የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ውዥንብር ፈጣሪ ያላቸውን ግለሰቦች አስጠነቀቀ

 

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እግር ኳሱ ላይ ውዥንብርና ክፍተት የሚፈጥሩ በጣት የሚቆጠሩ ግለሰቦች እንዳሉ ደርሰንበታል ሲል አስታወቀ፡፡

ፌዴሬሽኑ ካፍ የሚያውቃቸው ኢንስት ራክተሮች እነማን ናቸው በሚል የተነሳውን ውዝግብ መፍትሔ ለመስጠትና በካፍ የዘጋጀው ኮንቬሽን ላይ የመገናኛ ብዙኃንን ጠርቶ በሰጠው መግለጫ የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው እንደተናገሩት “በደካማው እግር ኳሳችን ላይ ሌላ ችግር ተከስቷል ውዥንብር በመፍጠር ስፖርቱ በሠላም እንዳይቀጥል የሚያደርጉ ግለሰቦች እንዳሉ ደርሰንበታል የሀገራችን ኢንስትራክተሮች በካፍም ሆነ በፌዴሬሽኑ ገንዘብ አይከፈላቸውም በነፃነትና በእኔነት ስሜት ስራቸውን እንዳይሰሩ ሞራላቸው መነካቱ ግን መቆም አለበት” ሲሉ ቅሬታቸውን ገልፀዋል፡፡ ኢንስትራክተር ሰውነት እንደሚሉት “እውቀታችን ተበትኖ ያለፍን አቅምን ያለን ባለሙያዎችን ነን ካፍ የማንንም አገር ላይሰንስ አላደሰም እኔን ብትጠይቁኝ ኢንስትራክተር የሆንኩት በካፍ እንጂ ፌዴሬሽኑ አልሰጠኝም የተጠራሁትና ጋቦን ድረስ ሄጄ የወሰድኩት ላይሰንስ የማያረጅ ነው“ ሲሉ ተናግረዋል፡፡
“ቴክኒካል ዳይሬክተርነት ዝም ብሎ አይያዝም ከውጭ ለቦታው ራሳቸውን እያዘጋጁ ያሉ አሉ፤ በፍፁም ግን ይሄ አይሆንም” ያሉት የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢው “ከውጭ ሆነው ተጨዋቾቹን ለማሳመን የሚደረግ ሙከራ አለ፤ በጥቂት ግለሰቦች የሚደረግ ዘመቻን በተመለከተ ማስረጃው አለን ይሄን ጉዳይ ለማስቆም ፌዴሬሽኑ አስፈላጊ ነው ያለውን እርምጃ ይወስዳል፡፡ በመግለጫ ብቻ አንተወውም” ሲሉ ድርጊቱን ፈፃሚዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አስጠንቅቀዋል፡፡
በእለቱ ስለ ካፍ ኮንቬሽን ማብራሪያ የሰጡት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ በበኩላቸው “ፕሮ ላይሰንስ ስልጠና ለኢትዮጵያ መጥቶ ፌዴሬሽኑና ኢንስትራክተሮች ከልክለዋል የሚለው ትልቅ ውሸት ነው፤ ምንም የመጣ ስልጠና የለም በአፍሪካ ደረጃ ለሙከራ የጀመረችው ከፈረንሣይ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በመነጋገር መሮኮ ስትሆን ይህም ለሙከራ የተደረገ ነው” ሲሉ ገልፀዋል፡፡ ኢንስትራክተር አብርሃም ከዳር ሆነው እየተታኮሱ ነው ላሏቸው ሰዎች ባስተላለፉት መልዕክት “ዳርና ዳር ይዘን አንታኮስም ይሄ ለሀገር አይጠቅምም እንደ ባለሙያ ተከባብረን አብረን እንስራ፤ በጋራ ከመስራት ውጪ መሰዳደብና መተቻቸት መቆም አለበት” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ፌዴሬሽኑ በሰጠው በዚህ መግለጫ በካፍ ደረጃ የሚታወቅ ኤሊት ኢንስትራክተር አንድ ሲሆን እሱም ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ መሆኑ አስታውቋል፡፡ ከዚህ ውጪ በወንዶች ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው፣ ኢንስትራክተር ዶ/ር ሲራክ ኃ/ማርያም፣ ኢንስትራክተር አብርሃም ተ/ኃይማኖት፣ ኢንስትራክተር መኮንን ኩሩ፣ ኢንስትራክተር ዳንኤል ገ/ማርያም፣ ኢስትራክተር ዶ/ር ጌታቸው አበበ እና ኢንስትራከተር አንተነህ እሸቴ ሲሆኑ በስቶች ደግሞ ኢንስትራክተር ሠላም ዘራይ፣ ኢንስትራክተር መስከረም ጎሽሜ፣ ኢንስትራክተር መሠረት ማኔ፣ ኢንስትራክተር ህይወት አረፋአይኔ፣ ኢንስ ትራክተር በኃይሏ ዘለቀን ብቻ እንደሚያውቅ አስታውቋል፡፡

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport