በ2010 ህዳር ላይ የተጀመረው እና በዛው አመት መጠናቀቅ እያለበት በተለያዩ ምክንያቶች እየተጎተተ እና እየተንከባለለ ወደ 2011 የተዛወረው የኢትዮጵያ ዋንጫ ዛሬ ፍፃሜውን የሚያገኝ ይሆናል።
በሀዋሳ አርቲፊሻል ስታዲየም ሲደረግ የቆየው ይህ ውድድር ዛሬ 9:00 ሲል በሀዋሳ ኢንተርናሽናል ስታዲየም መከላከያ ከቅ/ጊዮርጊስ በሚያደርጉት የፍፃሜ ጨዋታ መዝጊያውን የሚያደርግ ይሆናል። በተጠናቀቀው የ2010 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለቱ ቡድኖች ተገናኝተው በአንደኛው ዙር 0-0 እንዲሁም በሁለተኛው ዙር ደግሞ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት አጠናቀው አመቱን ሳይሸናነፉ ተለያይተዋል። መከላከያ ለተከታታይ 4ኛ ጊዜ የኢትዮጵያ ዋንጫ ፍፃሜ ላይ የሚሳተፍ ሲሆን ቅ/ጊዮርጊስ ደግሞ ከ2006 ዓ.ም በኋላ ከአፍሪካ መድረክ ላለመራቅ ከፍተኛ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
መከላከያ በግማሽ ፍፃሜው ኢትዮጵያ ቡናን በምንይሉ ወንድሙ ብቸኛ ጎል 1-0 በማሸነፍ እንዲሁም ቅ/ጊዮርጊስ ደግሞ ጅማ አባጅፋር በግማሽ ፍፃሜው አልሳተፍም በማለቱ በፎርፌ በማሸነፍ ለፍፃሜ ሊበቁ ችለዋል። ሁለቱ ቡድኖች ከ2006 ጀምሮ 3 ጊዜ ለፍጻሜ የተገናኙ ሲሆን 2006 ላይ በመደበኛ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 0-0 ተለያይተው መከላከያ በመለያ ምት ሲያሸንፍ በ2008 በመደበኛ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 0-0 ተለያይተው ቅ/ጊዮርጊስ በመለያ ምት አሸናፊ መሆን ችለዋል። ለሶስተኛ ጊዜ በሚገናኙበት የ2010 የኢትዮጵያ ዋንጫ ማን አሸናፊ ይሆናል የሚለው በኢትዮጵያ እግርኳስ አፍቃሪያን ዘንድ ጨዋታውን ተጠባቂ አድርጎታል። ሁለቱ ቡድኖች ከ2008 ጀምሮ በፕሪሚየር ሊጉ 6ጊዜ የተገናኙ ሲሆን 1 ጊዜ መከላከያ 1 ጊዜ ቅ/ጊዮርጊስ ሲያሸንፍ ቀሪዎቹን 4ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ማጠናቀቅ ችለዋል።
የሁለቱ ቡድኖች አሸናፊ የዋንጫ ባለቤት ከመሆኑ ባሻገር ከ2010 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊው ጅማ አባጅፋር ቀጥሎ በአፍሪካ ውድድር (በአፍሪካ ኮንፌደሬሽን ዋንጫ) ኢትዮጵያን የሚወክል ይሆናል። የሁለቱን ቡድኖች ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ በዋና ዳኝነት ክንፈ ይልማ እና አበራ አብርደው በረዳት ዳኝነት እንዲሁም ሄኖክ አክሊሉ በአራተኛ ዳኝነት የሚመሩት ይሆናል።
አስተያየት ይስጡ