ፊፋ ጅማ አባጅፋርን ከተጨዋች ዝውውር ማገዱ ተሰማ !

 

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊው ክለብ ጅማ አባ አፋር የቀድሞውን ጋናዊ ግብ ጠባቂው ዳንኤል አጃይ ደሞዝ መክፈል ባለመቻሉ ምክንያት ለቀጣዮቹ ሶስት የዝውውር መስኮት ከማንኛውም የተጫዋቾች ዝውውር ማገዱን አሳውቋል ፡፡

ከወራት በፊት ጅማ አባ ጅፋር ለተጫዋቹ ቀሪ ክፍያ መፈፀማቸውን የሚያሳይ የሰነድ ማስረጃ እንዲያሟሉ የተጠየቀ ቢሆንም ማስረጃውን አለማቅረባቸው በተገኘው መረጃ ለማወቅ ተችሏል ።

የ 2010 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮናዎች የቀድሞውን የጋና ብሔራዊ ቡድን ኮከብ ግብ ጠባቂ ክፍያ መፈፀማቸውን የሚያሳይ ምንም ዓይነት ሰነድ ማቅረብ አልመቻላቸው ተገልጿል ።

ጅማ አባ ጅፋር የዳንኤልን አጃይን ክፍያ ሙሉ ለሙሉ በከፈለ ሰዓት እገዳው እንደሚነሳ የተጫዋቾች ወቅታዊ ሁኔታ ሀላፊ ኤሪካ ሞንቴሞር ፌሬራ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና ለጅማ አባ ጅፋር ክለብ በላኩት ደብዳቤ አሳውቀዋል ።


ሀትሪክ ስፖርት የጅማ አባ ጅፋር ስራ አስኪያጅን አቶ ሱልጣንን ለማነጋገር ብንሞክርም ከአጭር የስልክ ቆይታ በኋላ ስልካቸውን ስለዘጉበን ለማግኘት አልተቻለም ።

ሀትሪክ ስፖርት ከክለቡ የውስጥ ምንጭ ለማግኘት እንደቻለችው ጅማ አባ ጅፋር ከዳንኤል አጃይ በተጨማሪ የቀድሞው የክለቡ ተጫዋቾች ዲድዬ ሌብሪ እና ማማዱ ሲዲቤ በተመሳሳይ ክፍያ ያልተፈፀመላቸው ተጫዋቾች መሆናቸውን ለማወቅ ችላለች ። ከዚህ በተጨማሪ ከህዳር ወር አንስቶ አንዳንድ የክለቡ ተጫዋቾች እስከ አሁን ደሞዝ እንዳልተከፈላቸው ለማወቅ ተችሏል ።

ሀትሪክ ስፖርት በቀጣይ የክለቡ ፕሬዝዳንት አቶ አጃኢብን ለማናገር ስትችል ስለ ጉዳዩ የሰሙት ነገር እንደሌለ በመረጃው ከላይ እንደተገለፀው በሚያዚያ ወር ደብዳቤ መላካቸውን እና ከዳንኤል አጃይ በተጨማሪ የዲድዬ ሌብሪ እና ማማዱ ሲዲቤን መረጃ ለፊፋ መላካቸውን ገልፀው ጉዳዩ በሂደት ላይ እንዳለ ብቻ እንደሚያውቁ ገልፀውልናል ።

በቀጣይነት ይህ መረጃ በኢሜል ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሚላክ በመሆኑ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን ብንደውልም ስልካቸው ዝግ በመሆኑ ልናገኛቸው አልቻልንም ።

ሀትሪክ ስፖርት በዚህ ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የምታገኘውን መረጃ እንደደረስን የምናቀርብ ይሆናል ።

Hatricksport website Editor

Twitter

kidus Yoftahe

Hatricksport website Editor