የሊግ ኮሚቴው አመራሮች መስመሩን አልፈዋል፤ የክለባችንን መብት ተጋፍተዋል በዚህም አዝነናል” አቶ ሽፈራው (ተ/ኃይማኖት) የመቐለ 70 እንደርታ እግርኳስ ክለብ ዋና ስራ አስኪያጅ

ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመግታት መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በማውጣት አዋጁ እስከ ነሀሴ 30/2012 ድረስ እንደሚፀና ካስታወቀ ቆየት ብሏል፡፡ በእግር ኳሱ አደባባይም የ2012 መርሃ ግብር መቼ ይቀጥል ይሆን? የሚል ጉጉት ባለበት ሰዓት በመቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ የሚመራው አዲሱ የሊግ ኮሚቴ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ የ2012 ሻምፒዮን፣ ወራጅና ኃላፊ ክለብ የለም ሀገሪቱም በ2013 በአፍሪካ መድረክ አትሳተፍም ብሎ ውሳኔውን አሳውቋል፡፡ ይህን ተከትሎ ድጋፍም ተቃውሞም እየቀረበበት ያለው የሊግ ኮሚቴ ውሳኔ በተለይ በአምናው ውጤትም ይህን በዘንድሮው 17ኛ ሳምንት ድረስ ባለው ውጤት የመካፈል እድሉ የነበራቸው ፋሲል ከነማና መቐለ 70 እንደርታ የከረረ ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡ በዚህ ውዝግብ የመቐለ 70 እንደርታ ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ሽፈራው ተ/ኃይማኖትና የፋሲል ከነማውን አሰልጣኝ ስዩም ከበደን የሀትሪኩ ዮሴፍ ከፈለኝ አነጋግሯቸዋል፡፡
ሀትሪክ፡-የሊግ ካምፓኒ በወሰነው ውሳኔና ክለቦችን ከአፍሪካ መድረክ ውጪ ያደረገው አካሄድ ዙሪያ ምን ይላሉ?
ሽፈራው፡-ደብዳቤ ሳይደርሰን መግለጫ መስጠት አልፈለግንም ነበር ነገር ግን አሁን ቅሬታችንን በደብዳቤ አስገብተናል፡፡ ዋናው ጉዳይ ፋሲል ከነማና መቐለ 70 እንደርታ የሚያልፉበት የተቀመጠ ሕግ የለም ያልታሰቡ ጉዳዮች ሲገጥሙ ግን ለጠቅላላ ጉባኤ አቅርቦ ማስፀደቅ ይቻላል፡፡ ለዚህ ጉዳይ ብለው ጠቅላላ ጉባኤ እንደማይጠሩ አውቃለው እገምታለሁም፡፡ ነገር ግን ብዙ አማራጮች ነበሯቸው….የግድ የመቐለ 70 እንደርታ ሃላፊ ስለሆንኩ ሳይሆን የዘንድሮ ውድድር ተሰርዟል እልባት የለውም ከተባለ የባለፈው አመት ውጤትን ተንተርሶ ለካፍ መላክ ይቻል ነበር ብዬ አስባለው፡፡ ይሄ ማንንም አያከራክርም እነ ጊዮርጊስ ሲዳማ ቡናም በ1 ነጥብ ብቻ እየተበለጡ መብትቸውን መጠየቃቸው አይቀርም፡፡ ህጉም በዚህ ላይ የሚለው ስለሌለ የአምናውን መጠቀም ይችሉ ነበር ይህን ባለማድረጋቸው ቅር ብሎናል፡፡
ሀትሪክ፡-ከሁለታችሁ /ፋሲል ከነማና መቐለ 70 እንደርታ/ ስር ያሉ ክለቦች ተጠይቀው ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል የሚል መረጃ አለኝ….?
ሽፈራው፡- መቼም ኢትዮጵያ መካፈል የለበትም የሚለው አካሄድ ለክለቦችም ሆነ ለሀገራችን ይጠቅማል ብዬ አላስብም፡፡ የዘንድሮውን ውጤት ተንተርሰው ወደ አፍሪካ ውድድር ከላኩ ወራጅና ሻምፒዮና ማነው ወደሚለው ስሌት ሊገባ ነው ይሄ ደግሞ አያስኬድም…. የአምናው ውጤት ብቻ ነው ሕጋዊ የሚሆነው፡፡ በኛ በኩል ግን በአምናውም ቢባል በዘንድሮም ችግር የለብንም ሁለቱም ላይ አለንብትኮ… አይከፋኝም፡፡
ሀትሪክ፡- ውሳኔውን ተንተርሶ መቐለ 70 እንደርታ ተበደልን ብሎ ያስባል?
ሽፈራው፡-በጣም ተደበለናል ብለን ነው የምናምነው….ቀድሞ ነገር ኢትዮጵያ በአፍሪካ መድረክ መሳተፍ አትችልም ብለው መወሰናቸውን አንቀበልም መወሰንም አይችሉም መተዳደሪያ ደንብ ላይ በተፃፈ መንገድ ነው አንድ ነገር ማለት የሚችሉት… ወጣ ካለ ደግሞ ለባለድርሻ አካላት ሃሣቡን ለውሳኔ ማቅረብ ይችላሉ ነገር ግን የሊግ ኮሚቴው አመራሮች መስመሩን አልፈዋል፤የክለባችንን መብት ተጋፍተዋል በዚህም አዝነናል፡፡
ሀትሪክ፡- ሊግ ካምፓኒው ፋሲል ከነማና መቐለ 70 እንደርታ ይለፉ ቢል በተቃራኒው የሚቃወሙ አይኖሩም ብለው ያምናሉ?
ሽፈራው፡-በዘንድሮው ውድድር ውጤት ለምን ይፈቅዳሉ? ያን ካደረጉ ችግር ይፈጥርባቸዋል በአምናው ሲሄዱ ግን ውጤቱ ሕጋዊ ስለሆነ ማንም አይከራከርም፤ችግሩን ማለፍ ይችሉም ነበር፡፡ ይሄ ግን አልሆነም በአምናው ተቃውሞ ከመጣ መነጋገር ይቻላል ከሃገር በላይ የሚሆን የለም በብዙ መንገድ መታለፍ ይቻል ነበር…..እኔ ካልበላሁ እበትነዋለው አይነቱ ነገርም መቆም አለበት ብለን እናምናለን…. እኔ በነርሱ ቦታ ብሆን የአምናውን ደረጃ እጠቀምበት ነበር፡፡ ይሄ ነው ትክከለኛው መንገድ፡፡
ሀትሪክ፡-ሙሉ የፕሪሚየር ሊግ ክለቦችን ማማከር ነበረባቸው የሚሉ አሉ… ወራጅ ቀጠና ውስጥ ያሉ ክለቦች ስለ አፍሪካ ውክልና ምን አግብቷቸው ይወያያሉ የሚሉም አሉ… እርስዎስ ምን የሚሉት ነገር አለ?
ሽፈራው፡-ጉዳዩ ችግር የሆነው የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ የተቀመጠ አቅጣጫ የለም ስለዚህ ውድድሩን እንዴት አድርገን እንምራ ብለው ክለቦችን መጠየቅ ነበረባቸው ብዬ አምናለሁ…. ነገር ግን መወያየት ግድ አይደለም መንግሠት አግዶ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ ውይይቱ ምንም ላይፈጥር ይችላል፡፡ ስለ አፈፃፀሙ ግን በቴሌ ኮንፈረንስ ይሁን በሌላ መንገድ ክለቦችን ማወያየት ነበረባቸው ክለቦቹ ዋነኛ ባለድርሻ መሆናቸው መረሣት የለበትም፡፡
ሀትሪክ፡-ሰባቱ የሊግ ካምፓኒ አመራሮች በ16 ክለቦች እንደ መወከላቸው ውሳኔዎችን መወሰን አይችሉም….?
ሽፈራው፡- ሰባቱም ሰዎች ወክለን በመተዳደሪያ ደንቡ መሰረት አስተዳደሩን አልናቸው ከደንቡ ውጪ የሆነ ችግር ሲመጣ ግን አሁን የወሰኑትን ውሳኔ የመወሰን መብት ያላቸው አይመስለኝም፡፡ በየትኛውም መንገድ የወሰኑት ውሳኔ እንዲወስኑ መብት የሚሰጥ ደንብም የለም፤ ይሄን ማድረጋቸውን የሚደግፍ መንገድም የለም፡፡ እነርሱ ስለ ጉዳዩ ከአሰልጣኝና በደጋፊ መረጃ ከሚቀበሉ ከክለብ ባለቤቶች ግብአት የሚሆን ነገር ቢሰባሰቡ ይሻል ነበር ዋናው ባለድርሻ አካል ክለቦቹ ናቸውና፡፡ በርጥ ግብአት ለማግኘት ባለድርሻ አካላቱን ማነጋገራቸውን ባልቃወምም በአፍሪካ መድረክ እንካፈል አንካፈል? ምን ይደረግ ትላላችሁ ተብሎ መጠየቅ የነበረበት ባለቤት ክለቦችና አመራሮቹን ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ስለ ውድደሩ ይቀጥል አይቀጥል… ማን ሻምፒዮን ይሁን የሚሉ መጠይቆችን ለክለቦች ደጋፊዎች መቅረቡ ተገቢ ነው? ደንቦችና መመሪያዎች በደጋፊ አስተያየት ላይ ይወሰናል?
ሽፈራው፡-ጥናት ስታደርግ የነበሩትን ባለድርሻ አካላትን ማነጋገር አይከፋም ዳታ ሲሰበሰብ መረጃ መውሰድ አይከፋም ዋናው ጉዳይ ትልቁ ውሳኔውን የሚወስነው ማነው የሚለው ነው፡፡ ዋናው ወሳኝ ደግሞ ክለቦች ናቸው፡፡ የክለቦቹ ባለቤቶች ናቸው መጠየቅ የነበረባቸው…ይሄ ባለመደረጉ ነው ተቃውም የቀረበው….በኛ በኩል ተበድለናል ተጎድተናል ብለን ደብዳቤ ፅፈናል፤አገሪቱ በአፍሪካ ተወካይ እንድታጣ የተደገውን ውሳኔ እንቃወማለን እንደ ክለብ ያለንን እድል መነፈጋችንን አንቀበልም፡፡
ሀትሪክ፡-አመሰግናለሁ፡፡

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport