መነሻ ገጽ Oldies but Goodies  አልጄሪያዎች እናንተ ሩጫ እንጂ ኳስ አትችሉም ብለውን አሸንፈናቸው የተናደዱበትን ጊዜ መቼም አልረሳሁም” ብዙነህ ወርቁ /በሶ
Oldies but Goodies ዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ

አልጄሪያዎች እናንተ ሩጫ እንጂ ኳስ አትችሉም ብለውን አሸንፈናቸው የተናደዱበትን ጊዜ መቼም አልረሳሁም” ብዙነህ ወርቁ /በሶ

አጋራ
አጋራ


“ዋና በመቻሌ ከአስከፊው የመኪና አደጋ ህይወቴን ባተርፍም የጓደኛዬ ሞት ግን አሁንም ድረስ ያሳዝነኛል” በመሽሻ ወልዴ

​የኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ በክለብ 
ደረጃ ለኤሌክትሪክ፣ ለኒያላ ለኢትዮጵያ ቡናና 
ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በመጫወት 
እውቅናን ካተረፉት ተጨዋቾች መካከል አንዱ 
የሆነው ብዙነህ ወርቁ ለእረፍት ኑሮውን 
ካደረገበት አሜሪካ በመምጣት ጊዜውን 
እያሳለፈ ሲሆን ይህን የቀድሞ ተጨዋች 
በዛሬው የOldies but Goodies………
አምዳችን እንግዳ አድርገን በማቅረብ የቀድሞ 
የእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመኑንና ሕይወቱን 
ይዳስሳል፡፡ ተከታተሉት፡፡
-ስለውልደቱ፣ እድገቱ ኳስ አጀማመሩና 
አፈፃፀሙ፡- ‘‘የእኔ የትውልድ ስፍራና እድገቴ 
ጃንሜዳና አካባቢው ነው፤ እዚያውም ነው 
ከልጅነቴ አንስቶ የማፈቅረውንና ከልብ 
የምወደውን እግር ኳስ ከጓደኞቼና ከሰፈሬ 
ልጆች ጋር በመጫወት ወደ ተጨዋችነት 
ዓለሙ የገባሁት፤ በክለብ ደረጃ ለመጀመሪያ 
ጊዜ የተጫወትኩት ለኤሌክትሪክ የታደጊ 
/ሲ/ ቡድን ነው፤ ከዚያም ወደ ዋናው ቡድን 
አድጌ በክለቡ ቆይታዬ ለ8 ዓመታትም ያህል 
ተጫወትኩ፤ ከኤሌክትሪከ ቆይታዬ በኋላ 
ደግሞ ያመራሁት ወደ ኒያላ ክለብ ነበር፤ 
እዚያም ለአንድ ዓመት ያህል ከቆየው በኋላ 
ለኦሎምፒክ ብሔራዊ ቡድን ተመረጥኩና 
ተጫወትኩ፤ በመቀጠል ያመራሁት ወደ 
ኢትዮጰያ ቡና ነበር፤ እዚያም ጥሩ ቆይታን 
ካሳለፍኩ በኋላ ወደ ሰበታ ከተማ ክለብ 
አምርቼ በመጨረሻም ወደ አሜሪካ አገር 
የሚወስደኝን እድል በማግኘቴ በእዚያው 
የእግር ኳስ ጫማዬን ሰቀልኩ፡፡


–ስለመጀመሪያው የእግር ኳሱ ክለብ 
ኤሌክትሪክ፡-
‘‘ኤልፓ በሀገራችን ውስጥ ለእኔ 
ብቻ ሳይሆን ለብዙዎች ኢትዮጵያዊያኖች 
የእግር ኳስ ተጨዋቾች መገኛና እናት የሆነም 
ክለብ ነውና የክለቡን ቆይታዬን መቼም 
ቢሆን የማልረሳው ነው፤ በክለቡ ውስጥ 
ከታዳጊ ቡድኑ አንስቶ እስከዋናው ቡድን 
ድረስ ተጫውቼ ሳሳልፍ ብዙ ትዝታዎች 
ነበሩኝ፤ የእኛ ክለብ ያኔ ከሌላው ይለያል፤ 
ከስር አድገህ ሁሉ እንደፈለግክ በነፃነት 
የምትጫወትበትም ቡድን ነው፤ ሁሉም 
ተጨዋች በእኩል የሚታይበት እና ሲኒየር 
የሆነ ተጨዋች ተብሎ የሚለይበት ነገርም 
እኛ ጋር አልነበረም፤ ያኔ ለክለቡ አድገን 
ስንጫወትም እንደ እነ ፀጋዘሀብ አሰግዶም፣ 
ተክሌ ብርሃኔ፣ አፈወርቅ ኪሮስ፣ ያሬድ 
ጌታቸው /ካንጋሮ/ እና ስምኦን አባይን 
የመሳሰሉትም ምርጥ ችሎታ የነበራቸው 
ተጨዋቾች ይመክሩንና በኳሱ ላይ የችሎታ 
ለውጥ እንድናመጣም ይረዱን ስለነበር ከእነሱ 
ጋር ያሳለፍኳቸውን ምርጥ ጊዜያቶች አሁንም 
ድረስ አስታውሳችኋለው፡፡ 
–የመድን ክለብ ታዳጊዎች የተጨዋቾች 
ምርጫ ላይ በእሱ ስም ሌላ ተጨዋች 
ገብቶ ስለመያዙ፡-
‘‘ታሪኩ የእውነት ነው፤ 
ያን ጊዜ እኔ ለኤሌክትሪክም ለመድንም 
የታዳጊ ቡድኖች የክለብ ሙከራን አድርጌ 
በመጀመሪያው ምርጫ ተይዤ ነበር፤ ያን 
ወቅት ላይ ታድያ ማናቸው ጋር ብገባ ይሻላል 
የሚል ነገርን ሳስብና ሰዎችን ሳማክር ለአንተ 
ተጨዋቾችን በብዛት ስለሚያሳድግ ወደ 
ኤሌክትሪክ /ኤልፓ/ ብትገባ ነው የሚሻልህ 
አሉኝና እዚያው ገባሁ፤ መድንም በምርጫ 
የተያዘኩበት ቡድን ነው፤ በእዚያን ወቅት 
ታዲያ የመድኑ እድል እንዳይበላሽ በሚል 
መላኩ ሲሳይ የሚባል የሰፈራችን ልጅ ነበርና 
የመድን ቀጣይ ምርጫ ላይ እሱ በእኔ ስም 
ገብቶ የመሞከር እድሉን እንዲያገኝ ሁለታችን 
ሁኔታዎችን አመቻችተን ተነጋገርን፤ ያን 
ጊዜ የሚጠየቀውም የስድስተኛ ክፍል 
የሚኒስትሪ ካርድ ነበርና በእኔ የትምህርት 
መረጃ የእኔን ፎቶ ካነሳነው በኋላ የእሱን 
ፎቶ ለጥፈን በአንዱ የክለቡ የሙከራ ጨዋታ 
ላይ ታየና በአሰልጣኙ በመወደዱ ሊያዝ 
ቻለ፤ ልጁ ወዲያውኑም በምርጫው መያዙን 
ካረጋገጠ በኋላም የእኔ ስም ብዙነህ አይደለም 
መላኩ ሲሳይ ነው በሚል እውነቱን ተናግሮ 
አሰልጣኙም ልጁ በችሎታው ጎበዝ ነበርና 
ለቡድኑ ሊያስፈርመው የቻለበት ሁኔታ ልዩ 
ገጠመኝ ሆኖ የተመለከትኩት ነው፡፡
–በእግር ኳስ በጣም የተደሰትክበት 
ቀን፡-
‘‘መቼም ቢሆን የማልረሳው ከፍተኛ 
ደስታዬ የኢትዮጵያ ወጣት ብሄራዊ ቡድን 
ተጨዋች በነበርኩበት ሰዓት ዛንዚባር ላይ 
ተዘጋጅቶ የነበረውን የምስራቅና መካከለኛው 
አፍሪካ ወጣቶች ዋንጫን በአሰልጣኝ ሰውነት 
ቢሻውና በአሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ 
በመመራት ኡጋንዳን በፍፁም ቅጣት ምት 
አሸንፈን ሻምፒዮና የሆንበትን ጊዜ ነው፤ ያኔ 
የውድድሩ ተሳትፎአችን ላይ አሸናፊ ስንሆን 
ብዙዎቹ ሀገራት በአካል ብቃትም በፍጥነትም 
ይበልጡን የነበረ ቢሆንም እኛ በምንችለው 
ሌላ አቅም ተጫውተን ነው አሸናፊ ልንሆን 
