የጨዋታ ዘገባ | ድሬዳዋ ከተማ እና ፋሲል ከነማ ነጥብ ተጋርተዋል።

 

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 17ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ትናንት (ሀሙስ) እና ዛሬ (አርብ) የተከናወኑ ሲሆን ከነዚህ ጨዋታዎች በኋላም በብሔራዊ ቡድኑ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ምክንያት ሊጉ ለቀጣዮቹ 21ቀናት እንደሚቋረጥ ይታወቃል። በ17ኛ ሳምንት ከተደረጉ ጨዋታዎች ድሬ ላይ ድሬዳዋ ከተማ ፋሲል ከነማን ያስተናገደበት ጨዋታ አንዱ ሲሆን በውጤቱም ሁለቱ ቡድኖች ያለግብ ጨዋታቸውን አጠናቀዋል።

የመጀመሪያው አጋማሽ የመጀመሪያ 10ደቂቃዎች በፈጣን እንቅስቃሴ የጀመሩ ቢሆንም ከዛ በኋላ ግን እየተቀዛቀዘ እየሄደ በሁለቱም ቡድኖች መካከል ረጃጅም ኳሶች ሲጣሉ ተስተውሏል። በጨዋታው የመጀመሪያውን ሙከራ በማድረግ ቅድሚያ የወሰዱት ፋሲል ከነማዎች ሲሆኑ 15ኛው ደቂቃ ላይ የድሬዳዋ ከተማው ያሬድ ዘውድነህ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን ቅጣት ምት የፋሲል ከነማው ሱራፌል ዳኛቸው በቀጥታ ሞክሮት በተከላካዮች ተመልሷል። ከዚህች ሙከራ በኋላ መነቃቃት ያሳዩት አፄዎቹ ያልተረጋጋውን የድሬን የመሀል እና የተከላካይ ክፍል ሲረብሹት ውለዋል። ይህንንም ተከትሎ 22ኛው ደቂቃ ላይ ሙጂብ ቃሲም ያመከናት ኳስ በፋሲል ከነማ በኩል መሪ ልታደርጋቸው የምትችል እና እጅግ በጣም የምታስቆጭ ነበረች።

ከ25ኛው ደቂቃ በኋላ ተረጋግተው ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት እያደረጉ የነበሩት ድሬዎች ተደጋጋሚ ሙከራ ለማድረግ ችለዋል። በዚህም ሁለት ቅጣት ምቶችን ሞክረው በአፄዎቹ ተከላካዮች በቀላሉ ተመልሰዋል። 27ኛው ደቂቃ ላይ የድሬዳዋ ከተማው ሪችሞንድ ኦዶንጎ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን ቅጣት ምት ኤልያስ ማሞ ቢመታውም ለጥቂት ወደ ውጭ ወጥቶበታል። የተቀዛቀዘና ጥፋት በበዛበት የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ ጨዋታ ወደጎል በመድረስ ረገድ ፋሲል ከነማ የተሻለ ሲሆን ድሬዎች በአንጻሩ ወደኋላ በማፈግፈግ ረጃጅም ኳሶችን ለመጠቀም ሲሞክሩም ነበር። በዚሁም የመጀመሪያው አጋማሽ ያለምንም ግብ ወደ እረፍት አምርቷል።

ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው አጋማሽ እጅግ የተቀዛቀዘ የነበረ ሲሆን የመሀል ሜዳ ሽኩቻ እና ጥፋት ባሻገር ያን ያህል አስደንጋጭ ሙከራ እንኳን አልተስተዋሉበትም። 72ኛው ደቂቃ ላይ የፋሲል ከነማው አማካይ ሱራፌል ዳኛቸው የመታው ቅጣት ምት እና ለጥቂት የወጣው ኳስ በሁለተኛው አጋማሽ ሊጠቀስ የሚችል ሙከራ ነበር። የጨዋታው መጠናቀቂያ ሲቃረብ እና 5ደቂቃዎች ሲቀሩት 85ኛው ደቂቃ ላይ ድሬዎች ግብ አስቆጥረው የነበረ ቢሆንም የእለቱ አርቢትር ጥፋት ተሰርቷል ብለው ግቧን ሽረዋታል። ከዚህ በኋላ ይህ ነው የሚባል ሙከራ ሳይደረግበት ጨዋታው ያለግብ ተጠናቋል።

ውጤቱንም ተከትሎ ባለሜዳው ድሬዳዋ ከተማ በ21ነጥቦች 13ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ተጋጣሚው ፋሲል ከነማ በአንፃሩ በ30ነጥቦች የሊጉ አናት ላይ ተቀምጧል። ጅማ አባጅፋር በ19፣ ወልዋሎ አ.ዩ. በ18 እንዲሁም ሀድያ ሆሳዕና በ14ነጥቦች ወራጅ ቀጠናው ውስጥ የመጨረሻዎቹን 3ደረጃዎች ይዘዋል።

hatricksport team

Hatricksport team

Facebook

hatricksport team

Hatricksport team