የጨዋታ ቅድመ-ዕይታ | ኢትዮጵያ ቡና ከ ወላይታ ድቻ

 

እለተ እሁድ ህዳር 21፣ 2012 ዓ.ም ጅማሬውን ያደረገው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያው ዙር የመጨረሻ ጨዋታዎችን ለማድረግ ከዛሬ (አርብ) ጀምሮ እስከ ሰኞ ድረስ ቀጠሮ ይዟል። እስካሁን ከተደረጉት የ14 ሳምንታት 112 ጨዋታዎች ውስጥ ከ3ጨዋታዎች በስተቀር ፍፁም ሰላማዊ እና መልካም እንግዳ አቀባበል የተስተዋለባቸው ነበሩ።

 

በዚህ ሳምንት ከሚደረጉ ተጠባቂ የ15ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ውስጥ በአዲስ አበባ ስታዲየም ኢትዮጵያ ቡና ወላይታ ድቻን የሚያስተናግድበትን ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል። መልካም ንባብ።

 

ጨዋታ: ኢትዮጵያ ቡና ከ ወላይታ ድቻ
የጨዋታ ቀን: እሁድ የካቲት 15/2012
የጨዋታ ቦታ: አዲስ አበባ ስታድየም
የጨዋታ ሰዓት: 9:00
የጨዋታ አርቢትር: ኢንተርናሽናል አርቢትር አማኑኤል ሃይለስላሴ

የዘንድሮው የካሳዬ አራጌ ኢትዮጵያ ቡና በሊጉ ወጥ አቋም ማሳየት ተስኖት ወራጅ ቀጠና አካባቢ የሚገኝ ሲሆን ከጨዋታ ጨዋታ መሻሻሎችን አሳይቶ ከዛ ደግሞ በተቃራኒው ድል እየራቀው አሰልጣኙ እና ተጫዋቾቹ ጫና ውስጥ ሊገቡ ችለዋል። በተለይ ደግሞ አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ያደርጋቸው የነበሩትን ጨዋታዎች ያለምንም ችግር በቀላሉ ሲያሸንፍ የምንመለከተው ኢትዮጵያ ቡና አሁን አሁን እሱም እየከበደው እየመጣ ይገኛል። ለዚህ ደግሞ እንደ ማሳያ ሊጠቀስ የሚችለው ያለፉትን በአዲስ አበባ ስታዲየም ያደረጓቸውን 3ተከታታይ ጨዋታዎች ማሸነፍ አለመቻላቸው እና በ3ቱ ጨዋታዎች 1ነጥብ ብቻ ማስመዝገባቸው ነው።

 

ከዚህ ባሻገርም ቡናማዎቹ ከሜዳቸው ውጪ የሚያደርጓቸውን ጨዋታዎች በቁላሉ ነጥብ ሲጥሉ እና ሲሸነፉ ማስተዋል ችለናል። ቡድኑ ጨዋታዎችን ከኋላ ከግብ ጠባቂ ጀምሮ ኳስ በመቆጣጠር ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረት የሚያደርጉ ሲሆን ተጋጣሚ ቡድን ግን ተጭኖ በመጫወት የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች ስህተት እንዲሰሩ ሲያደርጓቸው ይስተዋላል። በ8ኛው ሳምንት ከፋሲል ከነማ ጋር ሲጫወቱ ተጎድቶ የነበረው አጥቂው አቡበከር ናስር ባለፈው ሳምንት ወደ ሜዳ መመለሱ ለቡናማዎቹ እፎይታን የሚሰጥ ነው።

 

እንግዳው ቡድን ላይታ ድቻ በበኩሉ ከቀድሞው አሰልጣኙ ገ/ክርስቶስ ቢራራ ጋር ከተለያየ በኋላ እጅግ በርካታ መሻሻሎችን እያሳየ 5ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል። ወላይታ ድቻ ከቀድሞው አሰልጣኙ ጋር ከተለያየ በኋላ ካደረጋቸው 6ተከታታይ ጨዋታዎች በሀዋሳ ከተማ ብቻ ሽንፈት ሲያስተናግድ ቀሪዎቹን 5ጨዋታዎች ድል ማድረግ ችሏል።

 

በተጠባባቂ አሰልጣኙ ደለለኝ ደቻሳ የሚመራው ወላይታ ድቻ ከጊዜ ወደ ጊዜ ለተጋጣሚ ቡድን የሚያስጨንቅ መሆን ጀምሯል። ለዚህም ደግሞ የባዬ ገዛኸኝ፣ እዮብ አለማየሁ እና ቸርነት ጉግሳ ድንቅ ጥምረት መፍጠር እና ግብ ማስቆጠራቸው እንዲሁም የአንጋፋዎቹ ደጉ ደበበ እና ተስፋዬ አለባቸው ልምድ ማካበት ወላይታ ድቻዎችን የሊጉ አናት አካባቢ እንዲቀመጡ አስችሏቸዋል።

ነገ (እሁድ) በሚካሄደው ጨዋታ ባለሜዳው ኢትዮጵያ ቡና ድል የሚቀናው ከሆነ ነጥቡን ወደ 18ከፍ በማድረግ እስከ 9ኛ ደረጃ ከፍ ማለት ሲችል ወላይታ ድቻ በአንፃሩ ድል የሚቀናው ከሆነ የሲዳማ ቡናን እና የስሑል ሽረን ውጤት በመጠበቅ በ4ኛነት የመጀመሪያውን ዙር ማጠናቀቅ ይችላል።

በጨዋታው ያለፉትን 5ተከታታይ ጨዋታዎች ማሸነፍ የተሳነው ኢትዮጵያ ቡና ወይስ ካለፉት 6ጨዋታዎች 5ቱን በድል የተወጣው ወላይታ ድቻ ያሸንፍ ይሆን የሚለው ጉዳይ እግርኳስ አፍቃሪው ጨዋታውን በጉጉት እንዲጠብቀው ያደርገዋል።

ኢንተርናሽናል አርቢትር አማኑኤል ኃ/ስላሴ በሚመሩት እና እሁድ 9:00 ሲል በሚጀምረው ጨዋታ በኢትዮጵያ ቡና በኩል  አቡበከር ናስር የመጀመሪያ አሰላለፉ ውስጥ የመግባቱ ነገር አጣራጣሪ ሲሆን የፊት መስመር አጥቂው እንዳለ ደባልቄ ከአንደ ጨዋታ እረፍት በኃላ ዳግም ወደ ቋሚ አሰላለፍ  ይመለሳል ተብሎ ሲጠበቅ  በወላይታ ድቻ በኩል ደግሞ ደጉ ደበበ በጉዳት ምክንያት በጨዋታው የማይሳተፍ ይሆናል።

Muluken Tesfaye

Editor at Hatricksport website

Facebook

Muluken Tesfaye

Editor at Hatricksport website