“ይሄንን ምርጥ ክለብና ደጋፊ ትቶ የመሄድ ሃሣብ የለኝም፤ነገሮች ናቸው እየገፉኝ ያሉት” ፈቱዲን ጀማል

ኢት ቡናና ፈቱዲን ጀማል ስምምነት ላይ መድረስ አልቻሉም

በያዝነው አመት በኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ውስጥ ጎልተው ከወጡ ተጨዋቾች አንዱ ፈቱዲን ጀማል ነው፤ተጨዋቹ ከክለቡ ጋር ያለው ኮንትራት የፊታችን ሐምሌ 30 የሚጠናቀቅ ቢሆንም ተጫዋቹ ከክለቡ ጋር ይቀጥላል?…አይቀጥልም?የሚለው እስከ አሁን ቁርጥ ያለ ምላሽ አላገኘም፡፡

ከዚህ ከተጨዋቾች ውል ጋር በተያያዘ ኢት.ቡና የአህመድ ረሺድ (ሽሪላን)፣የተመሰገን ካስትሮንና የአማኑኤል ዮሐንስን ኮንትራት ማራዘማቸውን ያረጋገጡ ሲሆን ሌላው በክለቡ ደጋፊዎች ዘንድ በትኩረት ሲጠበቅ የነበረው የተከላካዩ ፈቱዲን ጀማል ኮንትራትን ግን ማራዘም እንዳልቻለ ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት፡፡
ለአላባ ከተማ፣ለወላይታ ድቻ ለሲዳማ ቡና በመጨረሻም ለኢትዮጵያ ቡና በመጫወት የእግር ኳሱ ሌላኛው ክስተት ሆኖ ብቅ ያለውን የፈቱዲን ጀማል ጉዳይን ከኢት.ቡና ጋር እየተደራደረ የሚገኘው የተጨዋቹ ኤጀንት ሲሆን እስከ አሁን በነበራቸው ውይይትና ድርድር በተለይ በጥቅማጥቅም ጉዳይ ላይ ስምምነት ላይ መድረስ እንዳልቻሉ ነው እየተሰማ ያለው፡፡
በተለይ ከሳምንት በፊት ክለቡና የተጨዋቹ ኤጀንት በዚሁ ጉዳይ ያደረጉት ውይይት ያለ ስምምነት መጠናቀቁ ብዙዎች ፈቱዲን በቀጣይ የውድድር ዘመን መለያውን ለብሶ ስለመጫወቱ ጥርጣሬ ውስጥ እንዲወደቁ አድርጓቸዋል፡፡
በተለይ የተጨዋቹ ኤጀንትና ክለቡ በነበራቸው ድርድር ስምምነት ላይ አለመድረሳቸውን ተከትሎ መቐለ 70 አንደርታ፣ፋሲል ከነማ፣ሲዳማ ቡናና ሐዋሳ ተጨዋቹን በእጃቸው ለማስገባት ጥረት እያደረጉ ሲሆን መቐለ 70 እንደርታና በተለይ አዲስ ግደይን ያጣው ሲዳማ ቡና ተጨዋቹን የግላቸው በማድረጉ በኩል የዝውውር ሩጫውን እየመሩና ለስምምነት እየተቃረቡ እንደሆነ ምንጮች ለሀትሪክ ጠቁመዋል፡፡
እንደ ታማኝ የዜና ምንጮቻችን ከሆነ የቡናውን ቁልፉ ሰው በእጅ በማስገባት በኩል ሲዳማ ቡና የተሻለ አማራጭ ለተጨዋቹ በማቅረብ ለስምምነት እየተቃረቡ እንደሆነ ተናግሯል፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየቱን እንዲሰጠን በእጅ ስልኩ ላይ በመደወል “ከኢት.ቡና ጋር ጨክነህ ልትለያይ” በማለት የተጠየቀው ፈቱዲን “አሁን ስልኩን ድንገት ስላነሳሁት እንጂ በዚህ ሰዓት በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ምንም አይነት ምላሽ መስጠት አልፈልግም፤እኔ ቀደም ሲል ፍላጎቴን ገልጬያለሁ፤ለኢትዮጵያ ቡና መጫወት ክብርም ትልቅ ነገርም ነው፤አሁንም ይሄንን ምርጥ ደጋፊ ትቼ የመሄድ ፍላጎቱ የለኝም፤በጥቅማጥቅም ጉዳይ ላይ ስምምነት ላይ መድረስ አለመቻላችንና ያለው ነገር ነው እየገፋኝ ያለው፤ከዚህ በላይ ምንም የምልህ ነገር የለኝም” በማለት ፈቱዲን አስተያየት የመስጠት ፍላጎት እንደሌለው ስልኩን ጆሮአችን ላይ በመዝጋት አረጋግጧል፡፡

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor.
The First Color Sport Newspaper in the country.

Yishak belay

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor. The First Color Sport Newspaper in the country.