የቻልነውና ያን ልዩ የደስታ ጊዜዬን ሁሌም 
የማስታውሰው ነው፤ ሌላው የደስታዬ ጊዜ 
የነበረውና ሁሌም ከአህምሮዬ የማይጠፋው 
ደግሞ በአሰልጣኝ አበራ ሀብቴ በሚመራው 
የኢትዮጰያ ኦሎምፒክ ብሄራዊ ቡድን ውስጥ 
ተጨዋች በነበርኩበት ሰአት በእግር ኳሱ 
ላይ ከፍተኛ ስምና ዝና ከሚታወቁት የሰሜን 
አፍሪካ ሀገራት አንዷ ከሆነችው የአልጀሪያ 
ወጣት ብሄራዊ ቡድን ጋር ለኦሎምፒክ 
የማጣሪያ ጨዋታ አልጀርስ ላይ ግጥሚያን 
አድርገን እኔ ታፈሰ ተስፋዬና ሳላህዲን ሰይድ 
ባስቆጠርናቸው ሶስት ግቦች 3-1 ያሸነፍናቸው 
ግጥሚያም የሚጠቀስ ነው፤ የእዚያ ጨዋታ 
ላይ የማልረሳው አልጀሪያዎች እኛን 
ንቀውን ነበር የጠበቁን፤ ሆኖም ግን ባለድሉ 
እኛ ተንቀን የነበርነው ልንሆን ችለናል፡፡ 
በጨዋታው ላይም ከማሸነፋችን በተጨማሪ 
ካስቆጠርናቸው ሶስት ግቦች ውስጥ አንዷን 
እኔ ስላስቆጠርኩም የደስታዬ መጠን በወቅቱ 
እጥፍ ድርብርብም ሊሆንልኝ ችሏል”፡፡ 
–የአልጀሪያን ኦሎምፒክ ብሔራዊ ቡድን 
በጊዜው ስታሸንፉ ውጤቱ የማይታመን 
ነው ስለመባሉ፡-
‘‘አዎን፤ የእውነት ነው 
አልጀሪያዎቹ እኛን ከመናቃቸው አኳያ 
በኢትዮጵያ እንሸነፋለን ብለው በፍፁም 
አልጠበቁም ነበር፤ ሆኖም ግን ወደ መጨረሻ 
ሰዓታት አካባቢ ተጭነው ለመጫወት ሞከሩ 
እንጂ በጨዋታ ጭምር ነው ተበልጠው 
ሊሸነፉ የቻሉት፤ በጊዜው የተመዘገበው 
ውጤትም ለብዙዎች የማይታመንም ነበር፤ 
ያን ወቅት ላይ እንደውም በ2 ሰአታት ጊዜ 
ውስጥ የአልጀሪያ ብሔራዊ ቡድን ከሊቢያ 
ብሔራዊ ቡድን ጋር የወዳጅነት ጨዋታን 
በሌላ ሜዳም ያደርጉ ስለነበር እኛ ጨዋታችንን 
ጨርሰንና ትንሽም አርፈን የእነሱን ግጥሚያ 
ለመመልከት ወደ ሌላው ሜዳ ስናመራ እዚያ 
የሚገኙት የአልጄሪያ ደጋፊዎች የኦሎምፒክ 
ቡድናቸው ጨዋታ እንዳለው ሁሉ ብዙም 
ግንዛቤው አልነበራቸውም መሰለኝ ምኖች 
ናችሁ? አሉን፤ እኛም ኢትዮጵያኖች ነን 
አልናቸው፤ በመቀጠል ምን ልታደርጉ 
ነው የመጣችሁት ሲሉን ጨዋታ ነበረን፤ 
የአልጀሪያን የኦሎምፒክ ቡድንንም 3-1 
አሸንፈን ነው ከሌላ ሜዳ የመጣነው ስንላቸው 
በፍፁም አላመኑንም፤ ይሄ ሊሆን አይችልምም 
አሉን፤ እናንተ ኢትዮጵያዊያን የምትችሉት 
እኮ ሩጫ እንጂ ኳስ ስላልሆነ እኛን በኳሱ 
በፍፁም አታሸንፉንም እያሉ በነበረበት ሰዓት 
ላይ የሁለታችንም የጨዋታ ውጤት እዚያው 
ስቴድየሙ ላይ በሚዲያ ደረጃ ሲነገር እነሱ 
በጣም የተናደዱበትን ሁኔታ ለመመልከት 
ችያለውና ያ ጊዜ ፈፅሞ የማይረሳኝ ነው፡፡ 
–በእግር ኳስ በጣም ያዘነውና ልቡ 
የተሰበረበት ቀን፡-
‘‘የእግር ኳስ ተጨዋች 
በነበርኩበት ሰአት ያዘንኩበትን ወይም ደግሞ 
ልቤ የተሰበረበትን ቀን አሁን ላይ ፈፅሞ 
አላስታውስም፤ ኳስን ከልጅነት እድሜዬ 
አንስቶ ስጫወት አስደሳችና ጥሩ ጊዜያቶችን 
ነው ያሳለፍኩት፤ ሁሌም ጨዋታዎች ካለቁ 
በኋላ ማዘንም አልወድምና ይሄ ነው የእኔ 
መገለጫዬ፤ ከኳሱ ውጪ ባለው የህይወት 
ቆይታዬ ግን በጣም ያዘንኩበትና ልቤም 
የተሰበረበት ቀን ቢኖር የመጀመሪያው የወላጅ 
አባቴንና ወላጅ እናቴን በሞት ማጣቴ ነው፤ 
