“ፊፋ የወሰነብን ውሳኔ የአገር ሉዓላዊነትን ከመድፈር አይተናነስም” አቶ ገዛኸኝ ወልዴ /የኢት.ቡና እግር ኳስ ክለብ ዋና ስራ አስኪያጅ/

በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋ የዑጋንዳዊው ቦባን የ6 ወር ደመዝ እንዲከፍል ኢትዮጵያ ቡና ላይ የተላለፈው ውሣኔ የሀገር ሉዓላዊነትን ከመድፈር የተናነሰ አይደለም ተባለ፡፡
የኢትዮጵያ ቡና ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ በተለይ ለሀትሪክ እንደገለፁት ተጨዋቹ ደመወዝ ይከፈለኝ የሚለው ጥያቄ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የፍትህ አካላት አቅርቦ ውሣኔ ሳያገኝ በቀጥታ ለፊፋ መክሰሱ ሉአላዊነትን መጋፋት ነው ሲሉ ኮንነዋል፡፡

“የእውነት ጠንክሮ መከራከር ቢቻል ኖሮ ክለባችን የማሸነፍ እድል ነበረው፡፡ ካፍ ላይ ይግባኝ ጠይቀን የነበረ ቢሆንም ጊዜው ስላለፈ የተወሰነውን ውሣኔ መቀልበሱ ከባድ ሆኖብናል፡፡ ነገር ግን በወቅቱ የነበሩት አሰልጣኝ ፈረንሣዊው ዲዲየር ጎሜዝ ተገቢውን ሂደት ተከትለው ነው ያሰናበቱት… በደንብ ተዘጋጅቶ ሉዛን ስዊዘርላንድ ድረስ ሄዶ መከራከር ቢቻል የማሸነፍ እድል ነበረን.. የተሟላ ዶክመንት አለን ለተጨዋቹ በተከታታይ የተሰጠው ደብዳቤ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬስንን ሕግና ደንብ መሰረት አድርገው በመሆኑ የመርታት እድሉ ነበረን፤ ነገር ግን የተጨዋቹ ደቡብ አፍሪካዊው ጠበቃ ጠንክሮ መፋለሙና በኛ በኩል መከራከር ባለመቻሉ የተሰጠውን ውሣኔ ከመቀበል ውጪ አማራጭ የለንም” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

“ቀሪ የ6 ወር ደመወዝ መክፈል እንዳለብን ተወስኖብናል፡፡ ፊፋ ጠንካራ ተቋም በመሆኑ ያለንን ከማድረግ ውጪ አማራጭ የለንም ውሣኔው ከተወሰነ በኋላ ወደ ኃላፊነቱ በመምጣቴ ምንም ማድረግ አልቻልኩም፡፡ ባለኝ ትውውቅ ግን ሁኔታውን ካስ /ዓለም አቀፉ የግልግል ፍ/ቤት/ ላሉ ሰዎች አናግሬ ነበር ነገር ግን ውሣኔው ከተወሰነ 3 ወር ያለፈው በመሆኑና የሚፈቀደው ጊዜ በማለፉ ምንም ማድረግ አንችልም ሕጉ እንደሚለው ውሣኔው በተወሰነ በአንድ ወር ውስጥ ቢመጣ ኖሮ ልናየው እንችል ነበር አሁን ግን ውሣኔውን ከመተግበር ውጪ አማራጭ የላችሁም በማለት ነግረውኛል” ያሉት አቶ ገዛኸኘ “ለመክፈል ተስማምተናል ትልቁ ችግር ግን ክለቡ ለተጨዋቹ በዶላር መክፈል አይችልም የምንገበያየው በብር ስለሆነ.. ሰውየው ደግሞ ወደ ደቡብ አፍሪካ ባንክ አዛውሩልኝ ብሏል ክለቡ ግን ወደ ደቡብ አፍሪካ የመላክ መብትና ስልጣን የለውም፡፡ ተጨዋቹ ከፈለገ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ወይም ሀገር ውስጥ አካውንት ከፍቶ ገንዘቡን መውሰድ ይችላል ቅጣት እንዳይጣልብን ሁኔታውን ለፊፋ አሳውቀን ፍቃድ አግኝተናል የተጨዋቹን ምላሽ እየጠበቅን ነው” በማለት ሁኔታውን ለሀትሪክ ገልፀዋል፡፡ ከክፍያው ጋርም ተያይዞ ኢትዮጵያ ቡና በፊፋ የሚቀጣበት ምክንያት እንደሌለም አረጋግጠዋል፡፡

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport

One thought on ““ፊፋ የወሰነብን ውሳኔ የአገር ሉዓላዊነትን ከመድፈር አይተናነስም” አቶ ገዛኸኝ ወልዴ /የኢት.ቡና እግር ኳስ ክለብ ዋና ስራ አስኪያጅ/

  • September 14, 2020 at 1:17 pm
    Permalink

    Mejemereya askedemo mekefel .endewem leethiopia sport ante neh enkefat yehonkebet gefi

Comments are closed.