የኢትዮጵያ ቡና የቀድሞ እግር ኳስ ተጨዋቾች ማህበር ከብራዚል ባስመጣው የእግር ኳስ ባለሙያ ስልጠና ተሰጠ

የኢትዮጵያ ቡና የቀድሞ እግር ኳስ ተጨዋቾች ማህበር ከብራዚል ባስመጣው የእግር ኳስ ባለሙያ አማካኝነት ለ3 ቀናት ያህል ማለትም ከጥር 28 እስከ ጥር 30 ባሉት ጊዜያቶች ከ17 ዓመት በታችና ከ20 ዓመት በታች ለሚያሰለጥኑ ኢትዮጵያውያን አሰልጣኞች ሲያሰጥ የነበረው የእግር ኳስ ስልጠና ኮርስ በትናንትናው ዕለት በሶሎቴ ሆቴል ተጠናቅቋል።
ብራዚላዊው የእግር ኳስ ባለሙያ ሚስተር አርማንዲኒሆ ማንጄታ በአሁን ሰዓት ወደ አገራችን በመምጣት ይህን የስልጠና ኮርስ ሊሰጡ የቻሉት ነዋሪነቱን በአሜሪካ ሀገር ባደረገው የኢትዮጵያ ቡናና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የቀድሞ ተጨዋች ከነበረው መሀመድ ኢብራሂም ኪንግ ጋር በነበራቸው መልካም የሆነ ግንኙነት እና ተግባቢነት ሲሆን በኪንግ አማካኝነትም ባለሙያው ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ይሄን የስልጠና ኮርስ መስጠታቸውም በኢትዮጵያውያን አሰልጣኞች ዘንድ ምስጋና ሊቀርብላቸው ችሏል። የኢትዮጵያ ቡና የቀድሞ እግር ኳስ ተጨዋቾች ማህበርም በቀድሞ ተጨዋቻቸው አመቻችነት ይህ ስልጠናን ከእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ጋር በጋራ በመተባበር እንዲሰጥ በማድረጋቸው እነሱም የተመሰገኑ ሲሆን በፌዴሬሽኑ ዘንድም እኛ የምንፈልገው እንዲህ ያለ አሰራርን ነው በማለትም ይህ የጋራ ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል እንዳሉም ተሰምቷል።


ብራዚላዊው የእግር ኳስ ባለሙያ የስልጠና ኮርሱን ሰጥቶ ካጠናቀቀ በኋላ ወደ ሀገሩ ሲመለስ ከክለቡ ክሩዜሪዮ ጋር በመነጋገር ኢትዮጵያን አሰልጣኞችም በማርች እና ጁላይ ወራቶች ወደ ብራዚል ተጉዘው ስልጠና የሚወስዱበትን እና እዚም ሲመለሱ እነሱ የተማሩትን ሊያስተምሩ የሚችሉበትን ሁኔታ ለመፍጠር ከእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ጋር የጋራ ስምምነት ፊርማ መከናወኑም ተነግሯል።
ብራዚላዊው የእግር ኳስ ባለሙያ በስፖርት ህይወቱ
በአሜሪካ በካናዳ በፖርቹጋል እና በሆላንድ የፕሮፌሽናል ሊጎች ውስጥ ተጫውቶ ያሳለፈ ሲሆን የብራዚሉ ክለብ ኤፍ ሲ ክሩዜይሮን ጨምሮ በተለያዩ ክለቦች ውስጥም በቴክኒካል አማካሪነት ሰርቶም ቆይቷል። በአሁን ሰዓት ደግሞ የክሩዜይሮ ክለብ ውስጥ የስካውንቲንግ ዲፓርትመንት ቴክኒካል አማካሪ ሆኖ እየሰራም ይገኛል። ይሄ ባለሙያ ከዛ ውጪም ሀገራቶች የቴክኒካል ድጋፍ ሲፈልጉም ወደ እነሱ በመሄድ እውቀትን ያካፍላል። በእስካሁኑ ቆይታውም ወደ አውስትራሊያ ካናዳ አሜሪካ እና በቅርቡ ደግሞ ወደ አንጎላ በመሄድም ትምህርትን ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ቡና የቀድሞ እግር ኳስ ተጨዋቾች ማህበር ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በጋራ በመሆን ይህ ስልጠና እንዲጠናቀቅ ካደረገ በኋላ የስልጠና ሜዳውን ለፈቀደላቸው ወጣቶች አካዳሚና ለሶሎቴ ሆቴል ባለቤት ምስጋናቸውን ገልፀዋል።

Editor at Hatricksport website

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Editor at Hatricksport website