የጨዋታ ዘገባ| መዓም አናብስት ሀይቆችን ረምርመው ወደ አሸናፊነት ተመልሰዋል

 

መቐለ 70 እንደርታ በ14ኛ ሳምንት የፕሪምየር ሊግ ጅማሮ ጨዋታ ሀይቆችን በሰፊ የግብ ልዩነት 5-1 በመርታት ወደ አሸናፊነት መንገድ ተመልሷል።

አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ በፋሲል ከነማ ሽንፈት ካስተናገደው ስብስብ ዳንኤል ደምሴን በሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ፣ሳሙኤል ሳሊሶን በያሬድ ከበደ ሲቀይሩ ሀዋሳዎች በበኩላቸው ጅማ አባጅፋር ላይ ድል ከተቀዳጀው የመጀመርያ ተሰላፊዎች ዳንኤል ደርቤ፣ኄኖክ ድልቢ፣ዘላለም ኢሳያስ፣ኄኖክ አየለ ወጥተው ወንድማገኝ ማዕርግ፣ብርሀኑ በቀለ፣የተሻ ግዛው፣ፀጋኣብ ዮውሀንስ አስገብተዋል።

ባለሜዳዎቹ ተሽለው በታዩበት የመጀመርያ አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች የታዩበት ነበር።ጨዋታው እንደተጀመረ ጫና መፍጠራቸውን የቀጠሉት መቐለ 70 እንደርታዎች በ5ኛው ደቂቃ በኦኪኪ ኦፎላቢ አማካኝነት መሪ መሆን ችለዋል፤ከማእዘን ምት ተሻምቶ በሀዋሳ ተከላካዮች የተመለሰውን ኳስ አሚን ነስሩ ወደ ውስጥ መልሶት ሥዩም ተስፋዬ ጋር ደርሶ የቀኝ መስመር ተከላካዬ ያሾለከውን ኳስ ኦኪኪ ኦፎላቢ በጥሩ አጨራረስ አስቆጥሮታል።

ከግቡ በኃላም ቀኝ መስመር ላይ ትኩረት አድርገው ማጥቃታቸውን የቀጠሉት ምዐም አናብስቶቹ ከቀኝ መስመር ኤፍሬም አሻሞ ከኦኪኪ ጋር በጥሩ ቅብብል አልፈው ኤፍሬም ያሻማውን ኳስ ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ ቢመታውም በሀዋሳ ተከላካይ ተጨርፎ ወደ ውጭ ወጥቷል።ከመሀል ሜዳ ተነስተው ወደ መስመር በሚወጡ ኳሶች እድሎችን ለመፍጠር የሞከሩት መቐለዎች የእንቅስቃሴያቸውን ውጤት በሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ አማካኝነት አግኝተዋል።ከቀኝ መስመር ሥዩም ተስፋዬ ያሻማውን ኳስ ሳጥን ውስጥ በግራ በኩል የነበረው ሙሉጌታ በሚገባ ተቆጣጥሮ የሀዋሳዎች መርበብ ላይ አሳርፎታል።

ከሁለቱ ግቦች በኃላ በመጠኑ ተሽለው የታዩት ሀይቆቹ በአለልኝ አዘነ እና ብርሀኑ በቀለ አማካኝነት እድሎችን መፍጠር ችለዋል።በተቀራራቢ ደቂቃዎች አለልኝ አዘነ ከርቀት እና በግምባሩ በመግጨት ያደረጋቸው ሙከራዎች በፊሊፕ ኦቮኖ ጥረት ሊመለሱ ችለዋል።በተጨማሪ
አለልኝ አዘነ ከመሀል ያሾለከው ኳስ ብርሀኑ በቀለን ከኦቮኖ ጋር በሳጥኑ በቀኝ በኩል ቢያገናኝም ቀኝ መስመር ላይ የተሰለፈው ብርሀኑ በቀለ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።ሀዋሳ ከተማዎች የተሻለ መነቃቃት ባሳዩበት ሰዐት አለልኝ አዘነ ኤፍሬም አሻሞ ላይ በሰራው ጥፋት የዕለቱ ዳኛ ብሩክ የማነብርሀን የማስጠንቀቂያ ካርድ ከሰጡት በኃላ ከዳኛው ጋር በገባው ሰጣ ገባ በሁለተኛ ቢጫ ከሜዳ ሊሰናበት ችሏል።

ከቀይ ካርዱ በኃላ ሙሉ የጨዋታውን ብልጫ የወሰዱት መቐለዎች እንደነበራቸው የኳስ ቁጥጥር በላይነት ብዙ የግብ እድሎችን መፍጠር ሳይችሉ የመጀመርያው አጋማሽ በመዓም አናብስት 2-0 መሪነት ተጠናቋል።

ሁለተኛው አጋማሽ በመቐለ 70 እንደርታዎች ብልጫ በ4 ግቦች ታጅቦ ተካሂዷል።አክሊሉ ተፈራና ተባረክ ኢፋሞን ቀይረው ያስገቡት አዲሴ ካሳ በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመርያ 10 ደቂቃዎች ላይ ጥሩ መንቀሳቀስ ችለዋል።የዚህ ማሳያም
ጨዋታው ላይ በቸኛ አጥቂነት የተሰለፈው ብሩክ በየነ ከርቀት በግራ እግሩ የመታው ኳስ ፊሊፕ ኦቮኖ አድኖበታል።

ጨዋታው እየገፋ ሲሄድ ጨዋታውን መቆጣጠር የጀመሩት መቐለዎች በተደጋጋሚ የሀዋሳ ፍፁም ቅጣት ምት ሳጥንን መጎብኘት ችለዋል።በ61ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር ከኤፍሬም ጋር በጥሩ ቅብብል ወደ ውስጥ ሰብሮ የገባው ኦኪኪ ከርቀት የመታው ኳስ ተከላካዮች ተደርበውት መልሶ ያገኘውን ኳስ ከርቀት በሚገርም ሁኔታ አስቆጥሮ የመቐለዎችን መሪነት ወደ 3 ከፍ አድርጎታል።

ከሦስተኛው ግብ 3 ደቂቃዎች በኃላ የጨዋታው ኮከብ ግዙፋ ናይጀርያዊው አጥቂ ኦኪኪ ኦፎላቢ ጨዋታው ላይ ሀትሪክ የሰራበትን ግብ ማስቆጠር ችሏል።የሀዋሳዎች ሳጥን ውስጥ በግራ በኩል አማኑኤል ገብረሚካኤል ከኦኪኪ የተቀበለውን ኳስ ተጠቅሞ ወደ ግብ ሲሞክር ቢሊንጋ መልሶበት በድጋሚ አማኑኤል አግኝቶት ለኦኪኪ ኦፎላቢ ሲያቀብለው ናይጀርያዊው አጥቂ በግራ እግሩ የሀይቆቹ መረብ ላይ አሳርፎታል።

ክፍት በነበረውና ሁለቱም ቡድኖች እየተመላለሱ ባጠቁበት ጨዋታ ሀዋሳዎች ከባዶ ሽንፈት የገላገለቻቸውን ግብ በፍፁም ቅጣት ምት ማስቆጠር ችለዋል።ቢያድግልኝ ኤልያስ በፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ውስጥ ኳስን በእጁ መንካቱን ተከትሎ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ብሩክ በየነ ማስቆጠር ችሏል።ጨዋታው ሊጠናቀቅ የዕለቱ ዳኛ ፊሽካ በሚጠበቅበት ወቅት ቢያድግልኝ ኤልያስ ስታድየም የተገኘውን ደጋፊ ያስገረመ ያልተጠበቀ ግብ አስቆጠረ።ከመሀል ሜዳ ኳስን ለማራቅ በሀይል አክርሮ የመታው ኳስ በቀጥታ የሀዋሳ መርበብ ላይ አርፎ የመቐለ ግብን ወደ 5 ከፍ አድርጎ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ችሏል።

ውጤቱን ተከትሎ መቐለ 70 እንደርታዎች ነጥባቸውን 25 በማድረስ ነገ ጨዋታቸውን ከሚያደርጉት ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ማጥበብ ችለዋል።

Hatricksport website writer

Twitter

ዳዊት ብርሀነ

Hatricksport website writer