የጨዋታ ቅድመ-ዕይታ | ወልዋሎ አ.ዩ. ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

 

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በዚህ ሳምንት 13ሳምንት ጨዋታውን ያከናውናል። በዚህ ሳምንት ከሚካሄዱት 8ጨዋታዎች መካከል በትግራይ ስታዲየም ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲ ቅዱስ ጊዮርጊስን የሚያስተናግድበት ጨዋታ በጉጉት ይጠበቃል።

ጨዋታ: ወልዋሎ አ.ዩ. ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ
የጨዋታ ቀን: እሁድ የካቲት 01/2012
የጨዋታ ሰዓት: 9:00
የጨዋታ አርቢትር: ፌደራል አርቢትር ብርሃኑ መኩሪያ
የጨዋታ ቦታ: ትግራይ ስታድየም

በሜዳው ጠንካራነቱን እያሳየ የሚገኘው ወልዋሎ አ.ዩ. ከአዲስ አበባ ውጪ ሲጫወት እጅግ ደካማ የሆነውን ቅዱስ ጊዮርጊስን ያስተናግዳል። አዲግራት የሚገኘውን የመጫወቻ ሜዳው እድሳት ተደርጎለት የተጠናቀቀ ቢሆንም በፌደሬሽኑ ውሳኔ መሰረት የ13ኛውን ሳምንት ጨዋታውን በትግራይ ስታዲየም ሊያደርግ ይገደዳል። ወልዋሎ ለፌዴሬሽኑ ቅሬታ ያስገባ ቢሆንም ፌደሬሽኑ ዛሬ በላከው ደብዳቤ የሊጉ አብይ ኮሚቴና የውድድርና ስነስርዓት ኮሚቴ ጉዳዩን በቀጣይ ለሚደረገው መደበኛ ስብሰባ እንደሚቀርብ እና የሜዳ ለውጥ ማድረግ እንደሚቻል ጠቅሷል።

ወልዋሎ አ.ዩ. ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች ከሜዳው ውጪ አድርጎ በሲዳማ ቡና 5-0 እንዲሁም በፋሲል ከተማ 1-0 ሽንፈት አስተናግዶ የነገውን ጨዋታ ለማ ድረግ ይዘጋጃል። የአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ቡድን በሊጉ ጅማሬ ላይ ድንቅ ውጤት ማስመዝገብ ችሎ የነበረ ቢሆንም ከጊዜ ወደ ጊዜ ወጥ አቋም ማሳየት እየተሳነው በደረጃው ቁልቁል መውረዱን ተያይዞታል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ በአንፃሩ ያለፉትን 3ተከታታይ ጨዋታዎች ድል በማድረግ ከ1ዓመት በኋላ የሊጉ አናት ላይ መቀመጥ ችሏል። በ12ኛ ሳምንት ጨዋታ ሲዳማ ቡና ላይ 6ግቦችን አዝንቦ ማሸነፉ ይታወሳል። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል የዘንድሮው ጥንካሬው ተደርጎ የሚወሰደው ቡድኑ ከሁሉም ክፍል ግብ ማስቆጠር መቻሉ ሲሆን እንደ አቡበከር ሳኒ አይነት ተጫዋቾች ደግሞ ከተቀያሪ ወንበር እየተነሱም ግብ ያስቆጥራሉ።

በሊጉ ወልዋሎ አ.ዩ. ካደረጋቸው 12ጨዋታዎች 4ጨዋታዎችን አሸንፈው 3አቻ በመውጣት 5ጨዋታዎችን ተሸንፈው ማግኘት ከሚገባቸው 36ነጥቦች ከግማሽ በታች 15ነጥቦችን ብቻ ሰብስቦ 12ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ቅዱስ ጊዮርጊስ እኩል 12ጨዋታዎችን አድርጎ 6ቱን አሸንፎ በ6ቱ አቻ ተለያይቶ በ1ጨዋታ ብቻ ሽንፈት አስተናግዶ በ23ነጥቦች የሊጉ አናት ላይ መቀመጥ ችሏል።

በነገው ጨዋታ ባለሜዳዎቹ የሚቀናቸው ከሆነ ነጥባቸውን 18 በማድረስ የሌሎች ቡድኖችን ውጤት በመጠበቅ እስከ 5ኛ ደረጃ መውጣት ሲችሉ ፈረሰኞቹ ድል የሚቀናቸው ከሆነ የሊጉ መሪነታቸውን ማጠናከር ያስችላቸዋል።

ነገ 9:00 ሲል በሚደረገው እና ፌደራል አርቢትር ብርሃኑ መኩሪያ በሚመሩት ጨዋታ ላይ በወልዋሎ አ.ዩ. በኩል ካርሎስ ዳምጠው፣ ፍቃዱ ደነቀ፣ አብዱላዚዝ ኬይታ፣ ዓይናለም ሀይሉ እና ሰመረ ሀፍተይ በጉዳት ምክንያት በነገው ጨዋታ ግልጋሎት የማይሰጡ ሲሆን በፈረሰኞቹ በኩል ደግሞ ረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ የነበሩት ግብ ጠባቂው ለዓለም ብርሀኑ፣ ሳለሀዲን ሰዒድ እና በቅርቡ የተጎዳው አስቻለው ታመነ ከነገው ጨዋታ ውጪ ሲሆኑ ናትናኤል ዘለቀ ከጉዳቱ ቢያገግምም ለጨዋታው ብቁ ባለመሆኑ ከነገው ጨዋታ ውጪ ይሆናል።

Muluken Tesfaye

Editor at Hatricksport website

Facebook

Muluken Tesfaye

Editor at Hatricksport website