1.ሀትሪክ:-የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በጋና አቻው 5ለ0 በሆነ ሠፊ ውጤት ተሸንፏል ይህ ውጤት ይረብሽሃል?
ኢንስ አብርሃም:-ስትሸነፍ በውስጥህ የሚቀር ነገር መኖሩ የሚካድ አይደለም፤ግን መረበሽን በተመለከተ በፍፁም አይረብሽንም።ሽንፈቱ ተጫዋቾች በቁጭት እንዲነሳሱ እንዲዘጋጁም በሌላ በኩል መልካም የሚባል ጫናን አድርጎባቸዋል።በባለፈው ውጤት ከመረበሽ ይልቅ የሜዳችንን አድቫንቴጅ በመጠቀም የተሻለ ውጤት ይዘን ለመውጣት ነው እየተሠራ ያለው፤ስለዚህ ጉዟችን ወደፊት እንጂ ወደ ሃላ አይደለም።
2.ሀትሪክ:-የጋናን የ 5ለ0 ሠፊ ውጤት ሽንፈትን ለመርሳት በተጫዋቾቹ አእምሮ ላይ ምን ሠርተሃል?
ኢንሰ.አብርሀም:-ከሜዳ ላይ ስልጠና ባልተናነሰ እኔን ጨምሮ የኮቺንግ ስታፉ የስነ ልቦና ባለሙያ ጭምር በመጋበዝ በአእምሮ ላይ ብዙ ስራ ሰርተናል።ከላይ እንዳልኩህ ምንም ቢሆን ስትሸነፍ በውስጥህ የሚቀር ነገር አለ፤ይሄንን ነገር ከፍርሀት ይልቅ ወደ ቁጭት ውጤትንም መቀልበስ ይቻላል የሚል መንፈስን በውስጣቸው እንዲሰርፅ በማድረግ አእምሮ በመቀየር ረገድ ከፍርሀት ይልቅ ወደ ቁጭት የሚወስድ ጥሩ ሥራ ሠርተናል ብዬ አስባለሁ።
3.ሀትሪክ:-የሁለቱን ሀገሮች ጨዋታ የዳዊትና የጎልያድ ፍልሚያ ነው ብሎ መጥራት ይቻላል?
ኢንስ.አብርሃም:-አረ ይሄ እግር ኳስ ነው!ምንአልባት የተፈለገው በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ልዩነት ለማሳየት ተፈልጎ ከሆነ የሚመስል ነገር አለ፤ጋና ቀአህጉሪቱ የእግር ኳስ ካርታ ላይ በጣም ጎልታ የምትታይ በየሀገሩ የሚጫወቱ ታላላቅ ፕሮፌሽናል ተጫዋቾች ያላት ውጤታማ ሀገር ናት፤በአንፃሩ የእኛን ስታየው ውጪ የሚጫወቱ ቢኖሩም የሚጫወቱበት ሊግ የሚታወቅ ነው።ዕውነቱን መናገር ካለብን ደረጃችንም ብዙ ልዩነት አለው ለንፅፅርም የሚቀርብ አይደለም።ሆኖም ግንእኛ ህብረታችንን አንድነታችንን መሠረት አድርገን ጋናዎችን በታሪካቸውና በውጤታቸው ሳናከብድ ተገቢውን ክብር ሰጥተን ማድረግ የምንችለውን እናደርጋለን።
5.ሀትሪክ:-መከላከልን ነው ማጥቃትን ነው መርጠህ የምትገባው?
ኢንሰ.አብርሃም:-መከላከል ብዙም ትርፍ የለውም የምንጫወተው በሜዳችን ከመሆኑ አንፃር ማጥቃትን እናስበልጣለን።
6. ሀትሪክ:-ጋናዎች 5 አስቆጥረውብናል እኛስ እነሱ እንዳደረጉት 5የምናስቆጥርበት ዕድል ሊፈጠር የሚችልበት ዕድል ያለ ይመስልሃል?
ኢንስ አብርሃም:-እግር ኳስ ቀድሞ አይገመትም፤የሚፈጠረውንም ቀድመህ አታውቀውም።እነሱ አምስት ስላገቡ ሳይሆን አቅማችን የፈቀደውን አድርገን የሚገባንን ይዘን እንወጣለን፤ይህንን ስልህ በእግር የማይፈጠር የማይሆን ነገር ሊከሰት እንደሚችል ዘንግቼው አይደለም፤ኳስ ሰለሆነ።
7.ሀትሪክ:-የጨዋታውን መጠናቀቅን የሚያበሰረው ፊሽካ ሲነፋ የውጤት ሰሌዳው ኢትዮጵያ ስንት ጋና ስንት ይሆናል ገምት?
ኢንስ.አብርሃም በግምት መንቀሳቀስ ጥሩ ነው ብዬ አላስብም፤በግምት ልጆቼንም መገደም አልፈልግም።ስትግምት ልጆችህን ለጫና አሳልፈህ እንደምትሰጥ መረዳት አለብህ፤በጨዋታው አቅማችን የፈቀደውን አድርገን ዳኛው የጨዋታው መጠናቀቂያን ቀፊሽካው ሲያበስር ጥሩ ውጤት ይዘን ለመውጣት ነው የምንጥረው እንጂ ቀድሜ ከጨዋታ በፊት ብዙ ማውራትን አልመርጥም።
8.ሀትሪክ:-ለሴራሊዮን መታገድ ነው ለዕገዳው መነሳት የምትፀልየው?
ኢንስ አብርሃም:-እሰከ ፀሎት የሚያደርሰኝ ነገር ባይኖርም ነገር ግን የሴራሊዮን በውድድሩ ውስጥ መቆየትን እመርጣለሁ።ይሄ የሚሆን ከሆነ ጋናን ማሸነፍ ከቻልንና ከሴራሊዮን ነጥብ ይዘን መመለስ ከቻልን በድምር 10 ነጥብ ገብተን ወደ ፍክክሩና የአፍሪካ ዋንጫ የመመለስ ህልም እንዳለን አልሸሸግህም፤ቀጣይ ትኩረታችን 6 ነጥቦችን ፍለጋ ነው።
9.ሀትሪክ:-ይህ ጨዋታ የአሠልጣኝነት ዘመንህ ትልቁ ጨዋታ ነው ብሎ መጥራት ይቻላል?
ኢንስ.አብርሃም :-ትላልቅ የሚባሉ የከበዱ ጨዋታዎችን ከየመን ብ/ቡድን ጋር ባደርግም የኢትዮጵያ ብ/ቡድንን በዋናና በምክትል አሠልጣኝነት ይዜ ስሰራ ይሄ ትልቁ ጨዋታዬ ነው።
10.ሀትሪክ:-የካሜሮኑንን የ2019ኙን የአፍሪካ ዋንጫ በአካል ተገኝተህ ወይስ በቴሌቭዥን መስኮት በየትኛው የምትከታተል ይመስልሃል?
ኢንስ.አብርሃም:-እየለፋሁ ያለሁት በቴሌቭዝን ለመመልከት አይደለም ይልቁንም ያሉትን አማራጮች ተጠቅመን ሌሎች እኛን በቴሌቭዝን መስኮት እንዲመለከቱ ለማድረግም ነው።
10.ሀትሪክ:-ሀትሪክ:-ጌታነህ አለመኖሩ ተረጋግጧል፤ይህ መሆኑ የአጥቂ ክፍሉን ጥርስ የሌለው ያደርገዋል?
ኢንስ አብርሀም:-በፍፁም እንደውም እሱን ተክተው የሚገቡ ተጫዋቾች የተሻለ ተንቀሳቅሰው በትክክል ለመተካት የተዘጋጁ መሆናቸውን የሚያሳዩበት መልካም አጋጣሚም ይሆንላቸዋል።
ሀትሪክ:- የእረፍት ጊዜህን ተሻምተህ ለቃለ-ምልልሱ ስለተባበርከኝ hatricksport.com አንባቢዎች ስም አመሰግናለሁ፤መልካም ጨዋታ ድል ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን።
ኢንስ.አብርሃም:-እኔም አመሰግናለሁ፤
አስተያየት ይስጡ