የጨዋታ ቅድመ-ዕይታ | ፋሲል ከነማ ከ አዳማ ከተማ

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ዙር ነገ (ቅዳሜ) እና ከነገ በስትያ (እሁድ) በሚደረጉ ጨዋታዎች የሚጀምር ሲሆን ቅዳሜ ሁለት እንዲሁም እሁድ ደግሞ ስምንት ጨዋታዎች በአዲስ አበባ እና በተለያዩ የክልል ከተሞች የሚካሄዱ ይሆናል። ከነዚህ ስምንት ጨዋታዎች መካከል ነገ የሚደረገው የፋሲል ከነማ እና የአዳማ ከተማ ጨዋታ በጉጉት የሚጠበቅ ነው።

በአሰልጣኝ ስዩም ከበደ የሚሰለጥኑት አፄዎቹ በሜዳቸው ለተጋጣሚ ከባድ ፈተና በመሆን አይበገሬነታቸውን ማሳየት ችለዋል። ለዚህም በሜዳቸው ምንም ሽንፈት አለማስተናገዳቸው እና የተቆጠረባቸውም ግብ 3ብቻ መሆኑ ግልፅ ማሳያ ነው። ይህ የሜዳ ላይ ሀያልነታቸው ከሜዳው ውጪ በጣም ለሚቸገረው አዳማ ከተማ ፈታኝ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

የዘንድሮው ፋሲል ከነማ ከሞላ ጎደል የተሟላ ቡድን ነው ማለት ያስደፍራል። በአንደኛው ዙር ከተካሄዱት 15 ጨዋታዎች ውስጥ በ8ጨዋታዎች መረቡን ያላስደፈረው ግብ ጠባቂው ሚካኤል ሳማኪ በተከላካይ ረገድ ደግሞ የሰዒድ ሀሰን፣ ያሬድ ባዬ፣ ከድር ኩሊባሊ እና አምሳሉ ጥላሁን የፈጠሩት ጥምረት ቡድኑ ብዙ ግቦችን እንዳያስተናግድ ከፍተኛ አስተዋጽኦን አበርክቷል። በማጥቃቱ ረገድ ሱራፌል ዳኛቸው ለሙጂብ ቃሲም እና ለሌሎቹ አጥቂዎች ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን በማድረሱ ረገድ ከፍተኛ ሚናን እየተወጣ ነው። በ15ጨዋታዎች 14ግቦችን ማስቆጠር የቻለው የዚህ ውድድር አመት ክስተት የሆነው ሙጂብ ቃሲም ያገኘውን እድል በአግባቡ መጠቀሙ አፄዎቹን ከመሪዎቹ ጎራ ሊያሰልፋቸው ችሏል። ሆኖም ግን ይህንን ድንቅ ብቃታቸውን ከሜዳቸው ውጪ መድገም ባለመቻላቸው ሊጉን በሰፊ ርቀት መምራት የሚችሉበትን እድል አምክነዋል። ፋሲል ከነማ ከስፖርታዊ ጨዋነት ጋር በተያያዘ 16ኛ ሳምንት ጨዋታውን ባህርዳር አለምአቀፍ ስታዲየም ላይ የሚያደርግ ይሆናል።

በአዳማ ከተማ በኩል የመጀመሪያ ዙሩን በበርካታ ውዝግቦች ያሳለፉ ሲሆን በተለይ ደግሞ የተጫዋቾች ደሞዝ ከመክፈል ጋር በተያያዘ ወጥ የሆነ አቋም ማሳየት እንዳይችሉ አስገድዷቸዋል። አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የሚመሩት አዳማ ከተማ ከሜዳቸው ውጪ እጅግ የሚቸገር ቡድን ሲሆኑ ካደረጓቸው 8የሜዳ ውጪ ጨዋታዎች በአንዱም ድል አለማድረጋቸው ከአፄዎቹ በሜዳቸው ካላቸው ጥንካሬ ጋር ተዳምሮ ለአዳማዎች ከባድ ፈተና ይሆንባቸዋል ተብሎ ይጠብቃል።

በዘንድሮው የአዳማ ቡድን ውስጥ የከነዓን ማርክነህ እና የአጥቂው ዳዋ ሁቴሳ ድንቅ ብቃት ላይ መገኘት ቡድኑ ከወራጅ ቀጠና እንዲርቅ ጠቅሞታል።

በነገው ጨዋታ ፋሲል ከነማ ድል የሚቀናቸው ከሆነ ቅዱስ ጊዮርጊስ እሁድ እስኪጫወት ድረስ የሊጉ አናት ላይ መቀመጥ ሲያስችለው አዳማ ከተማ በአንፃሩ ድል የሚቀናቸው ከሆነ የሌሎችን ቡድኖች ውጤት ጠብቆ እስከ 6ኛ ደረጃ ድረስ ከፍ ማለት ይችላሉ። ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያው ዙር የመጀመሪያ ሳምንት አዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ላይ ተገናኝተው ጨዋታቸውን ያለግብ 0-0 ማጠናቀቃቸው ይታወሳል።

ፌደራል አርቢትር ብርሃኑ መኩሪያ በሚመሩት እና ነገ 9:00 ሲል ባህርዳር አለም አቀፍ ስታዲየም ላይ በሚካሄደው ጨዋታ ላይ በአፄዎቹ በኩል በ14ኛ ሳምንት ጨዋታ በተመለከተው ቀይ ካርድ የ3ጨዋታዎች ቅጣት ተላልፎበት የነበረው እና አንድ ጨዋታ ተቀንሶለት የነበረው ሽመክት ጉግሳ በቅጣት ሁለተኛ ጨዋታ ሲያመልጠው በአዳማ ከተማ በኩል ደግሞ ግብ ጠባቂው ደረጀ አለሙ በቤተሰብ ሀዘን ምክንያት ከቡድኑ ጋር ወደ ባህርዳር ባለመጓዙ የነገው ጨዋታ የሚያመልጠው ይሆናል።

Muluken Tesfaye

Editor at Hatricksport website

Facebook

Muluken Tesfaye

Editor at Hatricksport website