የጨዋታ ዘገባ | ተጠባቂው ጨዋታ የለምንም ግብ አቻ ተጠናቋል

 

በሁለቱ ደጋፊዎች ደማቅ ህብረ ዝማሬ ታጅቦ የተካሄደው የመቐለ 70 እንደርታና ባህርዳር ከተማ ጨዋታ ብዙ ሙከራዎችን አስተናግዶ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።መቐለ 70 እንደርታዎች ባሳለፍነው ሳምንት ሀድያ ሆሳእናን ካሸነፋት ቀዋሚ ተሰላፊዎች ቢያድግልኝ ኤልያስን በአስናቀ ሞገስ ሲቀይሩ የጣና ሞገዶቹ በተመሳሳይ አንድ ቅያሪ አድርገዋል፤ስንታየሁ መንግስቱ ወጥቶ ማላዊው ማማዱ ሲዲቤ ገብቷል።

ብዙ ሙከራዎችን ያስተናገደው የመጀመርያው አጋማሽ በመጀመርያዎቹ 20 ደቂቃዎች ላይ በሁለቱም ቡድኖች ተመጣጣኝ ፋክክር እና ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች የታዩበት ነበር።በ4-2-3-1 የጨዋታ አቅራረብ ወደ ሜዳ የገቡት መቐለዎች ከሁለቱም መስመሮችና ከዮናስ ገረመው መነሻቸውን ባደረጉ ኳሶች እድሎችን ፈጥረዋል።የዚህ ማሳይ ሚሆነው ዮናስ ገረመው ጨረቃው ላይ ከኦኪኪ ኦፎላቢ ጋር በጥሩ ቅብብል አልፈው ዮናስ በሳጥኑ ውስጥ በግራ በኩል ለነበረው አማኑኤል ገብረሚካኤል አቀብሎት የተመታው ኳስ ሀሪሰን ሄሱ በቀላሉ ይዞታል።መሀል ላይ በተሰለፋት ዳንኤል ሀይሉ፣ፍፁም አለሙ እና ሳምሶን ጥላሁን ላይ መሰረት ያደረገው የባህርዳር የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ በመጀመርያ 20 ደቂቃዎች ላይ የተሻለ የነበረ ቢሆንም ጨዋታው እየገፋ ሲሄድ መቀዛቀዝ ታይቶበታል።የባህርዳሮች የመጀመርያው አጋማሽ ጠንካራ ሙከራ አምበሉ
ዳንኤል ሀይሉ በግምት ከ30 ሜትር የመታው ጠንካራ ኳስ የግቡ አግዳሚ ብረት መልሶበታል።

የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስደው መጫወታቸውን የቀጠሉት ምዐም አናብስቶቹ በ10ኛው ደቂቃ ላይ በአማኑኤል ገብረሚካኤል በኩል ያገኙትን እድል ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። ኦኪኪ ኦፎላቢ መሬት ለመሬት ያሾለከው ኳስ አማኑኤልን ከበረኛው ጋር ቢያገናኝም ሀሪሰን ሄሱ አድኖበታል።ከዚች ሙከራ ጥቂት ደቂቃዎች በኃላ ከመሀል ሜዳ በረጅሙ የተላከው ኳስ አሁንም አማኑኤል ገብረሚካኤል ከተከላካዮች መሀል ሾልኮ ቢያገኘውም ከበረኛው አናት ለማሳለፍ ሲሞክር ኳሱ ከግቡ አናት ወደ ላይ ወጥቷል።ማጥቃተቸውን የቀጠሉት መቐለዎች መስመር መናሻቸውን ባደረጉ ኳሶች አሁንም እድሎችን ቢፈጥሩም ጨዋታው ላይ ጥሩ የነበረው ግብ ጠባቂው ሀሪሰን ሄሱ ሊያድንባቸው ችልዋል።የዚህ እንቅስቃሴ ማሳያ ሚሆኑት 21ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታው ላይ ወደ መስመርና ወደ መሀል እየወጣ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ኦኪኪ ኦፎላቢ ከቀኝ መስመር ያሻማው ኳስ አልሃሰን ካሉሻ በግምባሩ የመታው ሀሪሰን የያዘበት እንዲሁም ከስድስት ደቂቃ በኃላ ኦኪኪ ከሳጥኑ ውጭ በግራ እግሩ የመታውና አሁንም ሀሪሰን የመለሰባቸው ተጠቃሽ ናቸው። በተጨማሪ ከግራ መስመር አስናቀ ያሻማው ኳስ ኦኪኪ በግምባሩ ቢገጨውም ሀሪሰተን መልሶበታል፤በዚህም መሠረት የመጀመርያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ችሏል።

የመቐለዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ እንዲሁም የባህርዳሮች አልፎ አልፎ ሚታይ ፈጣን መልሶ ማጥቃት የታየበት ሁለተኛው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን አስተናግዷል።ሥዩም ተስፋዬ ከቀኝ መስመር ወደ ግራ መስመር የበተነው ረጅም ኳስ አማኑኤል ተቆጣጥሮ ወደ ውስጥ መሬት ለመሬት አሻግሮት
ካሉሻ አልሃሰን የመታው ኳስ ከግቡ አናት ወደ ላይ ወጥቷል።

በቀጥተኛ ኳሶች እድሎችን ለመፍጠር መሞከራቸውን የቀጠሉት የገብረመድህን ኃይሌ ተጨዋቾች ተከላካዩ ተስፋዬ በቀለ በረጅሙ ያሻገረው ኳስ ሳጥን ውስጥ የነበረው ኦኪኪ በሚገባ ተቆጣጥሮ ለያሬድ ከበደ አቀብሎት አስቆጠረው ሲባል ሚኪያስ መኮነን ተደርቦ መልሶበታል።

ከመጀመርያው አጋማሽ በተሻለ መልኩ በመልሶ ማጥቃት እድሎችን ለመፍጠር የሞከሩት ባህርዳሮች ከፍፁም አለሙ መነሻውን አድርጎ ግርማ ዲሳሳ ላይ የደረሰው ኳስ ፈጣኑ የመስመር አጥቂ ግርማ በቀጥታ ቢመታውም ከግቡ አናት ለትንሽ ወጥቷል።ከባህርዳሮች ሙከራ ትንሽ ደቂቃዎች በኃላ ከግራ መስመር አማኑኤል ያሻገረው ኳስ ኦኪኪ በግምባሩ ገጭቶት የሀሪሰን ሄሱ እጅ ጨርፎ የግቡ አግዳሚ ገጭቶ መልሶበታል።

መቐለዎች ግብ ለማግባት በሚወጡበት ጊዜ ሚገኘውን ክፍተት ለመጠቀም ሲሞክሩ የታዩት ባህርዳሮች ፍፁም አለሙ በግል ጥረቱ በግምት ከ20 ሜትር የመታው ኳስ ፊሊፕ ኦቮኖ መልሶበታል።

የጨዋታው መገባደጃ መቃረቡን አይተው ግብ ለማስቆጠር ችኮላ ውስጥ የገቡት መቐለ 70 እንደርታዎች የጨዋታው መጨረሻ ደቂቃዎች ላይ በኦኪኪ ኦፎላቢ እና አማኑኤል ገብረሚካኤል አማካኝነት ያደረጉዋቸው ሙከራዎች ሳይሳኩላቸው ቀርተው ጨዋታው ያለ ግብ አቻ ሊጠናቀቅ ችሏል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የመቐለ 70 እንደርታና ባህርዳር ከተማ ደጋፊዎች አንድ ላይ ሆነው በጋራ ህብረዜማ አንድነታቸውን የገለፁበት መንገድ ሊበረታታ ሚገባው እና በሌሎች ክለቦችም ቀጣይነት ይኑረው ለማለት እንፈልጋለን።

Hatricksport website writer

Twitter

ዳዊት ብርሀነ

Hatricksport website writer