በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ተሳትፎ ቆይታው በጠንካራ ተፎካካሪነቱ ይታወቅ የነበረውና በዘንድሮው የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ጅማሬው ደግሞ ውጤቱ ሳያምር ቀርቶ ወደ ወራጅ ክለቦች አካባቢ በመገኘት ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ገብቶ የነበረው ሲዳማ ቡና ወደ ክለቡ ካስመጣው በኃላ አበረታች ለውጦችን ያስመጣለትን የአሰልጣኙን ገብረ መድህን ሀይሌን ውል ለሁለት ዓመት ያራዘመለት ሲሆን ቡድኑ ከአሰልጣኙ ሌላ ተጨዋቾችን ውል ከማራዘም በተጨማሪ ቡድኑን ሊያጠናክሩለት የሚችሉለት ተጨዋቾችንም በማስፈረም ላይ ይገኛል።
ሲዳማ ቡና በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎው የቀድሞ ጥንካሬውን ለመመለስና በመጪው ዓመትም ለሻምፒዮናነት ለመጫወት ካለው ከፍተኛ ፍላጎት በሊጉ የውድድር ታሪክ ለሁለት ጊዜ ከጅማ አባጅፋርና ከመቀለ 70 እንደርታ ጋር በሀላፊነት ዘመኑ ዋንጫውን ላነሳው አሰልጣኝ ገብረ መድህን ሀይሌ ውሉን ሊያራዝምለት የቻለው በአሰልጣኙ ብቃት በተመለከተው ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ የመጪው ዘመን ውድድር ላይ ስኬትን ያስገኝልናል በሚል እንደሆነም ከክለቡ አካባቢ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።
ሲዳማ ቡና ለሁለት ዓመት ውሉን ያራዘመለት አሰልጣኝ ገብረመድህን ሀይሌ በስራ ሀላፊነት ዘመኑ ሲዳማ ቡናን ከመረከቡ በፊት መቐለ 70 እንደርታን ጅማ አባጅፋርን መከላከያን ደደቢትን ኢትዮጵያ መድንን ኢትዮጵያ ቡናን ንግድ ባንክንና ትራንስ ኢትዮጵያን በክለብ ደረጃ ያሰለጠነ ሲሆን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንንም በሀላፊነት መርቷል ።
አስተያየት ይስጡ