የጨዋታ ዘገባ | ወልቂጤ ከመመራት ተነስቶ ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል

 

በ15ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ከአንድ አመት ከ ስድስት ወር ወደ ሜዳው በመመለስ ጨዋታውን ያደረገው ወልዋሎ 3-3 በሆነ ውጤት ከወልቂጤ ጋር ነጥብ ተጋተዋል።

ባለሜዳዎቹ ከባለፈው አሰላለፋቸው የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገው ከጉዳት የተመለሱት
አይናለም ኃይሉ እና ፍቃዱ ደነቀን በቋሚ አሰላለፍ ይዘው ሲገቡ። ወልቂጤዎች ይበልጣል ሽባባው በቋሚ አሰላለፋቸው አካተዋል።

ከጨዋታው መጀመር በፊት ወልዋሎዎች በስታዲዮም እድሳት ዙሪያ አስተዋፅኦ ላደረጉ አካላት የምስጋና ወረቀት አበርክተዋል።

በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ ብልጫ የነበራቸው ቢጫ ለባሾቹ ኳስን ይዘው የተጫወቱ ሲሆን ወልቂጤ ከተማዎች ግባቸውን በማስከበር እየተከላከሉ በመልሶ ማጥቃት እድሎችን ለመፍጠር ተጣጥረዋል። መሪ መሆን የቻሉት ወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርሲቲዎች 7ኛው ደቂቃ ላይ ጁኒያንስ ኒያንጂቡ ራምኬሎክ ያቀበለውን ኳስ ተጠቅሞ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል። በይበልጥ ወደ ግራ መስመር አድልተው ባለሜዳዎቹ ሲጫወቱ። ወልቂጤ ከተማዎች ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታ መስመር ገብተዋል። ከግራ መስመር በረጅሙ የተላከችለትን ኳስ ራምኬ ሎክ 41ኛው ደቂቃ በሚገባ ተጠቅሞ ግብ በማድረግ መሪነቱን ወደ ሁለት አሳድጓል። ከአምስት ደቂቃዎች በኋላም አህመድ ሁሴን ወደ ሳጥን እየገፋ ይዞ ሄዶ ያቀበለውን ኳስ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ጫላ ተሺታ ግብ አድርጎ ልዩነቱን አጥብቧል። በተደጋጋሚ የግብ እድሎችን የፈጠሩት ወልዋልዋሎ አዲግራት ሳይሳካላቸው 2-1 እየመሩ ለእረፍት ወጥተዋል።

 

በሁለተኛው አጋማሽ ጥሩ መሻሻሎችን ይዘው የቀረቡት ወልቂጤ ከተማ አጥቅተው በመጫወት ያገኟቸውን አጋጣሚዎች ለመጠቀም ምንም ማወላዳት አይታይባቸውም ነበር። ራምኬ ሎክ ላይ በተሰራው ጥፋት አማካኝነት የተገኘችውን የቅጣት ምት ሳሙኤል ዮሀንስ ሲያሻማ ኢታሙናይ ኬይሙኒ ግብ አድርጎ ወልዋሎን ሶስት ለአንድ እንዲመራ አስችሏል። በተለይ በዚህኛው አጋማሽ የመሀል ተከላካዩ አይናለም ሀይሉ እጁ ላይ ባለው ጉዳት ምክንያት ከሜዳ ተቀይሮ ከወጣ በኋላ የተጋጣሚያቸውን ጥቃት ለመመከት ተቸግረዋል። በዚህም ተከታታይ ሁለት ግቦችን እንዲያስተናግዱ አድርጓቸዋል። ተጭነው በመጫወት በጫላ ተሺታ እና አህመድ ሁሴን በርካታ ጥቃቶችን የሰነዘሩት ወልቂጤ ከተማዎች 72ኛው ደቂቃ ጫላ ተሺታ ግብ አስቆጥሮ ልዩነቱን ማጥበብ ሲችል። ከግቧ መቆጠር በኋላ ኳሱ ጀምሮ በፍጥነት ወልዋሎ ግብ ላይ የገኙት ወልቂጤ ከተማ የጠአመ ወልደኪሮስ ስህተት በሚገባ በመጠቀም ግብ በማድረግ ወልቂጤን አቻ አድርጓል። በመረበሻቸው ምክንያት ኳሶቻቸው በብዛት ሲበላሹባቸው የነበሩት ባለሜዳዎቹ ይበልጡኑ ተጋላጭ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። በተጨማሪ ደቂቃ ላይ ራምኬል ሎክ እና ኢታሙናይ ኬይሙኑ አግዳሚው የመለሰባቸው እጅግ አስቆጪ እና ወልዋሎ ከጨዋታው ነጥብ ይዞ ሊወጣ የሚችልበት አጋጣሚ ነበረች። ጨዋታው 3-3 በሆነ አቻ ውጤት ሲጠናቀቅ ወልዋሎ ወረጅ ቀጠና ውስጥ ለመግባት ተገዷል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርሲቲ ደጋፊዎች በተጫዋቾቻቸው ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ ሲሰነዝሩ የተስተዋለ ሲሆን በተለይ አምበሉ አይናለም ኃይሉ ትሪብል ድረስ በመሄድ ከደጋፊዎች ጋር ተወያይቷል። የወልቂጤ የቡድን አባላት ውጤቱ ይገባቸዋል ጎበዞች ናቹ በማለት መልካም እንዲገጥማቸው የተመኙበት የወልዋሎ ደጋፊዎች አስገራሚ ትዕይንት ነበር። ከጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ ተጫዋቾቹ ከሜዳ ለስአታት በዛው ቆይተው በስተመጨረሻ ወደ ማረፊያቸው አቅንተዋል።