ሌላው ደግሞ ከዓመታቶች በፊት አስከፊ 
በሆነው የመኪና መገልበጥ አደጋ ወደ 
ቁልቢ የቅዱስ ገብርኤልን ዓመታዊ በአል 
ለማክበር ሶስት ሆነን ሄደን እየተመለስን 
እያለን እኔ የማሽከረክረው መኪና ጎማው 
እንደመፈታትና እየላላም በመሄዱ መኪናችን 
ውሃ ውስጥ ተገልብጦ በመግባቱ ጓደኛዬንና 
እንደወንድሜም የምመለከተውን ብሩክ 
ተስፋዬን ከ5 ሰአታት ፍለጋና ቆይታ በኋላ 
መኪና ውስጥ ቤልቱን እንዳሰረ እሱን በሞት 
ያጣሁበት ቀን ሁሌም ቢሆን የማዝንበትና 
ልቤም የተሰበረበት ወቅት ነው፡፡
-በመኪና መገልበጥ አደጋው ጓደኛቸውን 
በሞት አጥተው እሱና ሌላው ጓደኛው እንዴት 
ከሞት ሊተርፉ እንደቻሉ፡-
‘‘በጊዜው ወደ 
ድሬዳዋ የቁልቢ በአልን ለማክበር አብረን 
ከተጓዝነው ሶስት ጓደኛማሞች መካከል እኔና 
ተመስገን አለሙ ከሞት አደጋው ልንተርፍ 
የቻልነው መኪናው እንደተገለበጠና ወደ 
ውሃው ውስጥም በፊት ለፊት እንደገባ እኔ 
የውሃ ዋና እችል ነበርና በተሰበረው መስታወቱ 
በኩል ነው እየዋኘው ከወንዙ በመውጣት 
ልተርፍ የቻልኩት፤ ለተመስገን ደግሞ ሰዎች 
ዱላ ሰጡትና ያንን ይዞ ነው ከውሃ ውስጥ 
በመውጣት ሊተርፍ የቻለው፤ ከአደጋው 
ተርፈን ከወጣን በኋላም እኔ ላይ ጓደኛዬን 
በሞት ስላጣሁትና ስለ አደጋውም ከባድነት 
አስብም ስለነበር በጊዜው በአህምሮዬ በኩል 
እየተጨነቅኩኝ ለተወሰነ ጊዜ ያለመረጋጋት 
ችግር ደርሶብኝ ነበርና ያ ወቅት የሚያሳዝን 
ሆኖ አልፏል፤ ያም ሆኖ ግን ከሞቱ አደጋ 
ምስጋና ለፈጣሪ ይግባውና በእሱ እርዳታ፣ 
ድጋፍና ትዕዛዝ ታግዘን በሕይወት ልንቆይ 
በመቻላችን ያ የተለየ አጋጣሚ ነው፡፡
–የእግር ኳስ ተጨዋች በነበረበት ወቅት 
ለመጀመሪያ ጊዜ ስላደረገው የኢትዮጵያ 
ፕሪምየር ሊግ ግጥሚያ፡-
‘‘በፕሪምየር ሊጉ 
የውድድር ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ያደረግኩት 
ግጥሚያ የኤሌክትሪክ ተጨዋች እያለሁ 
ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የነበረው ጨዋታ ላይ 
ተቀይሬ በመግባት ነው፤ ያኔ የቡድናችን 
አሰልጣኝ የነበረው ጉልላት ፍርዴ ሲሆን እሱ 
በወቅቱ ብዙ ተጨዋቾቻችንን በጉዳት 
አጥቷቸው ነበርና ያኔ የእነሱ አለሞኖርን 
ተከትሎ ነው እኔም ከስር አድጌ በመምጣት 
ተቀይሬ ገብቼ ልጫወት የቻልኩት፤ በእዚያም 
ጨዋታ ላይ ጥሩ ለመንቀሳቀስ ችያለው፤ 
ጨዋታውንም በቀጣይነት ክለባችንን 
በማሰልጠን ሃላፊነቱ የሚረከቡት ጣሊያናዊው 
አሰልጣኝ ሚስተር ጁሴፔ ፔትሬሊም 
እየተከታተሉት ነበርና በእዚያ ጨዋታ ላይ 
ጥሩ ለመንቀሳቀስ የቻልነውንና እሳቸውም 
የተመቻቸውን ተጨዋቾች በመዝገባቸው 
ላይ አስፍረው በቀጣይነትም ከጉና ጋር 
የነበረው ጨዋታ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ 
በቋሚ ተሰላፊነት የምጫወትበትን እድል 
አስገኝተውልኝ ሊያጫውቱኝ ችለዋል፡፡
–የእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመኑ ላይ 
በልዩ ክስተት የማይረሳቸው ጨዋታዎች፡-

‘‘ሶስት ናቸው፤ የመጀመሪያው የኤሌክትሪክ 
ክለብ ተጨዋች በነበርኩበት ሰአት ቅዱስ 
ጊዮርጊስን ስንገጥምና ስናሸንፋቸው ከቡድኑ 
የኮሪደር ስፍራ ተደናቂ /የመስመር ተጨዋች/ 
ከነበረው ዳዊት መብራቱ ጋር በጨዋታ 
እንቅስቃሴ በተደጋጋሚ ካታንጋ ጋር 
እንገናኝና እንፋጠጥም ስለነበር ሁለታችንም 
የእልኸኛነትንና የአልሸነፍ ባይነትን ስሜት 
ተላብሰን እየተናነቅን የተጫወትነውንና 
ዳዊትም እንደሌላው ጊዜ ክለቡን በሚጠቅም 
መልኩ ፈፅሞ እንዳይጫወት ያደረግኩበትን 
ግጥሚያ ፈፅሞ አልረሳውም፤ ሌላው 
የኢትዮጵያ ቡና ተጨዋች በነበርኩበት 
የ1999ቱ ቡድን ላይም ያንን ምርጥ ስብስብን 
ይዘንና ጥሩ ቡድንን መገንባት ችለን በወቅቱ 
በተፈጠረው የእግር ኳሱ ግርግር ራሳችንን 
ከውድድሩ ያገለልንበትን ጊዜ ነው፤ በወቅቱ 
እኛ ከነበረን ጥሩ ቡድን አኳያ የሊጉን 
ውድድር ብንጨርስ ኖሮ ዋንጫውን 
የማግኘት እድሉም ይኖረን ነበር፤ ከእዚያ 
ውጪ ሌላው ፈፅሞ የማልረሳው የእግር ኳስ 
ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጨዋች 
በነበርኩበት ሰአት ወደ ዲሞክራቲክ ኮንጎ 
አምርተን ያኔ ኮንጎዎች እንደ እነ ሉዋሉዋና 
በአውሮፓ ሊግ የሚጫወቱ ስድስት የሚደርሱ 
ተጨዋቾችን ይዘው በመግባት እነሱ በ80 ሺህ 
ደጋፊዎቻቸው ፊት ታጅበው 2-0 ያሸነፉን 
ጨዋታ በጣም የሚገርም ነበር፤ ጨዋታው 
ላይ የነበረው ጩኸት እኛን አደናግሮናል፤ 
እንዳንደማመጥም አድርጎናል፤ አንዴ 
እንደውም ከቡድናችን አንድ ተጨዋች ጋር 
መሰማማት ስላልቻልን ወደ አጠገቡ ሄጄ 
በጆሮው ልነግረው ስል አንድ ኳስ ወደ 
እኛ ክልል መጣና ሳልነግረው የሄድኩበት 
አጋጣሚም ነበርና ያ ጨዋታ መቼም ቢሆን 
የሚረሳኝ አይደለም፡፡
–የጨዋታ ዘመንህ ምርጡ አሰልጣኝ፡
– ‘‘ለእኔ ክፍሌ ቦልተና ቀዳሚውን ስፍራ 
ይወስዳል፤ ክፍሌ ሀገራችን ካፈራቻቸው 
ምርጥ አሰልጣኞች መካከል በአሰለጣጠን 
ብቃቱ በጣም የማደንቀው ነው፤ በሙያው 
ቆይታ ኳስ የሚጫወት ቡድን ይሰራል፤ 
ሌላው ከእሱ የምታደንቅለት ትልቁ ነገር 
ለአንድ ግጥሚያ ወደሜዳ የሚገቡ ቤስት 
ልጆችን በቋሚ ተሰላፊነት ካስገባ በኋላ 
የሚጫወቱበት የጨዋታ ፎርሜሽን ለምሳሌ 
3-5-2ን ይከተል ከነበረ ፎርሜሽኑን ወደ 
4-4-2 በመቀየር በእነዚያው ልጆች ሰው 
ሳያስወጣ ኳስን በደንብ የሚጫወት ቡድንን 
ይሰራልና ያ የአሰለጣጠን ብቃቱ ይገርመኛል፤ 
የልምምድ አሰጣጡም ላይ የማይሰለች 
ስራንም ስለሚያሰራ ከአሰልጣኞች እሱን ነው 
የማደንቀው፡፡
–የጨዋታ ዘመንህ ምርጡ ተጨዋች፡
–
‘‘ለእኔ ተክሌ ብርሃኔና ስምኦን አባይን 
በቀዳሚ ደረጃ ላይ ነው የማስቀምጣቸው፤ 
ሁለቱንም የኳስ አስማተኞችም ብዬ ነው 
የምጠራቸው፤ የእኛ ክለብ ውስጥ ያኔ ከእነሱ 
ውጪም እንደ እነ አፈወርቅ ኪሮስና ያሬድ 
ጌታቸውንም የመሳሰሉ ተጨዋቾች ይገኙም 
ስለነበር እነሱንም ፈፅሞ የማልረሳቸውና 
የማደንቃቸውም ተጨዋቾች ነበሩ፡፡ 
–በጨዋታ ዘመኑ አብሮት ባለመጫወቱ 
የሚቆጨው ተጨዋች፡-
‘‘የቅዱስ ጊዮርጊስና 
የአትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአማካይ ስፍራ 
ተጨዋች ከነበረው ሙሉአለም ረጋሳ ጋር 
አብሬ ባለመጫወቴ ይቆጨኛል፤ እሱ 
በችሎታው ልዩና በአህምሮውም ኳስን 
አስቦ የሚጫወት ተጨዋች ስለነበር ያንን 
የመጫወት እድል ከእሱ ጋር ለማግኘት 
አልቻልኩም፡፡
–በጨዋታ ዘመኑ ከአጠገቡ ጋር ሆኖ 
ሲጫወት ስለተመቸውና ተግባብቶት 
ስለተጫወተው ተጨዋች፡-
‘‘ይሄ ምን ጥያቄ 
ያስፈልገዋል የመጀመሪያውና ዋናው ሰው 
ታፈሰ ተስፋዬ ነው፤ ከእሱ ጋር በተደጋጋሚ 
የመጫወት እድልን አግኝቻለው፤ ሁለታችን 
ያኔ አጠገብ ለአጠገብ ሆነን ስንጫወትም 
በጣም ፈጣን ከመሆናችን በተጨማሪ ኳሱ 
ላይ በሚገባ ተግባብተን እንጫወት ስለነበር 
በጥምረታችን ሊሳካልኝ ችሏል፤ ከታፈሰ 
በተጨማሪ ሌሎቹ ተግባብቼ የተጫወትኳቸው 
ተጨዋቾች አንዳርጋቸው ሰለሞን /ሸበላው/ 
ዮናስ ገብረሚካሄልና አሸናፊ ግርማ ናቸውና 
እነሱን አስታውሳለው፡፡
–የጨዋታ ዘመኑ ላይ ተቃራኒ ሆኖ 
ስላስቸገረው ተጨዋች፡-
‘‘የኤሌክትሪክ ቡድን 
ውስጥ በአንድ ወቅት ከአዳማ ከተማ ጋር 
ስንጫወት ካልሆነ በስተቀር በጨዋታ 
ዘመኔ እኔን ያስቸገረኝ ተጨዋች ማንም 
የለም፤ በእዚያም ጨዋታ ላይ ቢሆን ልጁ 
እኔን እንዳልጫወት ካስቸገረኝ በኋላ ራሱ 
ተቀይሮም ሊወጣ ችሏል፤ የአዳማ ከተማ 
ክለብን በተፋለምንበት የእዚያ ጨዋታ ላይ 
ልጁ እኔን ያዝ ተብሎ ነው መሰለኝ ወደ 
ሜዳ የገባውና ኳስን ይዤ ሳልፈው ከስር 
ስሬ እየተከተለ እግሬን ይመታኛል፤ አንዴ 
እንደውም በጥፊም መታኝ፤ ያን ጊዜም 
በጣም ተናደድኩኝና ስማ አንተ ቆንጆውን 
ልጅ ያዝና ምታው ተብለህ ነው የታዘዝከው 
ስለው እሱም በጣም ተናደደና ሜዳ ውስጥ 
መጫወት አቃተው፤ እረፍት ወጥተን ሁሉ 
የእነሱ አንድ ተጨዋች ሲነግረኝ እየተመከሩ 
በነበረበት የመልበሻ ክፍል ሰዓት ላይ እኔን 
ቀደም ሲል በተናገርኩት ነገር ብስጭቱ 
ሳይለቀው ይሰድበኝና ወደ ሜዳ ስንገባም 
እሰብረዋለውም ይል ሁሉ እንደነበር 
ስለተነገረኝ የሁለተኛው አጋማሽ ላይ አንድ 
ነገር እንዳያደርግኝ ማለትም እግሬን መትቶ 
እንዳይጎዳኝ ነገረኝና ለመጠንቀቅ ቻልኩ፤ 
ልጁም የሁለተኛው አጋማሽ ላይ ጨዋታው 
እንደተጀመረ ከባድ ታክል ገባብኝና ቢጫ 
ካርድ ተመልክቶ ተቀይሮ የወጣበትን ሁኔታ 
በጣም የማስታውሰው ጨዋታ ነው፡፡
–ከባህር ማዶ ክለቦች የሚደግፈው፡
–
‘‘የማንቸስተር ዩናይትድን ልጅ ሆኜ 
ጀምሮ የምደግፈው ክለብ ነው፤ ያም ሆኖ 
ግን የአርሰናልን ጨዋታ ማየት በጣሙን 
ስለሚያረካኝ እነሱም ደስ ነው የሚሉኝ፡፡ 
-ከውጪ ሀገር ተጨዋቾችስ ማንን ነው 
የምታደንቀው፡- ‘‘ምን ጥያቄ አለው እኔን 
በአጨዋወቱ የሚስበኝ ምርጡ ተጨዋች 
ሆላንዳዊው ዴኒስ ቤርካምፕ ነበርና የእሱ 
አድናቂው ሆኜ ነው ኳስን ይበልጥ ልወደው 
የቻልኩት፡፡ 
–ከባህር ማዶ ባለሙያዎች 
በአሰለጣጠናቸው የምታደንቀው አሰልጣኝ፡-
 
