የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ እግር ኳስ ክለብና ተጨዋቾች ላይ የቅጣት ውሳኔ ያሳለፈው በ22ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ኘሪሚዮር ሊግ በአዲስአበባ ስታዲዬም ፍፃሜውን ባለገኘው መከላከያ እና ወልዋሎ አ/ዩ ባደረጉት ጨዋታ በ83ኛው ደቂቃ በተፈጠረ የስፖርታዊ ጨዋነት ጥሰት በእለቱ የመሃል ዳኛ እያሱ ፈንቴ ላይ የደረሰባቸውን ድብደባ ተከትሎ ነው፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዲሲኘሊን ኮሚቴ በዕለቱ ከዳኞች የቀረበለትን የጨዋታ ሪፖርት በመመልከት በክለቡና በተጨዋቾቹ ላይ የቅጣት ውሳኔ ሲያሳልፍ በተቃራኒው ለጥቂት ተጨዋቾች የምስጋና ደብዳቤ እንዲፃፍላቸው ውሳኔ አሳልፏል፡፡
የፌዴሬሽኑ ዲሲፕሊን ኮሚቴ ዳኛ እያሱ ፈንቴን የመታውን የወልዋሎ ቡድን መሪ አቶ ማሩ ገብረፃዲቅን ከማንኛውም እግር ኳስ ውድድር ላይ እድሜልክ እንዳይሳተፍ እገዳ ሲጥል፡ተጨዋች ዋለልኝ ገብሬ 2ዓመት ፌዴሬሽኑ ከሚያዘጋጃቸው ውድድሮች የጨዋታ ዕገዳና ብር 15ሺ እንዲቀጣ ውሳኔ ሲያሳልፍ በተጨዋቾች- አፈወርቅ ሀይሉ፡በረከት ተሰማ፡ማናዬ ፋንቱ፡ አስሪ አልማህዲ፡አለምነህ ግርማና በረከት አማረ:ላይ የስድስት ወር የጨዋታ እገዳና እያንዳንዳቸው ብር 10ሺ እንዲቀጡ ሲወሰን፡ የዲሲፕሊን ኮሚቴው ወልዋሎ አ/ዩ ከጉዳዩ መከሰት በሇላ የቡድኑን መሪ እስከማሰናበት የደረሰ ውሳኔ ከማሳለፉ ባሻገር በተጨዋቾቹ ላይ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን በበጎ ጎን በማየት 250ሺ ብር በቅጣት እንዲከፍል ተወስኗል፡፡
በሌላ በኩል በዕለቱ ዳኛ እያሱ ፈንቴን ከአደጋ ለማዳን ጥረት ያደረጉት የመከላከያዎቹ ዳዊት እስጢፋኖስና ፡ፍፁም ገ/ማርያም እንዲሁም የወልዋሎው ተስፋዬ ደበበ ከፌዴሬሽኑ የምስጋና ደብዳቤ እንዲፃፍላቸው ተወስኗል፡፡የዕለቱ ጨዋታ ፍፃሜውን አለማግኘቱ የሚታወስ ቢሆንም ኮሚቴው መከላከያ በፎርፌ 3 ነጥብና 3 ጎል እንዲያገኝ ሲወሰን ወልዋሎ ተሸናፊ ሁኗል፡፡
በዚህም መከላከያ በ22 ጨዋታዎች በ28 ነጥብና በ4 የግብ ዕዳ በደረጃ ሰንጠረዡ ወደ 9ኛ ከፍ ሲል ወልዋሎ በ21 ጨዋታዎች በ20 ነጥብና በ8 የግብ ዕዳ በነበረበት የወራጂ ቀጠናው አፋፍ 13ኛ ደረጃ ረግቷል፡፡


አስተያየት ይስጡ