“ሲዳማ ቡናን የረታንበት ድል አነቃቅቶናል፤ አሸናፊነቱን ለማስቀጠልም ተዘጋጅተናል”
“ስለ ቡና ደጋፊ ተወርቶ አይጠገብም”
ሀይሌ ገ/ትንሳይ /ኢትዮጵያ ቡና/
የኢትዮጵያ ቡናው የግራ መስመር የኮሪደር ስፍራ ተጨዋች የሆነው ሀይሌ ገ/ትንሳኤ ቡድናቸው ለቤት ኪንግ የፕሪምየር ሊጉ ጨዋታ ወደ ባህርዳር ከመጓዙ በፊት በቡድናቸው፣ በአሰልጣኛቸው እና ከራሱ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ዙሪያ ለሀትሪክ ስፖርት ድረ-ገፅ አስተያየቱን ሰጥቷል።
ስለ ትውልድ ስፍራው እና ስለ ኳስ አጀማመሩ
“የትውልድ ስፍራዬ በነገሌ ቦረና ሲሆን ያደግኩት እና እግር ኳስንም ደግሞ በደንብ አድርጌ መጫወት የጀመርኩት በምኖርበት በጎተራ አካባቢ ነው። ። ያኔም ነበር አሰልጣኝ ስዩም አባተ ነፍሱን ይማረውና በዛ አካባቢ ነዋሪ እንደመሆኑ ጥሩ ስጫወት አይቶኝ ወደ ቡና ገብቼ እንድጫወት ይፈልግ ነበርና ይመክረኝ እና ያበረታታኝ ነበር። በእዛን ወቅት መጀመሪያ ላይ ለመከላከያ ወጣት እና የተስፋ ቡድን ውስጥ እጫወት ነበር። በዛ ቡድን ቆይታዬም ወደ ዋናው ቡድን ታድጋለህ አታድግም በሚል ውዝግብ ከቆየው በኋላ ቡድኑን ልለቅ ስለቻልኩና እና ወደ ሱፐር ሊግ ሄጄም ልጫወት ስል በስዩም አባተ ምኞትና በኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝም ዮሴፍ ተስፋዬም በጥብቅ በመፈለጌ ወደ ቡና ገብቼ ልጫወት ቻልኩ”።
ለኢትዮጵያ ቡና ገብቶ መጫወት ስለሚሰጠው ስሜት
“ለኢትዮጵያ ቡና መጫወት መታደል ነው። የማይገኝም ዕድል ነው። እግር ኳስን እረክተህም ትጫወትበታለህ”።
ወደ እግር ኳሱ ጠልቀህ ስትገባ ያደነቅከው ተጨዋች
“መስዑድ መሀመድን ነዋ! እሱን በችሎታው ብቻ ሳይሆን ባለው ዲስፕሊንም ነው በጣም የማደንቀው”።
ለኢትዮጵያ ቡና ሲጫወት ማረም የሚፈልገው
“በሜዳ ላይ ማስተካከል አለብኝ ብዬ የማስበው ጥሩ እንደምከላከለው ሁሉ ወደፊትም ሄዶ ማጥቃቱ ላይ ነው። በዛ ላይ ጠንክሬ እሰራለሁ”።

ከባህር ማዶ ስለሚያደንቀው ተጨዋች
“የማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊ ስለሆንኩ አይደለም። የማርኮሪዎስ አድናቂ ነኝ”።
ስለ አሰልጣኛቸው ካሳዬ አራጌ
“በጣም ጥሩ የሆነ አሰልጣኝ ነው ያለን። ምርጥ ልምምድንም ነው የሚያሰራን። በዛ ላይ የዋህ እና ክፍተቶች ሲኖሩ እንኳን በተጨዋቾች ላይ የማያሳብብ፤ እንዲህ ያሉ አሰልጣኞችም እዚህ ሀገር ላይ ስለሌሉ ሁላችንም እንደ አባታችን ነው የምናየው። በእሱ ስልጠና ሁላችንም እንደምንለወጥም እርግጠኛ ነኝ”።
የኢትዮጵያ ቡና አጨዋወት