አርሰን ቬንገር የእግር ኳስ ጣዕም እንዲኖረው 
ያደረጉ ባለሙያ ስለሆኑ እሳቸውን ነው 
የማደንቀው፤ አርሰን ቬንገር እንደሚፈልጉት 
መጠን ዋንጫ ባያገኙም በቆይታቸው 
ታዳጊ ተጨዋቾችን ከስር ከስር በማሳደግ 
የሚታወቁና የማይታወቁ ተጨዋቾችንም 
ለእውቅና ስለሚያበቁ አንዳንድ ጊዜ እንደ 
ቀድሞ የኤልፓ አሰልጣኝም ይመስሉኛልና 
ለእሳቸው ልዩ ክብርም ነው ያለኝ፡፡ 
-የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጨዋች 
በነበርክበት ሰአት ከአንድ የህክምና ዶክተር 
ጋር ስላደረግከው አጭርና ፈገግ ስላደረገ 
ቃለ-ምልልስ፡-
‘‘የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን 
ተጨዋች እያለው ነው ያኔ የኩላሊት ጠጠር 
አሞሃል ተባልኩና ቼክ ለማድረግ ስቴድየም 
አካባቢ ወደሚገኘው የብሩክ ከፍተኛ ክሊኒክ 
ሳመራ ዶክተሩ ኳስ ተጨዋች መሆኔን 
አወቀና ቀድሞ የፍጥነት ጥያቄን ጠየቀኝ፤ 
የማን ክለብ ተጨዋችና አድናቂ ነህ አለኝ፤ 
እኔም የቡና አልኩት፤ ቀጥሎ ደግሞ ከስፔንስ 
የማን ነህ ሲለኝ የባርሴሎና አልኩት፤ 
ወዲያውኑ አከታትሎ ከእንግሊዝስ ሲለኝ 
የማንቸስተር ብዬ ስመልስለት ምላሽህን ሁሉ 
አዛምድ አደረግከው ሲለኝ ፈገግ ያልኩበት 
ጊዜን የማልረሳው ነው፡፡ 
–በአሁን ሰዓት የት እንደሚገኝና 
ጫማውንም ሰቀሎ የእግር ኳሱን ካቆመ በኋላ 
ስለተሰማራበት ሙያ፡-‘
‘የእግር ኳሱን ካቆምኩ 
በኋላ የአሁን ሰዓት ላይ የምገኘው በአሜሪካን 
ሀገር ነው፤ ወደ አሜሪካንም ካመራውበት 
ያለፉት ሰባት ዓመታት ጀምሮም በስራ ላይ 
ተሰማርቼ ኑሮዬን በጥሩ መልኩ እየመራው 
ነው የምገኘው፡፡
–በአሜረካን እግር ኳስን አሁን ላይ 
ይጫወት ስለመሆኑ፡-‘
‘አዎን፤ የእግር ኳስን 
በኢትዮጵያኖች ዓመታዊ ውድድር ላይ 
በአሰልጣኝ ብሩክ እስጢፋኖስ ለሚመራው 
የሲያትል ዳሽን ቡድን ውስጥ እጫወታለው፤ 
ከእዚያ ውጪም የእኔ የስራ ሁኔታ የትርፍ 
ጊዜና ሰዓት የሚያስገኝልኝም ስለሆነ 
በእረፍት ሰዓቴ ጤንነቴን ለመጠበቅ ኳስን 
የምጫወትበት አጋጣሚዎች አሉኝና እነሱን 
በአግባቡ እጠቀምባቸዋለው፡፡ 
–በምን ምክንያት የእግር ኳስ ጨዋታን 
አቁሞ ጫማውን እንደሰቀለ፡-
‘‘የኢትዮጵያ 
እግር ኳስ ላይ ኳስን ለረጅም ጊዜ መጫወት 
የምችልበት አጋጣሚው ነበረኝ፤ ኳሱን 
ያቆምኩት ተጎድቼ ወይም ደግሞ በቃኝ ብዬም 
አልነበረም፤ የውጪ እድል ስላገኘሁ ብቻ 
ነው ወደ አሜሪካን ሀገር ስለሄድኩና ስራም 
መስራት አለብኝ በሚል ኳስን መጫወት 
ያቆምኩት፡፡
–ስለ ቤተሰቡ እና እግር ኳሱ ላይ 
ስለነበራቸው አመለካከት፡-
‘‘የእኛ ቤተሰብ 
ጋር እግር ኳስ በጣም ይወደዳል፡
፡ ሰፈራችንም ጃልሜዳ አካባቢም ስለነበር 
ብዙዎቹም ተጫውተው አሳልፈዋል፡፡ 
ከእነዚህ የቤተሰባችን አባላት ውስጥም እኔ 
በተለያዩ ክለቦች ውስጥ ስጫወት ታናሽ 
ወንድሜም የኤሌክትሪክ ታዳጊና ወጣት 
ቡድን ውስጥ ተጫውቶ ወደዋናው ሊያድግ 
መቻሉ ይታወሳል፤ ሌላው ታላቃችንና ጥሩችሎታ የነበረው ደረጄ ወርቁም ለማረሚያ 
ቤትና ለአየር መንገድ እንዲጫወት እድሉ 
ተመቻችቶለት ሳይጫወት ቀረ እንጂ እሱም 
ኳስ ይጫወት ነበር፡፡ 
-በእግር ኳሱ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከፈለሀ 
ትልቅ ደመወዝና ክፍያው በወቅቱ ስለፈጠረብህ 
ስሜት፤ ብሩንስ ምን ላይ አዋልከው፡-

ለመጀመሪያ ጊዜ የእግር ኳስ ተጨዋች ሆኜ 
የተከፈለኝ ደመወዝ የኤሌክትሪክ ታዳጊ ቡድን 
ውስጥ እያለሁ 30 ብር ነው፤ ከዚያም ወደ 
ዋናው ቡድን አድጌ በተመላላሽነት ስሰራም 
700 ብርና በኋላም ላይ ደመወዜ 1700 ብር 
የሆነልኝ ጊዜ አልረሳውምና ይሄ ነበር የእኔ 
ደመወዝ የመጀመሪያው ደመወዝን ሳገኝ የእኔ 
ከፍተኛ ፍላጎትና ትኩረቴ ኳስ መጫወቱ ላይ 
ስለሆነ ብሩ ላይ ብዙም ትኩረትን አላደረግኩም 
ነበር፤ ሆኖም ግን የኤሌክትሪክ ክለብ ውሰጥ 
በነበርኩበት ያን ወቅት ላይ ቡድኑ የዋናውን 
የወጣትና የታዳጊ ቡድኖችን ዋንጫ ያነሳ ጊዜ 
በሽልማት መልኩ የተሰጠኝ የ6 ሺህ ብር 
ሽልማት ስለማይረሳኝ ያኔ ተደስቼ ለወላጅ 
እናቴ የሰጠኋትን ጊዜ የማልረሳው ነው፡፡ 
–ደመወዙን አሁን ለተጨዋቾች 
ከሚከፈለው በወር 200 ሺህ ብር ጋር 
ስታነፃፅረው ዛሬ ላይ ተጨዋች ብሆን ኖሮ 
ብለህ ትመኛለህ፡
-‘‘አልመኝም፣ ምክንያቱ
ምን መሰለህ ብሩ ያንን ያህል ቫልዩ የለውም፡ ያን ጊዜ እኛ 1700 ብር በምናገኝበት ሰአት 
አንድ ጥሩ ምግብ ቤት ገብተህ እንደ ስፖርተኛ 
ልትመገብ ስትል 20 ብር ነበር የምታወጣው አሁን 
ግን ለአንድ ጥሩ ለምትለው ምግብ እስከ 300 
ብር ከጓደኞችህ ጋር ከሆንክ ደግሞ እስከ 600 
ብር ከፍለህ የምትወጣበት ሁኔታ እዚህ ሰሞኑንም 
በራሴም ላይ በሌሎችም ወጪዎች ላይ ኑሮም 
ጠንከር እያለ ከመሆኑ አኳያ ስለተመለከትኩት 
የአሁን ጊዜ ተጨዋች ይህን አገኘ ብዬ እኔም 
በድጋሚ የእዚህ ዘመን ተጨዋች ልሁን ብዬ 
አላስብም፤ የአሁን ጊዜ የእግር ኳስ ተጨዋቾች 
የሚያገኙት የደምወዝ ክፍያን በሚመለከት ገንዘቡ 
ማደግ መቻሉ ጥሩ ነው፤ በእዚያ መልኩ ኳሱንም 
በመጫወት ትልቅ ስምና ዝናን የሚያገኙት 
እነሱ ናቸው ሆኖም ግን እዚህ መጥቼ አሁን 
የተመለከትኩትን ሁለት ጨዋታዎች ላይ ማለትም 
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከጅማ አባጅፋር ጋር ኤሌክትሪክ 
ከአዳማ ከተማ ጋር የተደረጉት ጨዋታዎች ላይ 
ሜዳው ሲጀመር ከኮረኮንች ያነሰ ሆኖ በጨዋታው 
ላይ እነዚህ ናቸው ይሄንን ብር የሚያገኙት ብዬ 
አስተያየትን ጥሩና መጥፎ ነው ብዬ መስጠት 
በፍፁም መስጠት አልፈልግም፡፡
–ብዙነህ ራሱን በ3 በተመረጡ ቃላቶች 
ሲገልፅ፡-መሸነፍ የማይወድ፣በጣም እልኸኛና 
ሁሌም ደስተኛ የሆነ ነው፡፡
–
በሶ በሚል መጠሪያ ስም እየተጠራ 
መሆኑ፡- አዎን፤ በእዚህ ስያሜ ለመጠራት 
የቻልኩት በአንድ ወቅት ለኤሌክትሪክ የታዳጊ 
ቡድን ስንጫወት ዋንጫ ለማንሳት ችለን ነበር፤ 
ያኔም ሽልማት ለእኛ ከመሰጠቱ በፈት ገንዘቡ 
ሲደርሰን ምን እንደምናደርግበት ስንነጋገር፤ 
አንዱ ተጨዋች ብራስሌት እገዛበታለው አለ፤ 
ሌላው ደግሞ ቲቪ፣ ቴፕ እያሉ ሲናገሩ ተራው 
የእኔ ሆነና ስጠየቅ 100 ኪሎ በሶ አስፈጫለው 
ስል ያን ጊዜ የቡድናችን ተጨዋች የነበረው 
ቢኒያም ኃይሌ /ዋሴ/ ነው እኔን በሶ በማለት 
ስያሜው እንዲወጣልኝ ያደረገው፡፡
የአስቴር አወቀን ኮንሰርት ለማየት ከክለብ 
ልምምድ ስለመቅረቱ፡- የኤሌክትረክ የዋናው 
ቡድን ውስጥ ከስር ባደግኩበት ጊዜ ነው ይሄ 
የሆነው፤ ለክለቡ ያን ወቅት ላይ ልምምድ ልስራ 
እንጂ እንደማልጫወት አውቅ ስለነበር ቅዳሜ ቀን 
ይካሄድ ለነበረው እና በጣም የምወዳት የአስቴር 
አወቀ ኮንሰርት ላይ መታደሙን ስለፈለግኩ 
አሞኛል በሚል ሰበብ ሳያመኝ ከሰፈር ልጆች 
ጋር ኮንስርቱን ገባው፤ እዚያው በጭፈራም 
ቀኑን አቀለጥነው፤ ኮንሰርቱም የቀጥታ ስርጭት 
ነበረው፤ ይሄኔ የምሳ ሰዓት ላይ ታዲያ አሰልጣኝ 
ጉልላት ፍርዴ የቡድናችን ተጨዋች ታምራት 
በጣም ጓደኛዬ ነበረና ብዙነህ የታለ ሲለው እኔን 
ተሸክመውኝ እጨፍር ስለነበር ያው ቲቪ ላይ 
ብሎ አሳየው፤ ያኔ ሁሉም ተጨዋቾች ነበር 
የሳቁት ከዚያም አሰልጣኝ ጉልላት መታኝ 
ተቆጣኝ ብዬ ሳስብ እነ ጋሽ ሀጎስም ነበሩና 
እሱም ይወደኝ ስለነበር በቃ የልጅ ነገር ሆኖ 
ነው እሷን ስለሚወዳት ነው የሄደው በሚል 
ምንም ሳይሉኝ ያለፈፈበትን ጊዜ አልረሳውም፡፡
–በመጨረሻ..የኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ 
ኳስን ስጫወት አበረታች የሚባል እንቅስቃሴን 
በማሳየት እስክ ክለብና የብሄራዊ ቡድን ደረጃ 
ላይ በመድረስ ከእኔ የሚጠበቀውን ብቃት 
እንዳሳይ የረዱኝን ብዙ አካላቶች አሉ፤ 
የእግር ኳሱ ላይ ከእኔ ጎን በመሆን በምክርና 
በማሰልጠን ሃላፊነቱም ጥሩ አስተዋፅኦ 
ያደረጉልኝ አጠቃላይ ሰዎችን መቼም 
ቢሆን የማልረሳቸው ናቸው፤ ሌላው በሞት 
ያጣኃቸውን እናትና አባቴን ከእዚያ በመቀጠል 
የአሌክትሪክ ክለብ ውስጥ ከታዳጊ ቡድን አንስቶ 
እኔን በማሰልጠን እስከ ኢትዮጵያ ቡና ክለብ 
ድረስ ለቡድኑ እንድጫወት ያደረገኝን አሰልጣኝ 
ክፍሌ ቦልተናን እና ጉልላት ፍርዴን ማስተር 
ቴክኒሺያን ሐጎስ ደስታን እንደዚሁም ደግሞ 
በኤሌክትሪክም በቡናም በነበረኝ ጥሩ ቆይታዬ 
ያበረታቱኝ የነበሩትን የሁለቱን ደጋፊዎች 
ለእኔ በጣም የቅርብ ጓደኞቼ የሆኑትና የሰው 
መውደድ የነበራቸው ታፈሰ ተስፋዬና ታምራት 
አበበ /ሎቲ/ መቼም ቢሆን የማልረሳቸው ሰዎች 
ናቸውና ላደረጉልኝ ነገር ሁሉንም በጣም ነው 
የማመሰግናቸው፡፡

አጋራ

አስተያየት ይስጡ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ተዛማጅ ጽሑፎች
ሽረ ምድረገነትዜናዎችየኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ

ምድረ ገነት ሽረ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር ውጭ ሆነ!

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሲሳተፍ የነበረው እና በተጠናቀቀው የውድድር አመት ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ...

መቻልኢትዮጵያ ቡናዜናዎችየዝውውር ዜናዎች

ሁለቱን ተጫዋቾች ሁለቱ ክለቦች ተካፈሉ

ለሁለት ክለብ በመፈረማቸው ቅጣት ላይ የነበሩት ተጫዋቾች ለመቻል እና ለኢትዮጲያ ቡና እንዲጫወቱ...

ካፍዜናዎች

የኒጀር እና ሞሮኮ ጨዋታ በኢትዮዽያዊያን ዳኞች ሊመራ ነው

ራቫት ላይ የሚደረገው ወሳኙ የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ በኢትዮዽያዊያን ዳኞች ይመራል። ኬኒያ...