የጨዋታ ዘገባ | አዳማ ከተማ ወሳኝ ሶስት ነጥብ በሜዳው አሳክቷል

 

በአስራ አራተኛው ሳምንት የሊጉ መርሀ ግብር ሁለቱን ቡድኖች ሲያገናኝ ከጨዋታው ጅማሮ በፊት ለቀድሞው የአዳማ ከተማ እና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋች ሞገስ ታደሰ የህሊና ፀሎት በማድረግ ጨዋታው ተጀምሯል ::

በአዳማ ከተማዎች ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ በተጀመረው በዚህ ጨዋታ ዳዋ ሆቴሳ ከመሀል ሜዳ የተሻገረለትን ኳስ አክርሮ በመምታት ቢሞክረም የወልዋሎ ግብ ጠባቂ አብድልአዚዝ ኬይታ ሊመልስበት ችሏል ::

ወልዋሎ አዲግራት በቀኝ መስመር ባመዘነው የማጥቃት እንቅስቃሴያቸው የመጀመሪያዎቹን አስራ አምስት ደቂቃዎች በምስግና ወልደ ዮሐንስ ለማጥቃት እና ጫና ለመፍጠር ሲሞክሩ ተስተውለዋል ::

አዳማ ከተማዎች በበኩላቸው በአማኑኤል ጎበና እና በበረከት ደስታ የማጥቃት እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ ሲሞክሩ ተስተውለዋል ::

አዳማዎች በቀኝ መስመር በኩል በአማኑኤል ጎበና ወደ መሀል የተሻማች ኳስ ሙከራዎችን ማድረግ ሲችሉ ከንአን ማርክነህ እንዲሁም ዳዋ ሆቴሳ ከሳጥን ውጪ ሞክረው በተመሳሳይ ሁኔታ በግቡ የግራ አግዳሚ ታካ ወጥታበታለች ::

ተደጋጋሚ ሙከራቸው ፍሬ አፍርቶ በግራ መስመር በኩል ዳዋ ሆቴሳ ለአማኑኤል ጎበና አቀብሎት አማኑኤል አዳማዎችን ቀዳሚ ያደረገች ጎል ከመረብ ላይ ለማሳረፍ ችሏል ::

ወልዋሎዎች ከመጀመሪያዎቹ አስራ አምስት ደቂቃዎች በተለየ መልኩ ለፊት መስመር አጥቂዎቹ ረጃጅም ኳሶችን በመጣል መጫወትን ሲመርጡ ከመሀል ሜዳ በሚላኩ ኳሶች ሲያጠቁ ለሪችሞንድ ኦዶንግ በረጅሙ በተላከለት ኳስ ካሳጥን ውጪ አክርሮ ቢሞክረም የግቡን የላይኛው አግዳሚ ታካ ወጥታበታለች ::

በሁለተኛው አጋማሽ ጥሩ የሚባል የማጥቃት እንቅስቃሴ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ላይ ሲታይ አዳማ ከተማዎች ሳጥን ውስጥ ያገኙትን ኳስ በረከት ደስታ ሞክሮ ግብ ጠባቂው የመለሰው እንዲሁም ዳዋ ሆቴሳ ላይ የተሰራውን ጥፋት ከሳጥን ውጪ ዳዋ ሆቴሳ መቶ በግቡ አግዳሚ ላይ የወጣበት ሙከራዎች ተጠቃሽ ነበሩ ::

ወልዋሎዎች እንደ መጀመሪያው አጋማሽ በረጃጅም ኳሶች መጫወት ሲመርጡ አስደንጋጭ ሙከራዎችን ሲያደርጉ አልተስተዋሉም ::

በሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ መልኩ ወደ ወልዋሎ የግብ ክልል መድረስ የቻሉት አዳማዎች መሪነታቸውን ያጠናከሩበት ጎል ማግኘት ችለዋል ::

የወልዋሎዎችን የተከላካይ ክፍል መዘናጋት የተመለከተው ቡልቻ ሹራ የተሻገረለትን ኳስ ከተከላካዮች ስር ሾልኮ በመውጣት የበረኛውን መውጣት በመመልከት በበረኛው አናት ላይ በማሳለፍ ግሩም ጎል ከመረብ ላይ ማሳረፍ ችሏል ::

ከጎሉ መቆጠር በሃላ የተቀዛቀዘ የጨዋታ እንቅስቃሴ ሲታይ በተለይም በአዳማ በኩል የከንአን ማርክነህ ተቀይሮ መውጣት የቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ ክፍተት ቢፈጥርም አልፎ አልፎም ቢሆን ሙከራዎችን ሲያደርጉ ተስተውሏል ::

አዳማዎች በበረከት ደስታ አስደንጋጭ ሙከራዎችን ማድረግ ቢችሉም በእለቱ ጥሩ ሙከራዎችን ሲያድን በነበረው አብድልአዚዝ ኬይታ አድኖበታል ::

ጨዋታው በአዳማ ከተማ የበላይነት ሲጠናቀቅ ውጤቱን ተከትሎ አዳማ ከተማ በሜዳው ተከታታይ ድል በማስመዝገብ በደረጃ ሰንጠረዡ በአስራ ስምንት ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ በውጤት ቀውስ ውስጥ የሚገኙት ወልዋሎዎች በአስራ አምስት ነጥብ አስራ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ ከወራጅ ቀጠናው በአንድ ነጥብ ብቻ ርቀው ተቀምጠዋል ::

Hatricksport website Editor

Twitter

kidus Yoftahe

Hatricksport website Editor