የጨዋታ ቅድመ-ዕይታ | ወላይታ ድቻ ከ ባህርዳር ከነማ

 

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ዙር ሊጠናቀቅ የ2ጨዋታዎች እድሜ ብቻ ሲቀረው በዚህ ሳምንትም የ14ኛ ሳምንት ተጠባቂ 8ጨዋታዎች የሚደረጉ ይሆናል። እነዚህ 8ጨዋታዎች ከዛሬ (ቅዳሜ) እስከ ከነገ በስትያ (ሰኞ) ድረስ የሚደረጉ ሲሆን ቅዳሜ 1፣ እሁድ 5 እንዲሁም ሰኞ 2ጨዋታዎች የሚደረጉ ይሆናል። ከነዚህ ጨዋታዎች መካከል ሶዶ ስታዲየም ላይ ወላይታ ድቻ ባህርዳር ከነማን የሚያስተናግድ ይሆናል።

ጨዋታ: ወላይታ ድቻ ከ ባህርዳር ከነማ
የጨዋታ ቀን: እሁድ የካቲት 08/2012
የጨዋታ ሰዓት: 9:00
የጨዋታ አርቢትር: ፌደራል አርቢትር ቢኒያም ወ/አገኘሁ
የጨዋታ ቦታ: ሶዶ ስታዲየም

ከቀድሞ አሰልጣኙ ገ/ክርስቶስ ቢራራ ጋር ከተለያየ በኋላ ጥሩ መነቃቃት ላይ የሚገኘው ወላይታ ድቻ ካለፉት 5ጨዋታዎች በ4ቱ ድል በማድረግ ከወራጅ ቀጠና ራሱን ማውጣት ችሏል። ለዚህ ውጤት መሻሻል ደግሞ የበረከት ወልዴ፣ እንድሪስ ሰዒድ፣ ቸርነት ጉግሳእና የባዬ ገዛኸኝ ጥሩ አቋም ላይ መገኘት እና ጥሩ ጥምረት መፍጠራቸው ተጠቃሽ ነው። ከዚህ በተጨማሪም በአንጋፋው ተከላካይ ደጉ ደበበ የሚመራው የተከላካይ ክፍል ባለፉት 5ጨዋታዎች 3ግቦች ማስተናገዱ ሌላው የቡድኑ ጥንካሬ ነው።

ባህርዳር ከነማ በአንፃሩ ግብ የማስቆጠር ችግር የማይታይበት ነገር ግን በቀላሉ የሚጋለጠው የተከላካይ መስመሩ በየጨዋታዎች በርከት ያሉ ግቦችን ለማስተናገድ እየተገደደ ይገኛል። ባህርዳር ከነማ በዚህ ሳምንት ባደረገው ጨዋታ ሰበታ ከተማን 3-2 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ቢችልም ሶስት ነጥብ ለማግኘት ግን እጅጉኑ ተፈትኗል። በተለይም ግብ አግብተው ግብ በቀላሉ የሚያስተናግድበት መንገድ ቡድኑ ያለውን ደከማ የመከላከል አቅም ከሜዳ ውጭ ነጥብ ይዞ እንዳይመለስ እያደረገው ይገኛል።

ወላይታ ድቻ በዘንድሮው ፕሪሚየር ሊግ ካደረጋቸው 13ጨዋታዎች 7ቱን ሜዳው ላይ ያከናወነ ሲሆን 3ቱን አሸንፎ 2ቱን ተሸንፎ በቀሪዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይቶ 7ግቦችን አስቆጥሮ 4ግቦችን አስተናግዷል። በአጠቃላይ ደግሞ ካደረጋቸው 13ጨዋታዎች 5ጨዋታዎች ሲያሸንፍ በ3ጨዋታዎች አቻ ተለያይቶ በቀሩት 5ጨዋታዎች ሽንፈት አስተናግዷል። በዚህም 14ግቦች አስቆጥሮ 12ግቦች ተቆጥረውበት 18ነጥቦችን በመሰብሰብ 8ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል።

ባህርዳር ከነማ በበኩሉ 7ጨዋታዎችን ከሜዳው ውጪ ሲያደርግ ምንም ጨዋታ ድል ማድረግ አልቻለም። 2ጨዋታዎችን አቻ ሲለያይ ቀሪ 5ጨዋታዎችን ተሸንፏል። በአጠቃላይ ደግሞ በ13ጨዋታዎች 6ጨዋታዎች አሸንፎ በ2ቱ አቻ ወጥቶ በ5ቱ ሽንፈት ሲያስተናግድ 21ግቦችን ሲያስቆጥር በተቃራኒው 22ግቦችን አስተናግዶ 20ነጥቦችን በመሰብሰብ 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

በወላይታ ድቻ በኩል ተከላካዩ ያሬድ ዳዊት በጉዳት የማይሰለፍ ሲሆን እንግዳው ባህርዳር ከነማ በኩል ደግሞ ፍቅረሚካኤል አለሙ፣ አዳማ ሲሴኮ፣ ማማዱ ሲዲቤ እና ሳላአምልክ ተገኝ በጉዳት እንዲሁም ፍፁም አለሙ 5 ቢጫ በመመልከቱ በቅጣት የማይኖር ይሆናል።

Muluken Tesfaye

Editor at Hatricksport website

Facebook

Muluken Tesfaye

Editor at Hatricksport website