የጨዋታ ዘገባ | ክትፎቹ ከፈረሰኞቹ ላይ ጣፋጭ ሶስት ነጥብ ነጥቀዋል

 

የመጀመሪያውን ዙር በመሪነት ያጠናቀቀው ቅዱስ ጊዮርጊስን እና አዲስ አዳጊውን ወልቂጤ ከተማ በ16ተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በአንጋፋው አዲስ አባባ ስታድዮም ዛሬ 10 ሰዓት ላይ መገናኘት ችለዋል።

በሊጉ በፋሲል ከነማ በአንድ ተበልጦ መሪነቱን ለማስመለስ ወደ ሜዳ የገባው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአዳማ ነተማ ጋር አቻ ለወጣው ቡድኑ ሁለት ቅያሬ በማድረግ ተከላካዩን ፍሪንፖንግ ሜንሱን በሳላዲን በርጌቾ እና አቡበከር ሳኒን ከጉዳት በተመለሰው ጋዲስ መብራቴ ቀይሮ ወደ ሜዳ ገብቷል። በአሰላለፍ ረገድም ጌታነህን ከ 10 ቁጥር ወደ ተፈጥሯዊ የፊት አጥቂነት ቦታ በመመለስ እና አቤል ያለው እና ጋዲሳ መብራቴን በመስመር አጥቂነት በማጫወት ነበር ጨዋታውን የጀመሩት።


በወልቂጤ ከተማ በኩል ከዚህ ቀደም የተለመደውን አቀራረባቸውን ይዘው የገቡ ሲሆን በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎችም ወደ ሃላ አፈግፍገው በመከላከል የሚገኙ ኳሶችን በረጅሙ ለመስመር ተጫዋቻቸው ጫላ ተሺታ እና ለአጥቂያቸው አህመድ ሁሴን ኳስን በማቀበል የግብ እድል ለመፍጠር ሲሞክሩ ታይተዋል።

በመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች የመስመር ተከላካዮቻቸውን በተለይ ደግሞ አብዱልከሪምን ወደ ፊት በመግፋት ከጋዲሳ መብራቴ ጋር እንዲጫወት በማድረግ ከወልቂጤ ተከላካዮች ጀርባ ያለውን ቦታ ለመጠቀም ሲሞክሩ የታዩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በርካታ ኳሶቻቸው ሲበላሽባቸው አይተናል።

በመልሶ ማጥቃት የሚያገኟቸውን ኳሶች ወደ ግብ ለመሞከር ሲጥሩ የነበሩት ወልቂጤ ከተማዎች በመጀሪያዎቹ አስራ አምስት ደቂቃዎች ተከታታይ ሁለት የማዕዘን ምቶችን ያገኙ ሲሆን ሆኖም ግን ሳይጠቀሙባቸው ቀርተዋል።

ፈረሰኞቹ የመጀሪያው አጋማሽ በገፋ ቁጥር በሜዳ ላይ ምን ለማድረግ እያሰቡ እንደሆነ ለማወቅ አዳጋች እየሆነ ሲመጣ ታዝበናል። በተለይም ሶስቱ አማካኞቻቸው ሙሉአለም (ዴኮ) ያብስራ እና ሀይደር ለአጥቂ ክፍሉ የግብ እድል መፍጠር ተስኗቸው የሚያገኟቸው ኳሶች ተደራጅቶ ሲከላለል ለነበረው የወልቂጤ ከተማ አማካኝ ክፍል እና ተከላካይ ክፍል ሲሳይ ሲሆኑ ተመልክተናል።

ወልቂጤዎች ከመጀምሪያዎቹ 15 ደቂቃዎች በውሃላ አላማ ቢስ የነበሩት የጊዮርጊስ ኳሶችን ተደላድሎ በመከላከል እና የተገኙ ኳሶችንም በረጅም ጫላ ተሺታ እና ለአህመድ ሁሴን በማቀብል የጊዮርጊስን የተከላካይ ክፍል ሲያስጨንቁ ታይተዋል።

የፈረሰኞቹ ከወግብ በላይ ያሉ ተጨዋቾች ፍሪያማ የማጥቃት እንቅስቃሴ የመፍጠር ችግር ለቡድኑ ትልቅ ራስ ምታት ሆኖ ሳለ የመሀል ተከላካዮች ሰልሀዲን በርጌቾ እና ምንተስኖት ጥረት ጥሩ አለመሆን ሌላ በሽታ ጭሮባቸው ጨዋታው ከቁጥጥራቸው እንዲወጣ እና ወልቂጤዎች በፈለጉት መልኩ ሲከላከሉ እንዲሁም ሲያጠቁ ለመታዘብ ችለናል።


