ባህር ዳር ከተማ በጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ በተቆጠረ ድንቅ ግብ ሀዲያ ሆሳዕናን 1 ለ 0 አሸንፏል ።
በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት የሶስተኛ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታ ከቀኑ 9 ሰዓት በኢንስትራክተር አብርሀም መብራቱ የሚመራውን ባህርዳር ከተማን በአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ከሚመራው ሀድያ ሆሳዕና ያገናኘ ነበር ።

በሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታ ባህርዳር ከተማ አዲስ አበባ ከተማን 3 ለ 0 ያሸነፈ ሲሆን ሀዲያ ሆሳዕና በበኩሉ በፋሲል ከተማ 3 ለ 1 ሽንፈትን አስተናግዷል ። ከነዚህ የመጀመሪያ ጨዋታዎቻቸው ላይ አተጠቀሟቸው ምርጥ 11 ባህርዳር ከተማ ሶስት እንዲሁም ሀድያ ሆሳዕና አንድ ቅያሪዎችን በማድረግ ነበር የዕለቱን ጨዋታ የጀመሩት ።
በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ በተወሰነ መልኩ ሀድያ ሆሳዕናዎች በተሻለ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረት አድርገዋል ። በተጨማሪም በመሀልና ክፍል ላይ የበላይነቱን በመውሰድ ጫና ለመፍጠር የሞከሩ ሲሆን ወደ የግብ ሙከራዎችን በማድረግ ረገድ ግን ሳምሶን ጥላሁን እና ኡመድ ኡክሪ ከሞከሯቸው ኢላማዎችን ከሳቱ ኳሶች ውጪ የግብ ሙከራዎችን አላስመለከቱንም ። በባህርዳር ከተማ በኩል በመከላከሉ ላይ ጥሩ የነበሩ ሲሆን በሀድያ ሆሳዕና የመሀል ሜዳ ተጨዋቾች ጥንካሬ ምክንያት ወደ ፊት እንደፈሉጉት መንቀሳቀስ አልቻሉም ።

በ28ኛው ደቂቃ ላይ ኦሴ ማውሊ ከፍፁም አለሙ የደረሰውን ኳስ ከግብ ጠባቂው ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል ። የመጀመሪያው አጋማሽም ያለምንም ግብ ተጠናቀቀ ።

በሁለተኛው አጋማሽ ሀድያ ሆሳዕናዎች ጫና ማድረጋቸውን የቀጠሉ ሲሆን ቀስ በቀስም ባህርዳር ከተማዎች ፈጣን ኳሶችን ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመላክ ለመጠቀም ሲሞክሩ ነበር። ነገር ግን በሁለቱም በኩል ግብ ጠባቂዎችን የፈተነ እና ለግብ የቀረበ የግብ ሙከራ በማድረጉ ረገድ ደክመው ታይተዋል ። ጨዋታው በ0 ለ 0 ውጤት መደበኛ 90 ደቂቃ ተጠናቆ 3 ተጨማሪ ደቂቃዎች በአራተኛው ዳኛ በኩል ታየ ።

የዕለቱ የመሀል ዳኛ የጨዋታውን መጠናቀቅ በፊሽካቸው ለማብሰር ሰከንዶችን በሚጠብቁበት ሰአት ፍፁም አለሙ በሀዲያ ሆሳዕና የማዕዘን መምቻው አካባቢ የነጠቀውን ኳስ ወደ ውስጥ ቢያሻማውም በሀዲያ ሆሳዕና ተከላካይ ተመለሰች የተመለሰችውን ኳስ ሰለሞን ወዴሳ በግንባሩ ሲገጨው ከሳጥኑ ውጪ የነበረው እና ጀርባውን ለግቡ ሰጥቶ የነበረው ኦሴ ማውሊ በሚደንቅ ሁኔታ በመቀስ ምት በመምታት አስቆጥሮ ባህርዳር ከተማ የማታ ማታ ሶስት ነጥብ እንዲያሳካ አስችሎታል ።

አስተያየት ይስጡ