የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች 300 ሺህ ብር ይመለስልን እያሉ ነው

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መቋረጡን ተከትሎ ለአመቱ የከፈልነውን የመመዝገበያ ክፍያ መልሱልን የሚሉ ክለቦች ብቅ ብቅ እያሉ ነው፡፡

ሀትሪክ ባገኘችው መረጃ ለ2012 ፕሪሚየር ሊግ መመዝገቢያ አንድ ክለብ 780 ሺህ ብር የከፈለ ሲሆን በአጠቃላይ 12 ሚሊዮን 480 ሺህ ብር ለአወዳዳሪ አካል ገቢ ማድረጋቸው የሚታወቅ ነው፡፡ ነገር ግን ሊጉ 17 ሳምንት ከተካሄደ በኋላ መቋረጡ ቀሪ 13 ጨዋታዎች እንዳይካሄድ አድርጓል፡፡ ክለቦቹም ከከፈልነው 780 ሺህ ብር የ13 ጨዋታ ክፍያ ተቀንሶ ይሰጠን እያሉ መሆናቸው ተሰምቷል፡፡ ከክፍያ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና የ2012 አዲሱ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አዘጋጅ አብይ ኮሚቴ ጋር በተለያየ ጊዜ ገንዘቦችን እያወጡ ሲጠቀሙ የነበረ ከመሆኑ አንፃር ጫናው ሁለቱ ወገኖች ላይ መጥቷል፡፡
የሀትሪክ ምንጮች እንደገለፁት በእስካሁኑ ሂደት ወልቂጤ ከተማና ወላይታ ድቻ የይመለስልን ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን ሌሎች ክለቦችም ተመሳሳይ ጥያቄ ሊያቀርቡና ሌላው የክርክር ምክንያት ሊሆን ይችላል ተብሎ ተሰግቷል፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ የሊግ ካምፓኒው ሰብሳቢው መቶ አለቅ ፍቃደ ማሞ እንደተናገሩት ከፌዴሬሽኑ ጋር ቁጭ ብለን ሂሳቡን ከተሳሰብን በኋላ ከወጪ ቀሪው ወደ አክስዮን ገቢ መደረጉ የግድ ነው በሁለት አካላት የተሰባሰበ ገንዘብ እንደመሆኑ ሂሳቡ ከተሰራና ቁጭ ብለን ከተነጋገርን በኋላ ውሳኔውን የምናሣውቅ ይሆናል ቢሉም የፌዴሬሽኑ ጊዜያዊ ዋና ፀሐፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን በበኩላቸው ሊጉ እስኪቋረጥ ድረስ ባለው 17 ሳምንት ወጪ ስናደርግ የነበርነው እኛ ነን፡፡ እኛ ጋር ያለው ገንዘብ፣ ወጪ ያደርግነው አሰልተን ከውጪ ቀሪ ያላቸው ብር ለሊግ ካምፓኒው አሳውቀናል፤ የሚቀረው ቁጭ ብሎ መተማመን ብቻ ነው፡፡ እንደፌዴሬሽን ግን የክለቦች ቀሪ ገንዘብ የመመለስ የቤት ስራው የኛ አይደለም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ክለቦቹ ከከፈሉት 780 ሺህ ብር መሀል በጨዋታ 26 ሺህ ብር የሚከፍሉ ሲሆን አሁን በ13 ጨዋታ ከ300 ሺህ እስከ 320 ሺህ ብር ድረስ እንዲመለስላቸው ይጠብቃሉ ሲል የሀትሪክ ምንጭ ገልጿል፡፡

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport