የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በሊጉ መራዘም ላይ ምን መዘዝ ይዞ ሊመጣ ይችላል?

 

በመላው አለም የተንሰራፋው የኮሮና ቫይርስ ወረርሽኝ አለንጋው በርትቶ በርካታ ሀገራት በጭንቅ ጊዜ ውስጥ ናቸው። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከእለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው ታግደው እራሳቸውን በመኖርያ ቤታቸው ውስጥ ከልለው የወረርሽኙ መፍትሄ ምን ይሆን እያሉ እየተጠባበቁ ይገኛሉ።

እግር ኳስም የዚህ ወረርሽኝ አንዱ ሰለባ ነው። በመላው አለም የሚገኙ በርካታ እግር ኳሳዊ ውድድሮች ታግደዋል መታገድም ብቻ አይደለም ወረርሽኙ ይዞት የመጣው መዘዝ የእግርኳሱ አለም ምጣኔ ሀብትን ወገቤን… እራሴን እያስባለው ይገኛል። የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ክለቦች በያዝነው ወር ብቻ ከ100 ሚሊዮን ፓውንድ በላይ ከስረዋል ተብሎ ይገመታል። በዚሁ ከቀጠለ ደግሞ የሚደርሰው ኪሳራ የትየለሌ ስለመሆኑ አንዳች አጠራጣሪ ነገር የለም።

ከትናንት በስቲያ (ሰኞ መጋቢት 14 2012 ዓ.ም) ከቀትር በኋላ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና የሊጉ ኩባኒያ አንድ ላይ በመሆን በሰጡት መግለጫ ፕሪምየር ሊጉ በቀጣይ ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙን ተናግረዋል።

ይሄ የሊጉ መራዘም በሊጉ ላይ ምን መዘዝ ይዞ ሊመጣ ይችላል?

አብዛኞቹ የሊጉ ክለቦች በጀታቸውን ከመንግስት እና ከስፖንሰሮች (አንዳንዶቹ) የሚያገኙ ሲሆን ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ከስፖንሰሮች እና ከተለያዩ ከሚደጉሟቸው አካላት የአመት በጀታቸውን ያገኛሉ። እስከ ዛሬ ድረስ በሚዲያው እና በእግር ኳስ አፍቃሪው ከባድ ተቃውሞ ይደርስበት የነበረው የእግርኳስ ክለቦቻችን የገቢ ምንጭ በዚህ ወጀቡ ባየለበት ወቅት የክለቦቹ መጠለያ ሆኖ በአለም እግር ኳስ ላይ እየደረሰ ካለው የፋይናንስ ቀውስ ሊያድናቸው ይችላል የሚል ሀሳብ አለኝ።

ለምን ብላቹ ብትጠይቁኝ ምላሼን እንደሚከተልው አስፍሬዋለው።

ታላላቅ ሊጎች ከሚያገኙት ገቢ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው የብሮድካስት መብት ሽያጭ ነው።
ይህ ደግሞ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ክለቦች አስተዳደር ውስጥ ለአፍታም እንኳን ብልጭ የማይል ሀሳብ ሲሆን እንደ ድንገት እንኳን የተገለጠለት ክለብ ቢኖር በበርካታ ቢሮክራሲዎች እና የጥቅም ጉዳዮች ሀሳቡ መና ሲቀር ተመልክተናል። በዚህም ምክንያት በዚህ ጨለማ ወቅት በብሮድካስት ምክንያት ክለቦች የሚያጡት ቤሳቤስቲን የለም ማለት ነው።

ከብሮድካስት ውጪ ደግሞ ሌሎች የማርኬቲንግ መንገዶችን በመጠቀም ገቢ ማግኘት ለክለቦቻችን ተራራን የመውጣት ያህል ከባድ ስለሆነ ከመንግስት በሚያገኙት የአመት በጀት እድሜ ዘመናቸውን ባሉበት እየተራመዱ ይኖራሉ።

ይሄ የክለቦቻችን ኋላቀር አካሄድ በዚህ ወቅት ከስታድዮም ገቢ ማጣት እና አንዳንድ ክለቦች ደግሞ ከስፖንሰሮች ጋር ያላቸው ስምምንት ሊቋረጥ ስለሚችል ከዛ ላይ ከሚያጡት ገንዘብ ውጪ በአመታዊ በጀታቸው እንደለመዱት በማያቋርጥ እንቅልፍ ውስጥ ሆነው የውድድር አመቱን ሊጨርሱት ይችላሉ።

ሆኖም ግን መንግስት በዚህ ወረርሽኝ ምክንያት ኢኮኖሚው ተቃውሶ ኧረ የናንተ ነገርስ በቃኝ ቢሊዮን እየፈሰሰባቹ ጣጣቹ ግን ትሪሊዮን ነው። ከታክስ ከፋዩ ህዝብ ገንዘብ ሰብስቤ የጥቂቶችን ሆድ መሙላት ታክቶኛልም ፀፅቶኛልም ለናንት ስባሪ ሳንቲም እንኳን አልመድብም ስራቹ ያውጣቹ ጥራቹ ግራቹ ብሉ ብሎ ለክለቦች የሚመድበውን ገንዘብ ካቆመ ምንም አትጠራጠሩ የፕሪምየር ሊጉ ክለቦች የጤና ቡድን ሆነው በበጎው ዘመን ቁጭ ብለው ተወያይተው ፕሮጀክት ቀርፀው ፋይናንሳቸውን ማሳደግ እየቻሉ እነርሱ ግን የሚሊዮን ብር ቼኮችን መቀለጃ ማድረጋቸው እና ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ ጋር በፍቅር ወድቀው ባሉበት የተራመዱበት ወቅት ፀፅቷቸው ጥፍራቸውን እየበሉ መኖራቸው አይቀሬ ነው።