የጨዋታ ቅድመ-ዕይታ | አዳማ ከተማ ከ ወልዋሎ አ.ዩ.

የ2012 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር እጅግ ሰላማዊ ፉክክር በታየበት ሁኔታ 14ኛ ሳምንት ላይ ሲደርስ በዚህ ሳምንትም በርካታ ተጠባቂ ጨዋታዎች ይደረጋሉ። በ14ኛ ሳምንት የሊጉ መርሐግብር 1 ጨዋታ ቅዳሜ ሲከወን 5ጨዋታዎች እሁድ እንዲሁም ቀሪ 2ጨዋታዎች ደግሞ ሰኞ የሚደረጉ ይሆናል። ከነዚህ ተጠባቂ ጨዋታዎች መካከል አዳማ ላይ አዳማ ከተማ ወልዋሎ አ.ዩ.ን የሚያስተናግድበት ጨዋታ ተጠቃሹ ነው።

በሊጉ በውጤት ረገድ ግራ መጋባት ውስጥ የሚገኙት ሁለቱ ቡድኖች ነገ (እሁድ) 9:00 ሲል በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ይሆናል። በአዳማ ከተማ በኩል ቡድኑ በሜዳው ጥንካሬውን የሚያሳይ ቡድን ቢሆንም ከሜዳው ውጪ ግን እጅግ ሲቸገር ይስተዋላል። ለዚህም እንደ ማሳያ የሚወሰደው አዳማ ከተማ በሊጉ ከሜዳቸው ውጪ ማሸነፍ ካልቻሉ ቡድኖች መካከል አንዱ መሆኑ ነው። ከዚህ ባለፈ ግን የቡልቻ ሹራ እና የዳዋ ሁቴሳ ጥሩ አቋም ላይ መገኘት የተከላካይ ክፍሉ ለሳሳው ወልዋሎ አ.ዩ. ፈተና እንደሚሆን ይጠበቃል።

በወልዋሎ አ.ዩ. በኩል ሜዳ ላይም ከሜዳ ውጪም በርካታ ችግር እየተስተዋለበት ይገኛል። በዘንድሮው ሊግ ሁሉንም ጨዋታውን ከሜዳው ውጪ እያደረገ የሚገኘው (የሜዳው ላይ ጨዋታውን ትግራይ ስታዲየም ላይ ይገኛል።) ወልዋሎ አ.ዩ. ከሜዳው ጋር በተያያዘ ከፌዴሬሽኑ ጋር አለመግባባት ውስጥ ገብቶ ቆይቶ ከ15ኛው ሳምንት ጀምሮ ግን በሜዳው አዲግራት ስታዲየም ላይ ጨዋታውን ማድረግ የሚጀምር ይሆናል። ከዚህ በተጨማሪም ቡድኑ ከአሰልጣኙ ዮሐንስ ሳህሌ ጋር የገባበት አለመግባባት ሌላው ለውጤቱ ማሽቆልቆል ጉልህ አስተዋጽኦ ይጫወታል። ወልዋሎ በ13ኛው ሳምንት በቅዱስ ጊዮርጊስ ከተሸነፈበት ጨዋታ በኋላ አሰልጣኙ ከክለቡ የተሰወሩ ሲሆን ልምምድ ሜዳ ላይም ሆነ ሆቴል ሊገኙ አለመቻላቸውን የክለቡ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አሸናፊ አማረ ገልፀው ነበር። ሆኖም የክለቡ የቦርድ አባላት ስብሰባ ተቀምጠው የአሰልጣኙን የስራ መልቀቂያ ተቀብለው መለያየታቸውን ትናንት (አርብ የካቲት 06 2012 ዓ.ም) አሳውቀዋል።

ወደ ሜዳ ጉዳዮች መለስ ስንል ደግሞ ወልዋሎ አ.ዩ. በ7ኛው ሳምንት ድሬዳዋ ከተማ ላይ ካስመዘገበው ድል በኋላ ያለፉትን 6ጨዋታዎች ማሸነፍ ተስኖታል።

ከዚህ በተጨማሪም ቡድኑ በመጀመሪያዎቹ ጨዋታዎች ጥንካሬ ቢያሳይም የፊት መስመራቸው ኳስ እና መረብን ለማገናኘት ሰንበትበት ከማለቱ ባሻገር የመከላከል መስመራቸው በቀላሉ እያፈሰሰ ባለፉት በሶስት ጨዋታዎች 10 ግቦች አስተናግዶ ከሊጉ አናት እጅግ ሊርቁ ተገደዋል።

በ13ኛው ሳምንት ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች ሽንፈት ያስተናገዱ ሲሆን አዳማ ከተማ ወደ ይርጋለም አቅንቶ በሲዳማ ቡና የ3-2 ሽንፈት ደርሶበት ሲመለስ ወልዋሎ አ.ዩ. ደግሞ በሜዳው በቅዱስ ጊዮርጊስ የ4-1 ሽንፈት ማስተናገዱ ይታወሳል። በሊጉ ካደረጓቸው 13 ጨዋታዎች አዳማ ከተማ 3ጨዋታዎችን ብቻ ሲያሸንፍ በ6ጨዋታዎች አቻ ተለያይቶ በቀሪዎቹ 4ጨዋታዎች ሽንፈት በማስተናገድ በ15ነጥቦች 11ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ወልዋሎ አ.ዩ. በበኩሉ በእኩል 13ጨዋታዎች 4አሸንፎ በ3ጨዋታዎች አሸንፎ በቀሪዎቹ 6ጨዋታዎች ተሸንፎ ከአዳማ ከተማ እኩል 15ነጥቦች ሰብስቦ በግብ ክፍያ ተበልጦ 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

ፌደራል አርቢትር ማኑኤ ወ/ጻዲቅ በሚመሩት ጨዋታ በአዳማ ከተማ በኩል ተከላካዩ ቴዎድሮስ በቀለ በጉዳት የማይሰለፍ ሲሆን ባለፈው ሳምንት ከሲዳማ ቡና ጋር ሲጫወቱ በተለያዩ ምክንያቶች ያለነበሩት ዳዋ ሁቴሳ እና ከነዓን ማርክነህ ወደ ሜዳ ይመለሳሉ። በወልዋሎ አ.ዩ በኩል አቼምፖንግ አሞስ፣ ሰመረ ሀፍተይ፣ ካርሎስ ዳምጠው፣ ፍቃዱ ደነቀ እና ዓይናለም ሀይሉ በጉዳት ከጨዋታው ውጪ ሲሆኑ አብዱላዚዝ ኬይታ ወደ ሜዳ ይመለሳል ተብሎ ይጠበቃል።

Muluken Tesfaye

Editor at Hatricksport website

Facebook

Muluken Tesfaye

Editor at Hatricksport website