ደስታ ደሙ በፋሲሉ ጨዋታ ቀይ ካርድ ማየቱን ተከትሎ ወደ ቡድኑ አሰላለፍ መግባት የቻለው የቀኝ መስመር ተከላካዮ አብዱልከሪም መሀመድ የሚገኛቸውን ኳሶች ለማቀበል በሚያደርገው ሂደት በርካታ ኳሶች ሲበላሽበት ተመልክተናል በተጨማሪም በተደጋጋሚ በሚሸፍናቸው የቦታ አጠባበቅ ስህተቶች ለወልቂጤው ጫላ ተሺታ በቂ የመጫወቻ ቦታ ሲከፈትለት ተመልክተናል።

በፈረሰኞቹ የተዘበራረቀ አጨዋወት እና በወልቂጤዎች የተጠና መከላከል እና የመልሶ ማጥቃት ስልት የመጀመሪያው አጋማሽ የተጠናቀቀ ሲሆን ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀሩ በፊት በጉዞ አድዋ ለተሳተፉት ሁለት ሴት የጊዮርጊስ ደጋፊዎች የእውቅና ዝግጅት የተዘጋጀ ሲሆን ተጓዦቹም ከሁለቱም ክለብ ደጋፊዎች ሞቅ ያለ ማበረታቻ አግኝተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ከተጀመረ በሃላ ፈረሰኞቹ ይሄ ነው የሚባል መሻሻል ሳያሳዩ ይሄ ነው በማይባል የማጥቃት ስልት እድላቸውን ሲሞክሩ ተስተውለዋል።

ከጨዋታው መጀመር አንስቶ ረጃጅም ኳሶች ወደፊት ሲያሻግሩ የነበሩት ወልቂጤዎች በ52ተኛው ደቂቃ ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ ጫላ ተሺታ በረጅም የተሻገረለትን ኳስ በጊዮርጊስ ተከላካዮች ስህተት ታግዞ ኳሷን መረብ ላይ በማሳረፍ ቡድኑን አሸናፊ ያደረገችውን ብቸኛ ግብ ማስቆጠር ችሏል።

ከግቧ መቆጠር በውሃላ የተደናገጡት ባለሜዳዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ወደ ግብ በማስቆጠር ወደ ጨዋታው ይመለሳሉ ተብሎ ሲጠበቅ ከመጀመሪያው አጋማሽ የበለጠ ግራ የተጋባ እና በርካታ አላማ ቢስ ኳሶችን ሲቀባበሉ ታይተዋል።

ፈረሰኞቹ በ58ተኛው ደቂቃ አማካኙም ያብስራ በአጥቂው ሰልሀዲን ሰዒድ የቀየሩ ሲሆን ሆኖም ግን የሰልሀዲን ወደ ሜዳ መግባት ጨዋትው ላይ የተለየ ነገር ያላያሳየን ሲሆን ይልቁ ወደ ሃላ ተስቦ በ10 ቁጥር ሚና እንዲጫወት የተደረገው ጌታነህ ከበደ በጨዋታው መክኖ የተሳኩ ኳሶችን እንኳን ማቀበል ሲሳነው ነበር።

ጨዋትው በገፋ ቁጥር በፈረሰኞቹ ላይ የደጋፊው ጫና እየበረከተ የመጣ ሲሆን። ተጫዋቾቹም ኳሱ ላይ ትኩረታቸውን እድርገው ከመጫወት ይልቅ በደጋፊው ጫና ስር በመውደቅ ኳሶችን ሲያበላሹ እና አላማ ቢስ ኳሶችን ሲቀባበሉ ተመልክተናል።

ጨዋታው በወልቂጤ ከተማ 1-0 አሸናፊነት የተጠናቀቀ ሲሆን ከጨዋትው መጠናቀቅም በውሃላ የፈረሰኞቹ ደጋፊዎች በአሰልጣኞቹ እና በተጫዋቾቹ ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ ያሰሙ ሲሆን በአንፃሩ ደግሞ የእንግዳው ቡድን ወልቂጤ ደጋፊዎች በሆይታ እና በጭፈራ ከሜዳ ወጥተዋል።

ውጤቱን ተከትሎም ቅዱስ ጊዮርጊሶች በ28 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው መቐለ ከተማ በግብ ተሽለው 2ተኛ ሆነው በሊጉ ሰንጠረዥ ሲቀመጡ 3 ነጥብ ማግኘት የቻሉት ክትፎዎቹ በ22 ነጥብ 6ተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችለዋል።