የጨዋታ ዘገባ | ቅዱስ ጊዮርጊስ ተከታታይ ሽንፈት አስተናግዷል

 

ያለ አሰልጣኝቸው ሰርጂዮ ዚቪጅኖቭ እየተመሩ ወደ ሜዳ የገቡት ፈረሰኞቹ የመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች ላይ በተደጋጋሚ ወደ ሰበታ የግብ ክልል ሲደርሱ ተስተውለዋል። በመጀመሪዎቹ ደቂቃ ላይ አቤል ያለው የሰበታ የተከላካይ ክፍል የሰራውን ስህተት አግኝቶ ያባከነው ሙከራ ለፈርሰኞቹ የምታስቆጭ አጋጣሚ ነበረች። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ከወትሮው ለየት ባለ ሚና በጨዋታው የተመለከትነው የመሀል ተከላካዩ ፍሪምፖንግ በግራ ተመላላሽ ሆኖ ሲጫወት ታይቷል።

የፈረሰኞቹ የማጥቃት እንቅስቃሴ በጋዲሳ መብራቴ የቀኝ መስመር ላይ ተገድቦ ሲታይ ለቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴም ምክንያት ሲሆን ተስተውለዋል። በአንድ አጋጣሚም በግራ በኩል የግል ብቃቱን ተጠቅሞ ይዞ ገብቶ ሞክሮ ግብ ጠባቂው ፋሲል ገ/ሚካኤል ያዳነበት ሙከራ የምታስቆጭ አጋጣሚ ነበረች።

በሰበታ ከተማ በኩል ኳስን ተቆጣጥረው መጫወት ቢያስቡም ያን ያህል አመርቂ ሆኖ አልታየም። አልፎ አልፎ ናትናኤል በግራ መስመር ከሚያደርጋቸው የማጥቃት እንቅስቃሴዎች ውጪ ጫና ሲያደርጉ አልተስተዋለም። ፈረሰኞቹ በተደጋጋሚ የሰበታ የግብ ክልል ውስጥ መድረስ ሲችሉ ሀይደር ከማእዘን ምት አግኝቶ የግቡን አግዳሚ ታካ የወጣችበት እንዲሁም ሳላህዲን ሰኢድ ሳጥን ውስጥ አግኝቶ ወደ ግብ ሳይቀየሩ የቀሩት አጋጣሚዎች የሚጠቀሱ ናቸው።

የማጥቅት እንቅስቃሴያቸው በመጀመሪያው አጋማሽ በጋዲሳ መብራቴ ላይ የተመሰረተው ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከርቀት ሞክሮ በግቡ ላይኛው አግዳሚ የወጣችበት ሙከራ ለግብ የቀረበች ነበረች። ሰበታ ከተማዎች በመሀል ክፍሉ ላይ ብልጫ በመውሰድ ለመጫወት ሲያስቡ ዳዊት እስጢፋኖስ በመሀል ያሾለከለትን ኳስ አስቻለው ግርማ ወደ ግብነት ቀይሮት ሰበታ ከተማን መሪ ያደረገች ጎል ማስቆጠር ችሏል። ከጎሉ መቆጠር በኋላ ተጭነው የተጫወቱት ጊዮርጊሶች ሳላህዲን ሰኢድ ለብቻው ተገናኝቶ ግብ ጠባቂው ፋሲል ቀድሞ የያዘበት ኳስ ለግብ የቀረብች ነበረች።

በሁለተኛው አጋማሽ ተጭነው ቢጫወቱም የተሳክ ሙከራ ማድረግ ያልቻሉት ፈረሰኞቹ በሰበታ በመልሶ ማጥቃት ሲቸገሩ ታይተዋል። የጨዋታው ክስተት በነበረው ሁኔታ ሳላህዲን ሰኢድ ካዳኛው ጋር አለመግባባት ውስጥ መግባቱን ተከትሎ በሁለተኛ ቢጫ በቀይ ካርድ ሲወጣ የጨዋታው እንቅስቃሴም ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ፈጥሮ ታይቷል።

ከቀይ ካርዱ በኋላ ጫና ውስጥ ገብተው የታዩት ፈረሰኞቹ ጌታነህ ከበደ ከሳጥን ውጪ ቢሞክርም የሰበታ ከተማው ግብ ጠባቂ ፋሲል ሲመልሰው ሀይደር አግኝቶት ቢሞክረውም ግብ ጠባቂው ይዞበታል። ሰበታዎች የቁጥር ብልጫውን ለመጠቀም የሞከሩ ሲሆን በመልሶ ማጥቃት ሙከራዎች ሲያደርጉ ሲስተዋሉ ወደ ግብነት ሳይቀይሩት ቀርተዋል።

ውጤቱንም ተከትሎ ፈረሰኞቹ የሊጉን መሪነት የሚይዙበትን እድል ሳይጠቀሙበት ሲቀሩ ባለ ድል መሆን የቻሉት ሰበታ ከተማዎች በ22ነጥቦች 10ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችለዋል።

Hatricksport website Editor

Twitter

kidus Yoftahe

Hatricksport website Editor