የጨዋታ ቅድመ-ዕይታ | ኢትዮጵያ ቡና ከ ወልቂጤ ከተማ

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 13ኛ ሳምንት የመጨረሻ 1 ጨዋታ ነገ ሲደረግ የውጤት ቀውስ ውስጥ የሚገኘው ኢትዮጵያ ቡና በደጋፊው ፊት ወልቂጤ ከተማን የሚገጥም ይሆናል።

ባሳለፍነው እሁድ ሊካሄድ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ምክንያት ወደ ነገ (ሀሙስ) የተዛወረ ሲሆን ሁለቱም ቡድኖች ጨዋታውን ለማሸነፍ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የካሳዬ አራጌው ኢትዮጵያ ቡና ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ መሻሻሎችን እያሳየ ቢገኝም ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች መሸነፉ ወራጅ ቀጠና ውስጥ እንዲገኝ አድርጎታል። ያለፉትን 3ተከታታይ ጨዋታዎች ድል ማድረግ ያልቻለው ኢትዮጵያ ቡና የነገውን ጨዋታ ድል በማድረግ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት የሚጫወት ይሆናል።

በዘንድሮው የውድድር ዓመት ኢትዮጵያ ቡና በሊጉ አዲስ አይነት አጨዋወት ይዘው የመጡ ሲሆን፣ በተለይ ጨዋታውን ከኋላ መስመር በማስጀመር ኳስን ተቆጣጥሮ በመጫወት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ ሲሞክሩ ይስተዋላል። በዚህ የጨዋታ ዘይቤ ግን ብዙ ጊዜ ለማስተዋል እንደቻልነው ተጭኖ የሚጫወት ተጋጣሚ ቡድን ሲገጥም የመሳሳት ችግር ይስተዋልበታል። ከዚህ ባለፈ ደግሞ ቡድኑ ከሜዳው ውጪ ሲጫወት ደካማ አቋም እያሳየ የሚገኝ ሲሆን ለዚህም እንደማሳያ ሊቀርብ የሚችለው ከሜዳው ውጪ ምንም ጨዋታ ማሸነፍ አለመቻሉ ነው። በሜዳው በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ግን ሀያልነቱን ሲያሳይ ታይቷል። ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ ቡና ባለፉት 3ጨዋታዎች ያስቆጠሩት 1ግብ ብቻ መሆኑ ደግሞ የቡድኑን ችግር ያጎላዋል። ለዚህ ደግሞ እንደ ዋነኛ ምክንያት የሚጠቀሰው የቡድኑ ዋነኛ አጥቂ አቡበከር ናስር ጉዳት ላይ መገኘት እና ሌሎቹ አጥቂዎች የሱን ቦታ አለመሸፈን ነው።

ወልቂጤ ከተማ በአንፃሩ ለሊጉ አዲስ ቢሆንም ጠንካራነቱን እያሳየ ይገኛል። በተለይ ከትልልቅ ቡድኖች ጋር ሲጫወት ጥንካሬውን በደምብ መመልከት ይቻላል። ለዚህ ደግሞ ማሳያ የሚሆነው ወልቂጤ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር አቻ ሲለያይ፣ በሊጉ ጠንካራ ጉዞ እያደረጉ የሚገኙትን ፋሲል ከነማ እና ባህርዳር ከነማን ማሸነፍ ችሏል። በክትፎዎቹ በኩል የሳዲቅ ሴቾ ግብ አስቆጣሪነት ከአምበሉ አዳነ ግርማ እና ጫላ ተሺታ ድንቅ ብቃት እንዲሁም የሰዒድ ሁሴን ወደ ግብ አግቢነት መመለስ ጋር ተዳምሮ ለቡድኑ ውጤት ማማር ወሳኙን ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

ከዚህ ጥንካሬ ባሻገር ግን ቡድኑ ከሜዳው ውጪ ሲጫወት ከፍተኛ ድክመት የሚታይበት መሆኑ የነገውን ጨዋታ ለኢትዮጵያ ቡና ቀላል ያደርግለታል ተብሎ ይጠበቃል። ወልቂጤ ከተማዎች በዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከጅማ አባጅፋር እኩል አነስተኛውን ግብ ያስቆጠረ ሲሆን (8 ግብ) ይህ ደግሞ በቡድኑ ዘንድ እንደ ትልቅ ድክመት የሚቆጠር ነው።

ኢንተርናሽናል አርቢትር ዶክተር ሃ/የሱስ ባዘዘው በሚመሩት እና ነገ (ሀሙስ) በሚካሄደው ጨዋታ ላይ በኢትዮጵያ ቡና በኩል በ8ኛው ሳምንት ጉዳት ያስተናገደው ወሳኙ አጥቂ አቡበከር ናስር ቀለል ያለ ልምምድ መስራት ቢጀምርም ለነገው ጨዋታ ግን የመድረሱ ነገር አጠራጣሪ ነው። በወልቂጤ ከተማ በኩል ይበልጣል ሽባባው በጨዋታው የማይሰለፍ ተጫዋች ነው።

Muluken Tesfaye

Editor at Hatricksport website

Facebook

Muluken Tesfaye

Editor at Hatricksport website