“በጣም ይመቻል። እንደተመቸንም በሜዳ ላይ ከሚታየው ኳስን ይዘን ከምንጫወትበት እንቅስቃሴ ተነስቶም መናገር ይቻላል። በአሁኑ ወቅት ለየት ያለ የጨዋታ ታክቲክንም ነው እየተከልን ያለነው። የበለጠ ተግባራዊ ስናደርገውም ከዚህ ቀደም የውጪ ሀገር ቡድኖች የእኛን ሀገር ቡድኖች በጉልበት እና በፍጥነት በልጠው የሚያሸንፉንን ነገር እኛ ኳሱን መስርቶ በመጫወት በምንበልጣቸው እንቅስቃሴ የምንመክትበትና የበላይነታችንንም የምናሳይበት ጊዜም ይመጣልና ያንንም እየጠበቅን ነው”።
የኢትዮጵያ ቡና ቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎ
“በጅማ ባደረግነው የመጨረሻው የቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎአችን ሲዳማ ቡና ላይ የሚያነቃቃንን ድል አስመዝግበን ነበር። ይሄን የአሸናፊነትንም ድል ባህርዳር ላይ በምናደርገውም ተከታታዮች ጨዋታዎችም ልናስቀጥለው ዝግጁ ነን”።
ቤት ኪንጉ ሲጠናቀቅ ቡና የት ደረጃ ላይ እንደሚቀመጥ
“የውድድሩ ዋንኛው ዓላማችን ለሻምፒዮንነት መጫወት ነውና በአንደኛ ደረጃ ነዋ የምንቀመጠው። ያንን ድል ለማሳካት ደግሞ እስከ መጨረሻው ሳምንት ድረስ እንፋለማለን። ይሄ ድል የሚገኘውም የእኛ ተጋጣሚዎች ሁሌም ወደሜዳ ሲመጡ ጨዋታችንን ለማበላሸት እና ለመከላከልም ስለሆነ ኳስን መስርቶ መጫወትን መቼም የምንለቀው አጨዋወት አይደለም”።
ስለ ተጨዋቾች ስብስባቸው እና ስለ ደጋፊዎቻቸው
“የእኛን ቡድን ደጋፊዎች በሚመለከት ስለ እነሱ ተወርቶ አይጠገብም። በጣም ምርጥ ናቸው። ከስራ እና ከቤተሰቦቻቸው በመራቅ እና በመንከራተት ከክልል ወደ ክልል በመዘዋወር የሚደግፉን ናቸው። ከዛ ውጪ ታማኝ እና የእውነተኛ ደጋፊዎችም ናቸው ያሉን። ሲደግፉንም የመጣውን እና ሁሉንም የሚያስደምሙም ናቸው። ዘንድሮ በኮቪድ ወደ ሜዳ በብዛት ተገኝተው ባይደግፉንም በዲኤስቲቪ ግን እየተመለከቱን ስለሚደግፉን በመንፈስ ጭምር ከእኛ ጋር እንዳሉ ስለምንቆጥር ሊመሰገኑ ነው የሚገባቸው። የተጨዋቾች ስብስባችንን በተመለከተ ደግሞ በኳስ ችሎታቸው የተካኑ፣ በታዳጊና ወጣቶች የተገነቡ እና ብዙ ነገርንም መስራት የሚችሉ ስብስብ ነው ያለን”።

በመጨረሻ
“ቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ በዲኤስቲቪ መተላለፉ ለክለቦቻችንንም ሆነ ለተጨዋቾቻችን ትልቅ ጥቅምን እያስገኘ ነው። በተለይ ለእኛ ሀገር ተጨዋቾች ራሳቸውን እንዲያሳዩበት እና ወደ ውጪም ወጥተው ለመጫወትም እንዲችሉበት የተመቻቸ ነገር ፈጥሯልና ልንጠቀምበት ይገባል። ይሄን ካልኩ በኳሱ ጥሩ ደረጃ ላይ መድረስን ስለማልም ለክለቤና ለሀገሬም ከእኔ የሚጠበቅብኝን ነገር መስራትን ስለምፈልግ ለዛ በበቂ ሁኔታ እየተዘጋጀው ነው። በኳሱ እስካሁን ለመጣሁበትም መንገድ ቤተሰቦቼን፣ የቡና ደጋፊዎችን፣ እንደዚሁም ደግሞ ነፍሱን ይማረው አሰልጣኝ ስዩም አባተን አሰልጣኝ ዮሴፍ ተስፋዬንና ከእኔ ጎን የሆኑትን ሁሉ አመሰግናለሁ። ድልም ለቡና እላለሁ”።
አስተያየት ይስጡ