮቤል ተክለሚካኤል ለግብ ጠባቂው ያቀበለው ኳስ በአየር ላይ ቢደርሰውም የግብ ዘቡ አቤል ማሞ እንደምንም በግንባሩ ገጭቶ ኳሱ የግቡን አግዳሚ መቶት ሊወጣ ችሏል ።

19ኛ ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት የተሻገረ ኳስ ዘካርያስ ፍቅሬ በጭንቅላት ቢገጨውም ኢላማውን አልጠበቀለትም ነበር ። ሰበታ ከተማዎች በፈጣን የመልሶ ማጥቃት እና ከክንፍ በተለይም ከቀኝ መስመር በሚሻገሩ ኳሶች ዕድሎችን ለመፍጠር ሞክረዋል ።
በተለይም 34ኛ ደቂቃ ሳሙኤል ሳሊሶ ከኢትዮጵያ ቡና ከአማኑኤል ዮሐንስ የነጠቀውን ኳስ ለዱሬሲ ሹቢሳ በተከላካዮች መሀል ጥሩ ኳስ ቢያቀብለውም ተጫዋቹ ኳሱ ላይ ሳይደርስበት ቀርቷል ። የግብ ዕድሎችን መፍጠር የተሳናቸው ቡናማዎቹ በ38ኛ ደቂቃ በሮቤል ተክለሚካኤል አማካኝነት ከርቀት ቢሞክሩም ኳሱ ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል ። በ43ኛው ደቂቃ ይኸው ተጫዋች ለአቡበከር ናስር በተከላካዮች መሀል ጥሩ ኳስ ቢያቀብለውም በጌቱ ሀይለማርያም ጥረት ኳሱን ሳይጠቀምበት ቀርቷል ።

በሰበታ ከተማ በኩል ከፊት መስመር የነበረውን ድክመት ለመቀነስ የመጀመሪያው አጋማሽ መጠናቀቂያ ደቂቃ ላይ ፍፁም ገብረማርያምን በዱሬሳ ሹቢሳ ቀይረው አስገብተዋል ።
በሁለተኛው አጋማሽ በኢትዮጵያ ቡና በኩል ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ወደ ግብ መቅረብ የቻሉባቸውን አጋጣሚዎች በተለይም በግራ መስመር መፍጠር የቻሉ ሲሆን በሰበታ ከተማ በኩል ደግሞ በመልሶ ማጥቃት ረጃጅም ኳሶችን በመጠቀም ግልፅ የሆኑ የማግባት ዕድሎችን ማግኘት ቢችሉም በአጥቂ መስመር ተጨዋቾቻው ድክመት ምክንያት የተገኙትን ዕድሎች ወደ ግብነት መቀየር ሳይችሉ ቀርተዋል ።

በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ጁኒያስ ናንጄቦ በረጅም የደረሰውን ኳስ ሁለት የቡና ተከላካዮችን አልፎ የነበረ ቢሆንም ወደ ግብነት መቀየር ሳይችል ቀርቷል ። በቀጣዮቹ ደቂቃዎችም ሮቤል ተክለሚካኤል ለአቡበከር በተከላካዮች መሀል ጥሩ ኳስ ቢያደርሰውም ግብ ጠባቂው ለአለም ብርሀኑ ደርሶ አውጥቶታል ።
በጨዋታው 66ኛ ደቂቃ ላይ ዘካሪያስ ፍቅሬ ከመሀል ክፍል መሬት ለመሬት ኳስ ቢደርሰውም የመጀመሪያ ንክኪው የተበላሸ በመሆኑ ኳሱ ለአቤል ማሞ ሊደርስ ችሏል ከሁለት ደቂቃ በኋላም ጁኒያንስ ናንጄቦ ሌላ ጥሩ አጋጣሚን በሳጥን ውስጥ አግኝቶ ወደ ግብ ቢመታውም በአቤል ማሞ ተመልሶበታል ። በ70ኛ ደቂቃም ፍፁም ገብረማርያም ለጁኒያንስ ናንጄቦ ከግራ መስመር አሻግርለት ናንጄቦ ኳሱ ላይ ሊደርስበት አልቻለም ። ቡናማዎቹ የኳስ ቁጥጥር ብልጫውን ቢወስዱም ለአለም ብርሀኑን የፈተነ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም ።

በ84ኛው ደቂቃ አቡበከር ናስር ከሀይሌ ገብረትንሳይ የተሻገረለትን ኳስ በጥሩ ሁኔታ መቆጣጠር ቢችልም ወደ ግብ የመታው ምት በሰበታ ተከላካዮች ተመልሶ ወደ ውጪ ወጥቷል ። ተቀይሮ የገባው ያብቃል ፈረጃ በ89 እና 92ኛ ደቂቃ ላይ የግብ ሙከራዎችን ቢያደርግም ኢላማቸውን የጠበቁ አልነበሩም ።
በመጨረሻም ጨዋታውም ያለምንም ግብ ተጠናቋል ። ከጨዋታው ውጤት በኋላ ሁለቱም ክለቦች ከሶስት ጨዋታዎች በተመሳሳይ ሁለት ሁለት ነጥቦችን ብቻ መያዝ ችለዋል ።

አስተያየት ይስጡ