የጨዋታ ቅድመ ዕይታ | ወልቂጤ ከተማ ከ አዳማ ከተማ

 

የ2012 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ምክንያት ለ3ሳምንታት የሚቋረጥ ይሆናል። ከዛ በፊትም 17ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች የሚከናወኑ ይሆናል። እነዚህ ጨዋታዎችም ነገ ሀሙስ ጅማሬያቸውን አድርገው እስከ እሁድ ፍፃሜያቸውን የሚያገኙ ይሆናል። ከነዚህ ጨዋታዎች ውስጥም ነገ (ሀሙስ) ወልቂጤ ከተማ አዳማ ከተማን የሚያስተናግድበትን ጨዋታ እንደሚከተለው ተመልክተነዋል።

በአወዳዳሪው አካል የዲስፕሊን ቅጣት ተላልፎበት ጨዋታዎችን በአዲስ አበባ ስታዲየም እንዲያደርግ የተገደደው ወልቂጤ ከተማ በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የሚያሰለጥነው አዳማ ከተማን ያስተናግዳል። አዲስ አዳጊው ወልቂጤ ከተማ ከጨዋታ ጨዋታ ራሱን እያሻሻለ የመጣ ቡድን ሲሆን ለትልልቆቹ ክለቦች ፈተና መሆኑን ማሳየት ችሏል። ለዚህም ደግሞ አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር አቻ የተለያየበት እና በ16ኛው ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስን ያሸነፈበት ጨዋታዎች በቂ ማሳያ ይሆናሉ።

በአሰልጣኝ ደግአረግ ይግዛው የሚሰለጥነው ወልቂጤ ከተማ በሊጉ ጠንካራ ተከላካይ ካላቸው ቡድኖች ጎራ የሚጠቀስ ነው። እስካሁን የተቆጠረባቸው ግብ 13 ብቻ ሲሆን 12ግብ ከተቆጠረባቸው ቅዱስ ጊዮርጊስ በመቀጠል ከፋሲል ከነማ ጋር በሊጉ ሁለተኛ ጠንካራ ተከላካይ ያለው ቡድን መሆን ችሏል። ክትፎዎቹ በመከላከሉ ረገድ ጠንካራ ቢሆኑም ግብ በማግባት በኩል እጅግ ደካማ እንደሆኑ በ16ጨዋታዎች ያስቆጠሩት 13ግቦች ብቻ መሆናቸው ምስክር መሆን ይችላል። ለዚህ የግብ ማግባት ድክመትም ቡድኑ ጫላ ተሺታ እና አህመድ ሁሴን ላይ ጥገኛ መሆናቸው በዋነኛነት ሊነሳ ይችላል።

አዳማ ከተማ በበኩሉ ከሜዳው ውጪ እጅግ የሚቸገር እና እስካሁንም ከሜዳው ውጪ ድል ማስመዝገብ ካቃታቸው ክለቦች አንዱ መሆን ችሏል። ለዚህም ደግሞ የአሰልጣኝ አባላቱ ለበርካታ ጊዜያት ከሜዳቸው ውጪ ሲጫወቱ የዳኞች ተጽዕኖ እንዳለ ሲገልፁ ይሰማል። ከዚህ ባሻገር ግን ከተጫዋቾቹ ጋር ገብቶ የነበረው የደሞዝ ክፈሉን ውዝግብ ቡድኑ ላይ ከፍተኛ የስነልቦና ተፅዕኖ ውስጥ እንዲገባና የውጤት ቀውስ እንዲከሰት አስገድዶታል። በአዳማ ከተማ በኩል ከነዓን ማርክነህ ከ ዳዋ ሁቴሳ ጋር ያላቸው ድንቅ ጥምረት ለቡድናቸው ጠቃሚ ቢሆንም የተከላካይ መስመሩ ግን መሻሻል ይጠበቅበታል። ከዚህ በተጨማሪም ከሜዳው ውጪ ሲጫወት ድል በማስመዝገብ ወደ መሪዎቹ ለመጠጋት ትግል ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።

በ16ኛው ሳምንት ሁለቱም ቡድኖች ከሜዳቸው ውጪ ጨዋታዎቻቸውን ያደረጉ ሲሆን የተለያየ ውጤት አስመዝግበው ለዚህኛው ሳምንት መጥተዋል። አዳማ ከተማ በ16ኛው ሳምንት ወደ ባህርዳር አቅንቶ ፋሲል ከነማን ገጥሞ በበዛብህ መለዮ ብቸኛ ግብ 1-0 ተሸንፎ የተመለሰ ሲሆን ወልቂጤ ከተማ በአንፃሩ ወደ አዲስ አበባ አቅንቶ በአዲስ አበባ ስታዲየም ቅዱስ ጊዮርጊስን ገጥሞ በጫላ ተሺታ ብቸኛ ግብ ጣፋጭ ድል ማስመዝገቡ ይታወሳል።

በነገው ጨዋታ ወልቂጤ ከተማ የሚያሸንፍ ከሆነ 6ኛ ደረጃውን የሚያስጠብቅ ሲሆን በአንፃሩ አዳማ ከተማ ድል የሚቀናው ከሆነ ከተጋጣሚው ወልቂጤ ከተማ በላይ መቀመጥ ይችላል።

ነገ 10:00 ላይ በሚደረገው እና ፌደራል አርቢትር ቢኒያም ወ/አገኘሁ በሚመሩት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ላይ በወልቂጤ በኩል ተከላካዩ ቶማስ ስምረቱ  በጉዳት ሲያጡ በአዳማ በኩል ደግሞ የመስመር ተከላካዩ ሱሌይማን ሰሚድን በተመሣሣይ በጉዳት እማይኖር ይሆናል።

Muluken Tesfaye

Editor at Hatricksport website

Facebook

Muluken Tesfaye

Editor at Hatricksport website