የጨዋታ ዘገባ | መቐለ 70 እንደርታ ከሜዳው ውጭ በጠባብ ውጤት በማሸነፍ ጣፋጭ ድል አስመዝግቧል።

 

በ16ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 6ጨዋታዎች ዛሬ (እሁድ) ሲደረጉ ወደ ሀድያ ያቀናው መቐለ 70 እ. በኦኪኪ አፎላቢ ብቸኛ ግብ 3ነጥብ ይዞ ተመልሷል።

በጨዋታው ባለሜዳዎቹ ሀዲያ ሆሳዕናዎች በጨዋታ እንቅስቃሴ የተሻሉ የነበሩ ቢሆንም ወደ ግብ በመድረስ ረገድ ግን መቐለ 70 እንደርታዎች የተሻሉ ነበሩ።

በመስመር ጨዋታ ላይ ትኩረት አድርገው ሲጫወቱ የተስተዋሉት ሀዲያ ሆሳዕናዎች 22ኛው ደቂቃ ላይ ቢስማርክ ኦፖንግ አክርሮ ወደ ግብ የመታትን ኳስ የመቐለ 70 እ. ግብ ጠባቂ ፊልፖ ኦቮኖ በቀላሉ ይዟታል። ከዚህች ሙከራ በኋላም መቐለ 70 እ. ጫና ፈጥረው ለመጫወት ጥረት ሲያደርጉ ተስተውለዋል። 36ኛው ደቂቃ ላይ የሀድያ ሆሳዕናው ቢስማርክ ኦፖንግ የመታው ኳስ የግቡን አግዳሚ ለትሞ የተመለሰበት በሀድያ በኩል እጅግ የሚያስቆጭ ነበር። ከዚህ በኋላም ይህ ነው የሚባል የረባ ሙከራ ሳይስተዋልበት ግብም ሳያስተናግድ የመጀመሪያው አጋማሽ ያለግብ 0-0 ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ባለሜዳዎቹ ጎል ለማስቆጠር ተጭነው ሲጫወቱ በቢስማርክ አፒያ አማካኝነት ተደጋጋሚ የጎል ሙከራዎችን ማድረግ ቢችሉም ወደግብነት መቀየር ግን አልቻሉም። 59ኛው ደቂቃ ላይ ከመስመር በኩል የተያሻገረለትን ኳስ የመቐለ 70 እንደርታው አጥቂ ኦኪኪ አፎላቢ በማስቆጠር እንግዳው ቡድንን መሪ ማድረግ ችሏል። ከግቧ መቆጠር በኋላም መቐለ 70 እንደርታዎች በመልሶ ማጥቃት ግብ ለማግባት ጥረት ያደረጉ ሲሆን አማኑኤል ገ/ሚካኤል እና አልሀሰን ካሉሻ ያደረጓቸው እና ያመከኗቸው ሙከራዎች የሚያስቆጩ ነበሩ።

ባለሜዳዎቹ ሀዲያ ሆሳዕናዎች አቻ ለመሆን መቐለ 70 እንደርታ ደግሞ ውጤቱን አስጠብቆ ከተቻለ ተጨማሪ ግብ አስቆጥሮ ጨዋታውን ለመግደል ጥንቃቄ የተሞላበት ጨዋታ ሲጫወቱ ተስተውሏል። በጨዋታው መጠናቀቂያ ደቂቃዎች የሀድያ ሆሳዕናው ይሁን እንደሻው ያሻማውን የቅጣት ምት አዩብ በቃታ በግንባሩ ገጭቶ ጎል ቢያስቆጥርም ከጨዋታ ውጪ ተብላ ተሽራለች። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳያስተናግድ በመቐለ 70 እ. 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱንም ተከትሎ ሀዲያ ሆሳዕና በ13ነጥቦች የሊጉን ግርጌ እንደያዙ ሲቀጥሉ ባለድል የሆኑት መቐለ 70 እንደርታዎች ነጥባቸውን ወደ 28 ከፍ በማድረግ ከመሪው ፋሲል ከነማ በ1ነጥብ ብቻ ዝቅ ብለው 3ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችለዋል።

📷 © hossana sport page

hatricksport team

Hatricksport team

Facebook

hatricksport team

Hatricksport team