ፕሪሚየር ሊጉ ይካሄዳባቸዋል የተባሉ 7 ስታዲየሞች ሊገመገሙ ነው

ፕሪሚየር ሊጉ ይካሄዳባቸዋል የተባሉ 7 ስታዲየሞች ሊገመገሙ ነው

ፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን ቢሾፍቱ ላይ ለውይይት ባለድርሻ አካላትን ጠርቷል


የ2013 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የማስተናገድ እድል ያገኛሉ የተባሉ ሰባት ስታዲየሞች በባለሙያዎች ሊገመገሙ መሆኑን የሀትሪክ ምንጮች ገለፁ፡፡

ሀትሪክ ከታማኝ ምንጯ ባገኘችው መረጃ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን የማስተናገድ እድል ያገኛሉ የተባሉት ስታዲየሞች የባህር ዳር፣ የመቐለ፣ የአዲስ አበባ፣ የሀዋሳ፣ የድሬዳዋ፣ የአዳማና የጅማ ስታዲየሞች የተቀመጠውን መመዘኛ ያሟላሉ ወይስ አያሟሉም የሚለውን ከፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን፣ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከጤና ሚኒስቴርና በ……….የተውጣጡ 6 አባላት ያሉት ኮሚቴ መዋቀሩ ታውቋል፡፡
ስታዲየሞቹ ከሰኞ ጀምሮ የሚገመገሙ ሲሆን መፀዳጃ ቦታ ውሃና ሌሎች ሊሟሉ የሚገባቸው በፕሮቶኮሉ የተዘረዘሩ ሁኔታዎችን ማሟላታቸው ይገመገማል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የሊጉ የ2013 መርሃ ግብርን ለማስጀመር በሚመስል ደረጃ ፌዴራል ስፖርት ኮሚሽንም ከስሩ ካሉት ፌዴሬሽኖችና አሶሴሽኖች ጋር በጥምረት እየሰራ መሆኑ ታውቋል፡፡ ኮሚሽኑ ሁሉንም ስፖርቶች በሚመለከት መልኩ “የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተቋረጠውን የስፖርት እንቅስቃሴ ወደ ነበረበት ለመመለስ የሚረዳ የአሰራር መመሪያ” በሚል ፕሮቶከል እየተዘጋጀ መሆኑም የደረሰን መረጃ ያስረዳል፡፡
ፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን በሀገሪቱ ውስጥ ያሉትን ስፖርቶች በበላይነት እንደመምራቱ በስሩ ላሉ ተቋማት የውድደር ደንብን የያዘ ፕሮቶኮል ማዘጋጀት ቢኖርበትም በከፍተኛ ሁኔታ እየተንቀሳቀሱ ባሉት በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መቀደሙ በቀጣይ እንዳይደገም የተሻለ መሪነት ለመስጠት እየተጋ መሆኑ ታውቋል፡፡ እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ በስሩ ያሉትን ወደ 70 የሚጠጉ ክለቦችን ጠርቶ ካነጋገረ ከ2 ሳምንት በኋላ ፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን በሰሩ የሉትን ፌደሬሽኑኖች አመራሮችን ለማወያየት ዛሬ ቢሸፍቱ ላይ ቀጠሮ ይዟል፡፡ የክልልና ከተማ አስተዳደር እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ፕሬዚዳንቶች፣ የስፖርት ኮሚሽኖች አመራሮች እንዲሁም ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ያላቸው ባለድርሻ አካላት በውድደሩ ፕሮቶኮሉ ላይ ለመወያየት ስብሰባ መጥራቱ ታውቋል፡፡ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ተከትሎ ባለፈው ህዳር የተቋረጠው አሸናፊና ወራጅ ክለቦች የሌሉበት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ2013 መርሃ ግብር በመጪው ህዳር ወር ይጀመራል ተብሎ ቢወራም ፌዴሬሽኑ በፍጥነት አስተባብሏል፡፡ “ማንም ሰው ነገን አያውቅም፡፡ በኛም በኩል እንደ ፌዴሬሽን ነገ ምን ይዞ እንደሚመጣ አናውቅም፡፡ በወጣው ፕሮቶኮል ላይ የመንግሥትም ምላሽ ምን እንደሚሆን ባልታወቀበት ሂደት ህዳር 1 ሊጉ ይጀመራል የሚለው ፍፁም የሆነ ውሸት ነው ፌዴሬሽኑም የሰጠው መግለጫ የለም፡፡ ይሄ የፌስ ቡክ መንደር ወሬ ነው በእኛ በኩል ሊጉን ለማስጀመር ግን የምንችለው ሁሉ እናደርጋለን ከሊግ ካምፓኒውና ከመንግሥት ጋር ጥሩ ግንኙነት ፈጥረን እየተንቀሳቀስን ነው” ሲሉ የፌዴሬሽኑ ዋና ፀሐፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን በተለይ ለሀትሪክ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በኢትዮጵያ እይጨመረ መሄዱና የሚያዙት ሰዎች ቁጥር በቀን ከ1000 በላይ በሆነበት የ2013 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ይካሄዳል ወይ? የሚለው የብዙዎች ስጋት ሆኗል፡፡

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport