የ2013 ፕሪሚየር ሊግ ጅማሮ ዙሪያ ግምገማ እየተካሄደ ነው በዝግ ይካሄዳል… በቴሌቬዥን ይተላለፋል

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የ2013 ዓ.ም መርሃ ግብር የሚካሄድበትን የውድድር ፕሮቶክልን አዘጋጅቶ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር እየገመገመ መሆኑ ተሰማ፡፡

በፌዴሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባዘጋጀው የውድድሩ ፕሮቶኮል መሠረት ጨዋታዎቹ በዝግ ስታዲየም የሚካሄድና በተመረጡ ስታዲየሞች የሚካሄደው ጨዋታ በቲቪ የቀጥታ ስርጭት የሚያገኝ መሆኑ ታውቋል፡፡ እያንደንዱ ተጨዋች ግጥሚያ ከመካሄዱ 72 ሰዓታት በፊት የኮቪድ 19 ምርመራ ውጤት ማቅረብ እንዳለበት ተገልጿል፡፡ ሁሉም ክለብ ሁለት ሁለት አውቶቢስ ማቅረብ የሚጠበቅባቸው ሲሆን ይህም ተጠጋግቶ መሄድን ለማስቀረት ታስቦ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሁሉም ተጨዋች የኃይላንድ ውሃ ሲጠጣ በስሙ በተጋጀለት የውሃ ላስቲክ ብቻ ይሆናል ሲል እየተዘጋጀ ያለው ፕሮቶኮል ያስረዳል፡፡ ያም ሆኖ ዳኞችና ኮሚሽነሮችን በተመለከተ የገለፀው ነገር አለመኖሩ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ አስገራሚው ነገር ይሄ ፕሮቶኮል የሚያስከትለው ወጪ ከመንግሥት ካዝና እንጂ ክለቦች ከሚያገኙት የራሣቸው ገቢ የሚያወጡ አለመሆኑ ተፈፃሚነቱ ላይ አጠያያቂ ሆኗል፡፡ መረጃው ለሀትሪክ ያቀበለው ምንጫችን ከተለያዩ ሀገራት ተሞክሮ ተወስዶ ወደ ሀገር ውስጥ ሲተገበር ክለቦች ከመንግሥት ካዝና እንጂ ምንም ገቢ በሌለበት መሆኑ ግን ግርምትን ፈጥሯል፡፡

ለአውሮፓና ላደጉት አፍሪካ የእግር ኳስ ሀገራት ክለቦች የሜዳ ገቢ ኢምንት ነው የቲቪ ገቢያቸው ግን የትየለሌ ነው፤ እዚህ ሀገር ግን የቲቪ ገቢ ፈፅሞ የማይታሰብ በመሆኑ ሙሉ በሙሉ እንዴት ይኮረጃል ሲል ምንጫችን ጠይቋል፡፡ ክለቦች ለተጨዋቾቹ የወር ደመወዝ ክፈሉ አትክፈሉ ግብግብ ባለበት ሰዓት ተጨማሪ ገንዘብ የሚያስፈልገው ፕሮቶኮል መዘጋጀቱ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ በዚህ እየተዘጋጀ ባለው ፕሮቶኮል ዙሪያ የፌዴሬሽኑ የጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን ውይይት እየተደረገበት መሆኑን አምነዋል፡፡ “ፌዴሬሽናችን ጥሩ ነው ያለውን የውድድር ፕሮቶኮል ማዘጋጀቱን ያምናል ጤና ሚኒስቴር፣ ፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን፣ ከኢትዮጵያ ጤና ሳይንት ኢንስቲቲዩት ጋር ፕሮቶኮሉን የማዳበር ስራ እየተሰራ ነው፤ ገና ለመፅደቅ ብዙ ይቀረዋል ከላይ የጠቀስኳቸው አካላት ጋር በየጊዜው እየተገናኘን እየተወያየን ነው፤ ወደፊት የተሻለና የሚያሰራ የውድድር ፕሮቶኮል ተዘጋጅቶ ወደ ተግባር እንገባለን ብለን እናስባለን፡፡ ከዚህ በኋላ ክለቦችን ጠርተን እናወያየለን፤ አሁን ያለው ሁኔታ ይሄ ነው” ሲሉ ለሀትሪክ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport