የጨዋታ ዘገባ |በርካታ ጎል በተቆጠሩበት ጨዋታ ሲዳማ ቡና በሀብታሙ ገዛኸኝ ሀትሪክ ታግዞ ወላይታ ድቻን አሸነፈ

 

የኢትዮጲያ ፕሪምየር ሊግ ከሁለት ሳምንት እረፍት በኋላ የሁለተኛው ዙር ጨዋታዎች ትላንት ጅማሮውን አድርጎ ዛሬም ቀጥሎ ሀዋሳ ላይ ሲዳማ ቡና ወላይታ ድቻን ባስተናገደበት ጨዋታ 5-3 በሆነ ውጤት አሸንፎ ወጥቷል።

በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ የተደረገው ይህ ጨዋታ የሊጉን ፈጣን ጎል አስተናግዷል። 39ኛው ሴኮንድ ዳዊት ተፈራ ለአዲስ ግደይ ከመሀል ሜዳ ያሻገረለት ኳስ የወላይታ ድቻ ተከላካዮችን መዘናጋት ተከመልክቶ በግንባሩ በመግጨት ግብ በማድረግ ቡድኑን መሪ አድርጓል።
ከግቡ መቆጠር በኳላ ሲዳማ ቡናዎች ይበልጥ ጫና ፈጥረው ተጨማሪ ጎል ለማግኘት ሲጥሩ ተስተውሏል።ለዚህም ማሳያ ይገዙ ቦጋለ ከመሀልሜዳ በቀጥታ ወደ ጎል የሚመታቸው በግብ ጠባቂው መክብብ ደገፉ ጥረት የመከኑ እንዲሁም አዲስ ግደይ ከዳዊ ተፈራ ጋር ሳጥን ውስጥ እርስ በርስ ተቀባብለው ዳዊት ወደ ግቡ የሞከራት ኳስ ለባለሜዳዎቹ ተጨማሪ ጎል የሚሆኑ አስቆጪ ሙከራ ነበሩ።

በባለ ሜዳዎቹ ብልጫ የተወሰደባቸው ወላይታ ዲቻዎች በበኩላቸው በባዬ ገዛኸኝ ሙከራ አቻ መሆን የሚችሉበት አጋጣሚ በግብ ጠባቂው መሳይ አያኖ ቢያከሽፍም በተመሳይ እንድሪስ ሰይድ የመሳይን መዘነጋት ተመልክቶ ከፍ አድርጎ ወደ ጎል በመምታት ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል።
በዛሬው ጨዋታ ጥሩ የነበረው ዳዊት ተፈራ ሳጥን ውስጥ ያገኛትን ኳስ በግሩም ሁኔታ ወደ ወደ ግብነት በመቀየር ባለሜዳዎቹን በድጋሚ መሪ ማድረግ ችሎ በሲዳማ ቡና 2-1 ለእረፍት ወጥተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ባለ ሜዳዎቹ በፍፁም የጨዋታ ብልጫ በመጫወት አዲስ ግደይ ላይ በተሰራ ጥፋት በግራ መስመር በግምት 29 ሜትር አካባቢ በተሰጠ ቅጣት ምት አበባየው ዮሀንስ ወደ ሳጥኑ አሻምቶ ሀብታሙ ገዛኸኝ በግንባሩ በመግጨት ወደ ግብ በመቀየር መሪነቱን ወደ 3-1 ከፍ አድርጎታል።ከግቧ መቆጠር በኳላ የሲዳማ ቡና ተጫዋቾች ይበልጥ ተጭነው በመጫወት የድቻ ተከላካዩችን ሲያስጨንቁ ታይተዋል።ድቻዎች በቀኝ መስመር በኩል ከፀጋዬ አበራ በሚነሱ ኳሶች ወደ ሲዳማ የግብ ክልል ቢቀርቡም ግብ ለማስቆጠር ተቸግረዋል።


ጥሩ ሲንቀሳቀስ ከነበረው ከዳዊት ፀጋዬ የተላከለትን ኳስ ሀብታሙ ገዛኸኝ 66′ ደቂቃ ላይ ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ አራተኛ ግብ በማስቆጠር ባለሜዳዎቹ ወደ 4-1 ውጤት መሪ ሲሆኑ በዛሬው ጨዋታ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረም እንድሪስ ሰይድ 76 ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጭ ያገኘውን ኳስ በቀጥታ ወደ ግቡ በመምታት መሳይ አያኖ ሳይቋቋማት ቀርቶ ግብ በማድረግ ውጤቱን በማጥበብ 4-2 እንዲሆን አድርጓል። ጨዋታው ቀጥሎ ይበልጥ በግቧ የተነቃቁ የመሰሉት ድቻዎች በእዩብ አለማየው ተቀይሮ የገባው ፀጋዬ ብርሀኑ በቀኝ መስመር በኩል ወደ ጎል በመቅረብ አመቻችቶ በማቀበል የሲዳማ ተከላካዮችን ሲያስጨንቅ ነበር።በተለይ እራሱ ከመስመር ኳሷን እየገፋ ወደ ጎቡ አካባቢ ደርሶ ግብ ጠባቂው ጋር ቢገናኝም ሳይጠቀምበት የቀረው ለወላይታ ድቻ ጎል የሚሆን አስቆጪ ሙከራ ነበረች።

ጨዋታው በሁለቱም በኩል ተመጣጣኝ ሆኖ ቢቀጥልም ጎል ለማስቆጠር ሲዳማዎች የታደሉ ነበሩ። 83 ደቂቃ ላይ ሀብታሙ ገዛኸኝ ጎል በማስቆጠር ሲዳዎች ወደ 5-2 ውጤት ከፍ አድርጎ ሀትሪክ ከሰሩ ተጫዋቾች ተርታ ስሙን ማስፈር ችሏል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ የባከ ሰአት ሲቀረው የሲዳማ ፍፁም ቅጣት ምት ውስጥ ጥፋት በመስራታቸው ሀብታሙ ገዛኸኝ ፍፁም ቅጣት ምቱን ወደ ግብነት በመቀየር የጦና ንቦች የጎል እዳ በመቀነስ ጨዋታው በሲዳማ ቡና 5-3 ውጤት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎ ሲዳማ ቡና ከመሪው ሁለት ነጥብ ብቻ ዝቅ ብሎ በ27 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።