የጨዋታ ዘገባ | ድሬዳዋ ከተማ እና ስሑል ሽረ ነጥብ ተጋርተዋል።

 

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 13ኛ ሳምንት 4ጨዋታዎች ሲደረጉ ድሬዳዋ ስታዲየም ላይ ስሑል ሽረን ያስተናገደው ድሬዳዋ ከተማ 1-1 አቻ ተለያይተዋል።

ድሬዳዋ ከተማ በ12ኛ ሳምንቱ ጨዋታ ወላይታ ድቻን ከገጠመው ቡድን ውስጥ በረከት ሳሙኤል በ ዘሪሁን አንሼቦ ተክቶ ጨዋታውን ሲጀምር ስሑል ሽረ ደግሞ ዮናስ ግርማይ፣ ሙሉዓለም ረጋሳ እና ሰዒድ ሀሰንን አስወጥቶ በረከት ተሰማ፣ ክፍሎም ገ/ህይወት እና ያሲር ሙገርዋ በመቀየር ጨዋታቸውን ጀምረዋል።

ስሑል ሽረዎች ጨዋታውን በተሻለ የጀመሩ ቢሆንም ቅድሚያ ግብ ለማስቆጠር የቻሉት ባለሜዳዎቹ ነበሩ። 8ኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ ሀሰን በግሩም ሁኔታ ያቀበለውን ኳስ በዘንድሮው የውድድር ዓመት ጥሩ ብቃቱን እያሳየ የሚገኘው ሙኸዲን ሙሳ አስቆጥሮ ባለሜዳዎቹን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። ይህ ግቡም በሊጉ ያስቆጠረው 4ኛ ግቡ ሆኖ ተመዝግቧል። ከግቡ መቆጠር በኋላም ኳስ ተቆጣጥረው ለመጫወት ሲሞክሩ ተስተውለዋል።

በስሑል ሽረ በኩል በድሬዳዋ የነበረው ሙቀት ከብዷቸው የታዩ ሲሆን መሀል ሜዳው ላይ ብልጫ ተወስዶባቸዋል። ይህንንም ተከትሎ ወደኋላ አፈግፍገው የተጫወቱት እንግዳዎቹ በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ጥረት አድርገዋል። ሆኖም የጨዋታውን መልክ የሚቀይር አንድ ክስተት 32ኛው ደቂቃ ላይ ተፈጠረ። የስሑል ሽረው ግብ ጠባቂ ወንደሰን አሸናፊ በሰራው ጥፋት ከሜዳ በቀይ ካርድ ተወግዷል። ስሑል ሽረዎችም ቀሪውን 58ደቂቃዎች በ10በ ተጫዋቾች ለመጫወት ተገደዋል።

የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ 2ደቂቃዎች ሲቀሩት 43ኛው ደቂቃ ላይ የድሬዳዋ ከተማው ያሬድ ታደሰ የመታውን ኳስ ተቀይሮ የገባው የስሑል ሽረው ግብ ጠባቂ ዋልታ አንደይ አውጥቶበታል። ከዚህ በኋላም የድሬዳዋው አጥቂ ሬችሞንድ ኦዶንግ የሞከረውን ኳስ ግብ ጠባቂው ይዞበታል። የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ በጭማሪ ሰዓት ላይ እንግዳዎቹ ግብ አስቆጥረው የነበረ ቢሆንም ከጨዋታ ውጪ በመሆኑ ተሽሯል። ከዚህ ሙከራ በኋላ ይሄ ነው የሚባል ጨዋታ ሳይስተዋልበት የመጀመሪያው አጋማሽ በባለሜዳዎቹ 1-0 መሪነት ተጠናቋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ተጀምሮ ድሬዎች ብልጫ ወስደው በመጫወት 50ኛው ደቂቃ ላይ ሬችሞንድ ኦዶንግ አመቻችቶ የሰጠዉ ያለቀ ኳስ ያሬድ ሀሰን ተንሸራቶ በመውደቁ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ከዚህ ሙከራ 3ደቂቃዎች በኋላ ቢኒያም ጥዑመልሳን ለሙኸዲን የሰጠዉን ኳስ ግብ ጠባቂዉን አልፎ ቢመታዉም የግቡን ቋሚ ታካ ወጣች። ስሑል ሽረዎች በመልሶ ማጥቃት ጨዋታውን ለመቆጣጠር ሲሞክሩ ተስተውለዋል።

ከዚህ በኋላም በጎዶሎ ተጫዋች ሲጫወቱ የነበሩት ስሑል ሽረዎች ወደኋላ አፈግፍገው በመልሶ ማጥቃት ወደ ድሬዳዋ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረት አድርገዋል። ይህንንም ተከትሎ 75ኛው ደቂቃ ላይ የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ሀብታሙ ሸዋለም ወደ ግብነት ቀይሮት እንግዳዎቹን አቻ ማድረግ ችሏል። ከዚህም በኋላ ሌላ ግብ ሳይስተናገድበት በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ውጤቱንም ተከትሎ ድሬዳዋ ከተማዎች በ14 ነጥቦች 14ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ እንግዳዎቹ ስሑል ሽረዎች በ20ነጥቦች 4ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

📷 Dire soccer

hatricksport team

Hatricksport team

Facebook

hatricksport team

Hatricksport team