የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የቀድሞ ተጨዋች ሰይፈ ውብሸት /ፕሮም/ ለኮሮና ቫይረስ ከፍተኛ እርዳታ አደረገ

የእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመኑን በክለብ ደረጃ ላሳደገው ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና በኋላም ላይ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ለጥቂት ጊዜያት ደግሞ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ክለብ ተጫውቶ ያሳለፈው የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ድንቅና ምርጥ የግራ መስመር የኮሪደር ስፍራ ተጨዋች የሆነው ሰይፈ ውብሸት ፕሮም የአሁን ሰዓት ላይ በዓለምም ሆነ በሀገራችን ከፍተኛ ወረርሽኝ እየሆነ በመምጣት ላይ ላለው እና የብዙ ሰዎችን ህይወት እየቀጠፈ ለሚገኘው የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ይውል ዘንድ ለሀገሬ እና ለህዝቤ አለውልሽ በሚል ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ300 ሺ ብር ጥሬ ገንዘብና ለ200 ሰዎች የሚሆን ደግሞ 200 ሺ ብር የሚያወጣ ቁሳቁስን የረዳ ሲሆን በወላጅ እናቱ አማካኝነት ደግሞ በተወለደበት የበረንዳ አካባቢ በሚገኘው የ02 ቀበሌ አካባቢም እስከ 15 ኩንታል የሚደርስ የእህል እርዳታ ድጋፍን ማድረጉ ታውቋል።
የኢትዮጵያ ታዳጊ እና የዋናው ብሄራዊ ቡድን የቀድሞው ምርጥ ተጨዋች ሰይፈ ውብሸት ፕሮም የአሁን ሰዓት ላይ ኑሮውን በስዊዘርላንድ ሎዛን ከተማ ያደረገ ሲሆን ከሀገር ከወጣ 20 ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም ወደ ኢትዮጵያ በሚመጣ ሰዓት ለተቸገሩ የቀድሞ ስፖርተኞችም በየጊዜው የተለያዩ እርዳታዎችን እንደሚያደርግም ይታወቃል።


ሰይፈ ውብሸት በተጨዋችነት ዘመኑ ከኤሌክትሪክ ጋር የመጀመሪያውን የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ ያነሳ ተጨዋች ሲሆን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋርም የዚህ ዋንጫን ያነሳም እንደሆነ ይታወቃል።
6 ቁጥር ለባሹ ሜዳ ላይ በግራ እግሩ በሚያሳየው ታምራዊ እና የማይጠገብ የኳስ ብቃቱ እንደዚሁም ደግሞ በጥቁረቱ እና መብራት ሀይል እያለ ደግሞ በነጩ የቡድኑ መለያ ወደ ሜዳ በሚገቡበት ሰዓት ይሄ ተጨዋች ከእነ መልኩና አጨዋወቱ የብላክ ስታሮቹን አጨዋወት ይመስላል በሚል በዛን ጊዜ ጋናዎች ጥሩ ጨዋታን ይጫወቱ ነበርና ሰይፈን ጋናዊ ነው እንዴ እስከማለት ደረጃ በመድረስ በርካታ አድናቂዎችንም በችሎታው አትርፎ የነበረ ሲሆን ወደ ስዊዘርላንድም ከባለቤቱ ወለላ ጋር ካመራ በኋላም በእዛው ሀገር ላይ ለሚገኝ ቡድን ኳስን መጫወት በጀመረበት ወቅትም በጊዜው ሪያል ማድሪድ ሎዛን ላይ ትራንዚት ሲያደርግ ዚዳንንም ሆነ ሪያል ማድሪድን በተቃራኒነት መግጠሙም ታውቋል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የቀድሞ ተጨዋች እንደ ሀገራችን ማህበራት እና ግለሰቦች እሱም የበኩሉን እርዳታና ድጋፍ በማድረጉ ሊመሰገን ይገባል።

Editor at Hatricksport website

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Editor at Hatricksport website