የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ቆይታው ላይ ለሀዋሳ ከተማ ለሲዳማ ቡና ለኤሌክትሪክ እና ለወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርስቲ እንደዚሁም ደግሞ ለባህር ዳር እና በታዳጊ እና ወጣትነት ዕድሜው ደግሞ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ለቅዱስ ጊዮርጊስ ወጣት ቡድኖች ተጫውቶ ያሳለፈው የአማካይ ስፍራ ተጨዋቹ ብሩክ አየለ የፕሪሚየር ሊጉን ከዓመታት በኃላ ዘንድሮ በድጋሚ ለተቀላቀለው ደቡብ ፖሊስ ለመጫወት ለአንድ ዓመት ፊርማውን አኑሯል።
ባሳለፈው የእግር ኳስ ጨዋታ ዘመኑ የመሀል ሜዳው ላይ በሚያሳየው አበረታች ብቃት እና አጨዋወት የብዙዎችን ትኩረት ይስብ የነበረው ይኸው ተጨዋች ለደቡብ ፖሊስ መፈረሙ ከዚህ ቀደም በሀዋሳ ከተማ እና በሲዳማ ቡና አሰልጥኖት ካለፈው የቀድሞ አሰልጣኙ ዘላለም ሽፈራው /ሞውሪኖ/ ጋር ዳግም እንዲገናኝ ያስቻለው ሲሆን ተጨዋቹ በወልዋሎ ሳለ ደርሶበት ከነበረው ጉዳት ሙሉ ለሙሉ ድኖ በመምጣቱ ለአዲሱ ክለቡ በሙከራ ከታየ በኋላ እንደፈረመም ታውቋል።
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ዘንድሮ የተቀላቀለው ደቡብ ፖሊስ ከብሩክ ውጪ ሰሞኑን ሙልዓለም ረጋሳ እና አበባው ቡታቆን ማስፈረሙ ይታወሳል።