በይስሐቅ በላይ
23 ሻማዎችን በመለኮስ ድፍን 23ኛ አመቱን አክብሯል፤ በ1990 ዓ.ም ተመስርቶ ላለፉት 23 አመታት የአካባቢውን ማህበረሰብ በማቀፍ ስፖርት ለጤንነት የሚለውን መርህ በመከተል በርካታ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ የሚታወቀውና በምሳሌነት የሚጠቀሰው የመካኒሳና አካባቢው ወንድማማቾች ጤና ስፖርት ማህበር ያዘጋጀውና በ6 ቡድኖች መካከል በኮንሶላታ ቤተክርስቲያን ግቢ ውስጥ በሚገኘው ሜዳ ሲካሄድ የነበረው የዙርና የጥሎ ማለፍ የመታሰቢያ ውድድር ከሣምንት በፊት በአዲካ ቤተህይወት አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
23 አመታትን ያስቆጠረው የመካኒሳና አካባቢው ወንድማማቾች ጤና ስፖርት ማህበር ህጋዊ እውቅናን አግኝቶ በአዲስ አበባ ከተማ ጤና ስፖርት ማህበር ስር በመመዝገብ ብዙ አመታትን ቢሾፍቱ ከተማ ላይ በሚዘጋጀው አመታዊ ውድድር ላይ ተሳትፎ በማድረግ በርካታ የሻምፒዮንና የስፖርታዊ ጨዋነት ዋንጫዎችን በማግኘት የሚታወቅ ሲሆን በስፖርት አደረጃጀቱም ከአዲስ አበባ ከተማ ጤና ስፖርት ማህበር ተሸላሚ ለመሆን የበቃ ነው፡፡
23 አመታትን ያስቆጠረው የመካኒሳ የወንድማማቾች ጤና ስፖርት ማህበር በውድድሮች ላይ ከመሳተፍ ባሻገር ለበርካታ አመታት በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ተሳትፎ የሚያደርግ ሲሆን ለቀይ መስቀል ማህበር በተደጋጋሚ የደም ልገሳ በማድረግና በማህበሩ አንድ አባል አማካይነትም ለኩላሊት ህመምተኞች ሊሠራ ለታቀደው የህክምና ማዕከል ግንባታ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ፣ በማህበሩ አባላቶች ላይም ችግርም ደስታም ሲያጋጥም ፈጥኖ በመድረስና ከፍተኛ ድጋፍ በማድረግ በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ወደር የማይገኝለት ተሳትፎ እያደረገ የሚገኝ ማህበር ነው፡፡
የመካኒሳና አካባቢው ጤና ስፖርት ማህበር በአዲስ አበባ ከተማ ጤና ስፖርት ማህበር ሥር ከሚያደርገው ተሳትፎ በተጨማሪ በማህበሩ መርሀ ግብር መሠረት አንደኛው በሆነው የውስጥ ውድድር የማህበሩ መስራች አባል በነበሩትና በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት በተለዩት በአቶ አርአያ ተስፋዬና በአቶ ጌታቸው ሉሉ ስም የመታሰቢያ ውደድር ለማድረግ በመስማማት ደንብ፣ በጀትና የምድብ ድልድል በማውጣት በሁለት ወር የጊዜ ገደብ ውስጥ የሚጠናቀቅ የዙርና የጥሎ ማለፍ ውድድር በማዘጋጀት የማህበሩ አባል የሆኑትን 82 አባሎች በስድስት ምድብ በመክፈል ከታህሳስ 25 ቀን ጀምሮ ሲያካሄደው የነበረው ውድድር በድምቀት ተጀምሮ በድምቀት ተጠናቋል፡፡
በዚህ ለሁለቱ የማህበሩ አባሎች መታሰቢያ በሚል በተዘጋጀው ውደድር ላይ የጌታቸው ሉሉ፣ አዱካ ቤተህይወት፣ ሳልሳዊ (አስማት)፣ ኤ ልቲ ሶፍትዌር፣ ንመኒ ሆቴልና መሠረት ደፋር ቢዝነስ ሴንተር የሚል ስያሜ ያላቸው ቡድኖች የተካፈሉ ሲሆን አዲካ ቤተህይወት በ7 ነጥብና በ7 ንፁህ ጎል 1ኛ በመሆን የወርቅ ሜዳልያ፣ ንመኒ ሆቴል በአንድ ጎል ዝቅ ብሎ በ7 ነጥብና በ6 ጎል 2ኛ በመሆን የብር ሜዳልያ፣ ሳልሳዊ በ5 ነጥብና በ1 ንፁህ ጎል ሶስተኛ በመሆን የነሐስ ሜዳልያ ባለቤት ሲሆን ኤል ቲ ሶፍትዌር አራት የቢጫ ካርድ ብቻ በማየታቸው የውድድሩ የፀባይ ዋንጫ ተሸላሚ ለመሆን በቅተዋል፡፡
የዚህ ውድድር ሁለተኛው መርህ ግብር በሆነው የጥሎ ማለፍ ውደድር ተጋባዥ ሆኖ የቀረበውን የአየር መንገድ ግሩፕስ ቀዳማዊ መሠረታዊ ሠራተኞች ማህበር ቡድንን ጨምሮ በ7 ቡድኖች መካከል ለሶስት ሣምንታት ሲካሄደ ከቆየ በኋላ ኤ ልቲ ሶፋትዌርና የአየር መንገድ ግሩፕስ ቀዳማዊ መሠረታዊ ሠራተኞች ማህበር ለፍፃሜ ደርሰው በጨዋታ 1ለ1 በሆነ አቻ ውጤት ከተለያዩ በኋላ በመጨረሻ በተሰጠው የፍፁም ቅጣት ምት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕስ ቀዳማዊ መሠረታዊ ሠራተኞች ማህበር 5ለ4 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የመታሰቢው ውድድር የጥሎ ማለፍ ዋንጫ አሸናፊ ለመሆን በቅቷል፡፡
ውድድሩ ባማረ መልኩ ፍፃሜውን ሲያገኝ ጥሪ የተደረገላቸው የክፍለ ከተማው የስፖርት አስተዳደሪዎች፣ የአዲስ አበባ ከተማ ጤና ስፖርት ማህበር አመራሮች፣ የሟች ቤተሰቦች፣ የቀድሞ የብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና የማህበሩ አባላት በክብር እንግድነት በተገኙበት በድምቀት ተጠናቋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘም በእለቱ በተዘጋጀው የምሣ ፕሮግራም ላይ በቅርቡ በድንገተኛ ሕመም ከዚህ ዓለም በሞት በተለየው በማህበሩ እንቅስቃሴ ትልቅ ተሳትፎ ለነበረው ለአቶ ዮናስ ወንድሙ ቤተሰቦች ድጋፍ የማሰባሰብ ፕሮግራም የተካሄደ ሲሆን የሟች ልጆችንና ቤተሰቦቻቸውን ለማገዝና ድጋፍ ለማድረግ ሁሉም አባል አጋርነቱን በማሳየት አመርቂ የሆነ እርዳታ ለማግኘት መቻሉንም የማህበሩ ፕሬዚዳንትና የአዲስ አበባ ከተማ ጤና ስፖርት ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅና የመካኒሳና አካባቢው ወንድማማቾች ጤና ስፖርት ማህበር የኮሚቴ አባልና የውድድሩ አዘጋጅ የሆነው የቀድሞ የኢትኮባ ተጨዋች የነበረው አመለሸጋው እሸቱ ከበደ ለሀትሪክ ከላከው መረጃ ለማወቅ ተችሏል፡፡
አስተያየት ይስጡ