የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 12ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ እና በቀጣዩ ሳምንት መጀመሪያ የሚደረጉ ሲሆን ስድስት ጨዋታዎች ነገ (እሁድ) ሲደረጉ ቀሪ ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ ከነገ በስትያ (ሰኞ) የሚደረጉ ይሆናል። በነገው እለት ከሚደረጉት ጨዋታዎች መካከል ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ሲዳማ ቡና የሚያደርጉትን ጨዋታ ለእናንተ እንዲስማማ አድርገን እንደሚከተለው ዳሰነዋል። መልካም ንባብ።
ጨዋታ: ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ሲዳማ ቡና
የጨዋታ ቀን: እሁድ ጥር 24/2012
የጨዋታ ሰዓት: 9:00
የጨዋታ አርቢትር: ኢንተርናሽናል አርቢትር በአምላክ ተሰማ
የጨዋታ ቦታ: አዲስ አበባ ስታዲየም
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 12ኛ ሳምንት ላይ የደረሰ ሲሆን በዚህ ሳምንትም የ11ኛ ሳምንት መርሀ ግብራቸውን በድል ያጠናቀቁትን ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሲዳማ ቡናን ያገናኛል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ በ11ኛው ሳምንት በተጠባቂው ሸገር ደርቢ ኢትዮጵያ ቡናን በሙሉዓለም መስፍን (ዴኮ) ብቸኛ ግብ ያሸነፈ ሲሆን ሲዳማ ቡና በበኩሉ በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ስታዲየም ላይ ወልዋሎ አ.ዩ.ን 5-0 በሆነ ሰፊ ውጤት በማሸነፍ ጣፋጭ ድል ማስመዝገብ ችሏል።
የአሰልጣኝ ሰርዳን ዝቪጅኖቨ ቅዱስ ጊዮርጊስ በዘንድሮው የውድድር አመት ረጃጅም ኳሶች እና ቀጥተኛ አጨዋወት ላይ ትኩረት በማድረግ የሚጫወት ሲሆን የተከላካይ ክፍሉ ጠንካራ ጥምረት በተለይ ደግሞ የአስቻለው ታመነ እና ኤድዊን ፍሪምፖንግ ጥምረት የቡድኑ ዋነኛ ጥንካሬ ሲሆን በሊጉ እስካሁን በተደረጉ 11 ጨዋታዎች 6ግብ ብቻ ማስተናገዱ ደግሞ እንደ ዋንኛ ማሳያ መጥቀስ ይቻላል።
ከዚህ በተጨማሪም ቡድኑ ከሁሉም አቅጣጫ ግብ የሚያስቆጥር መሆኑ ሌላው ጥንካሬው ነው። ለዚህ ደግሞ እንደ ማሳያ የሚቀመጠው ያለፉት 3ጨዋታዎች ላይ ቡድኑ ያስቆጠራቸውን 3ግቦች በሙሉ የተቆጠሩት በአማካይ ተጫዋቾች መሆናቸው ነው። (ምንተስኖት አዳነ ከሀድያ ሆሳዕና ጋር፣ ሀይደር ሸረፋ ከባህርዳር ከተማ ጋር እንዲሁም ሙሉዓለም መስፍን (ዴኮ) ከኢትዮጵያ ቡና ጋር) ይህ ማለት ቡድኑ አጥቂዎች ላይ ብቻ እንዳልተንጠለጠለ ማሳያ ነው።
ከዚህም አለፍ ሲል ድንቁን አጥቂ ሳላህዲን ሰዒድን በጉዳት በማጣታቸው ምክንያት በጋዲሳ መብራቴ፣ ጌታነህ ከበደ እና አቤል ያለው የተፈጠረው ጥምረት ወጣ ገባ የሚል ቢሆንም በተደጋጋሚ ጨዋታዎች የተቃራኒ ቡድን ተከላካዮችን ሲያስጨንቁ ይስተዋላል።
በሲዳማ ቡና በኩል ምንም እንኳን ከሜዳቸው ውጪ ሲጫወቱ የሚቸገሩ ቢሆንም የፊት መስመር ላይ በአዲስ ግደይ፣ ሀብታሙ ገዛኸኝ እና ይገዙ ቦጋለ የተፈጠረው ጥምረት ለቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካዮች ፈተና ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። ከተጠቀሱት ሶስት ተጫዋቾች በተጨማሪ በወልዋሎው ጨዋታ ድንቅ ብቃት ያሳየው እና 3ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን ማቀበል የቻለው ዳዊት ተፈራ ለፈረሰኞቹ የመሀል ሜዳ ክፍል ራስ ምታት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። ቡድኑ በሜዳው ተጋጣሚውን ለማሸነፍ የማይቸገር ሲሆን ከሜዳው ሲወጣ ግን በተጋጣሚው የኳስ ብልጫ እየተወሰደበት ሲሸነፍ ማስተዋል ችለናል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ በዘንድሮው የውድድር አመት ካደረጓቸው 11ጨዋታዎች 5ጨዋታዎችን በሜዳቸው ያደረጉ ሲሆን ከነዚህ 5ጨዋታዎች በ4ቱ ሲያሸንፉ ቀሪውን 1ጨዋታ ከስሁል ሽረ ጋር ያለግብ አቻ ተለያይተዋል። በአጠቃላይ በሊጉ 11ጨዋታዎች አድርገው በ5ጨዋታዎች አሸንፈው በ5ጨዋታዎች አቻ ወጥተው በ1ጨዋታ ደግሞ ተሸንፈው 20 ነጥቦችን በመሰብሰብ ከሊጉ መሪ መቐለ 70 እንደርታ በ2ነጥቦች ብቻ አንሰው በሊጉ 2ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችለዋል።
ሲዳማ ቡና በአንፃሩ በሊጉ ካደረጓቸው 11ጨዋታዎች 6ቱን ከሜዳቸው ውጪ አከናውነው 2 ጨዋታዎች አሸንፈው በ4ቱደግሞ ተሸንፈዋል። በአጠቃላይ በሊጉ 11ጨዋታዎች አድርገው በ4ጨዋታዎች አሸንፈው በ7ቱ ተሸንፈው ምንም ጨዋታ አቻ ሳይወጡ ማግኘት ከሚገባቸው 33 ነጥቦች 12ነጥቦችን ብቻ ሰብስበው 7ኛ ደረጃ መቀመጥ ችለዋል።
በእሁዱ ጨዋታ ፈረሰኞቹ የሚያሸንፉ ከሆነ እና መቐለ 70 እንደርታ የሚሸነፉ ወይም አቻ የሚወጡ ከሆነ የሊጉ አናት ላይ መቀመጥ ይችላሉ። በአንፃሩ ሲዳማ ቡና ድል የሚቀናቸው ከሆነ የሌሎች ቡድኖችን ውጤት በመጠበቅ እስከ 4ኛ ደረጃ ድረስ ከፍ ሊሉ ይችላሉ።
በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ የሚገኙት ለዓለም ብርሀኑ፣ ናትናኤል ዘለቀ እና ሰልሀዲን ሰዒድ በነገው ጨዋታ የማይሳተፉ ሲሆን የተከላካዩ አስቻለው ታመነ መግባትም አጠራጣሪ ነው። በሲዳማ ቡና በኩል ሙሉቀን ታሪኩ ከጉዳቱ ያገገመ ሲሆን ሚሊዮን ሰለሞን እና ወንድሜነህ ዓይናለም በጉዳት የማይሰለፉ ሲሆን፣ የግብ ጠባቂው መሳይ አያኖ መግባትም አጠራጣሪ ነው።
አስተያየት ይስጡ