በመሸሻ ወልዴ
ሀትሪክ፡- ከወልቂጤ ከተማ ጋር አቻ
ተለያይታችሁ የፕሪምየር ሊጉን ነጥብ
በመጣል ጀምራችኋል፤ ጨዋታው ምን መልክ
ነበረው? ውጤቱስ ለእናንተ የሚገባ ነው?
አብዱልከሪም፡- ወልቂጤን ወደ
ዝዋይ ተጉዘን የተፋለምንበት የፕሪምየር
ሊጉ መክፈቻ ጨዋታ ውጤቱ ለእኛ
የሚገባን ባይሆንም በሜዳ ላይ የነበረን
እንቅስቃሴ በጣም ጥሩ ነበር፤ ያም ