የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ደጋፊዎች ማህበር ለኮሮና ቫይረስ መከላከያ እርዳታ አሰባሰቡ

 

የኮሮና ቫይረስ ለዓለም ከፍተኛ ስጋት ሆኖ በርካታ የሰው ህይወትን እያጠፋ በሚገኝበት እና ወደ እኛም ሀገር ይህ ቫይረስ ገብቶ የተያዦቹ ቁጥር ዕለት ተዕለት እየጨመረ በመጣበት የአሁኑ ሁኔታ ለቫይረሱ መከላከያ ይሆን ዘንድ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የደጋፊዎች ማህበርም እርዳታን በማሰባሰብ እና ራሱም እርዳታን በማድረግ የራሱን የሆነ ማህበራዊ ግዴታውን እየተወጣ ሲሆን በእዚህም ከፍተኛ ምስጋና እየቀረበለት ይገኛል።


ለወገን ደራሽ ወገን ነው የሚል መሪ ቃልን ያነገበው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የደጋፊዎች ማህበር ትናንት ካዛንችስ አካባቢ ባደረገው የእርዳታ እና የድጋፍ አሰባሰብ ፕሮግራም ላይ ከገንዘብ አንስቶ ለቫይረሱ መከላከያ የሚሆኑ ነገሮችና ምግቦችን ጨምሮ ከማህበረሰቡ ያገኘ ሲሆን በእዚህ እርዳታ የማሰባሰብ ሂደታቸው ላይ በተለይ ደግሞ በእዛው አካባቢ በጉሊት ስራ ላይ ለበርካታ ዓመታት ተሰማርተው የሚገኙትን ወይዘሮ ፀሀይ ዱፌራ ካላቸው አነስተኛ ገቢ ላይ ለምንም ነገር ሳይሳሱ ወገኔ ይበልጥብኛል ብለው ለኮሮና ቫይረሱ መከላከያ የ500 ብር ድጋፍ እና አሰባሳቢዎቹን ምሳ በማብላታቸው እንደዚሁም ቤተልሄም ምግብ ቤትን የጄኔቭ ሆቴል ባለቤትን ሸዋ ሱፐር ማርኬትን የአረቧ ምግብ ቤት ባለቤትን ቆዝላ መሀመድን የካዛንችስ አካባቢ ነዋሪዎችን የወረዳ 8 ወጣቶችና በጎ ፈቃደኛ ማስተባበሪያ ቢሮ እና የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 አስተዳደርም ከእነሱ ጋር ሆኖ ለሰራው ከፍተኛ ስራ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የደጋፊዎች ማህበር ትናንት ባካሄደው የእርዳታ አሰባሰብ ፕሮግራም ላይ በተለይ ኢትዮጵያ ከ31 ዓመታት በኋላ ለደቡብ አፍሪካው የአፍሪካ ዋንጫ ስታልፍ የቡድኑ ተጨዋቾች ከነበሩት ውስጥ ብርሃኑ ቦጋለ /ፋዲጋ/ ስዩም ተስፋዬ እና አስራት መገርሳ የተገኙና እነሱም ድጋፍን ያደረጉ ሲሆን ለእነሱም ምስጋና ከመቅረቡ ባሻገር ከዋልያዎቹ የደጋፊ ማህበርም አንድ የብሄራዊ ቡድን ማልያ መጥቶ ለሶስቱ ዕጣ ከወጣ በኋላ ማልያው ለብርሃኑ ቦጋለ ደርሶት በስጦታ መልክ ተበርክቶለታል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የደጋፊዎች ማህበር የትናንቱን ጨምሮ ሰሞኑን ለኮረና ቫይረስ መከላከያ የእርዳታ ማሰባሰብ ፕሮግራም ላይ ተሳታፊ በመሆኑም እንደሌሎቹ ማህበራት ሁሉ እያስወደሰውም ይገኛል።

Editor at Hatricksport website

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Editor at Hatricksport website