ከሲዳማ ቡና በውጤት ማጣት የተሰናበተው አሰልጣኝ ዘርአይ ሙሉ አዳማ ከተማን ከወራጅ ቀጠና የማትረፍ አደራ ተሰጥቶት የአዳማ ከተማን ሃላፊነት ተረክቧል።
አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው፣ አሰልጣኝ ሲሳይ አብርሃምና አሰልጣኝ አዲሴ ካሳ ቡድኑን ሊረከቡ ይችላሉ የሚል የቅድሚያ ግምት የነበረ ቢሆንም ቦርዱ አሰልጣኝ ዘርአይን መምረጡ ታውቋል።
በ7 ነጥብና 15 የግብ እዳ 13ኛ ደረጃ ላይ ያለው የአዳማ ከተማ ቦርድ አሰልጣኝ አስቻለሁ ገ/ሚካኤልን ካሰናበተ በኋላ ቡድኑን የማትረፍ ትልቅ ሃላፊነትን ለአሰልጣኝ ዘርአይ የሰጠ ሲሆን አስልጣኙ ዛሬ ወደ ባህርዳር በማቅናት ቡድኑ በመጪው ሰኞ አራት ሰአት ከጅማ አባጅፋር ጋር ለሚያደርገው ጨዋታ ቡድኑን ያዘጋጃል ተብሎ ይጠበቃል። ትላንት ምሽት በነበረው የቦርድ ስብሰባ ላይ የደጋፊ ማህበሩ ውሳኔውን ባለመቀበል ስብሰባውን ረግጦ መውጣቱ ታውቋል።
የደጋፊ ማህበሩ “ክለባችንን ወደ ውጤት የሚያመጣው አሰልጣኝ ዘርአይ ሙሉ ነው ብለን አናምንም። ከሲዳማ ቡና ሃላፊነቱ በውጤት ማጣት መሰናበቱ እየታወቀ እንዴት ክለባችንን ወደ ተፎካካሪነት ይመልሳል ብለን እንቀበላለን?” በማለት የቦርዱን ውሳኔ እንደማይቀበሉት አሳውቀዋል።
አስተያየት ይስጡ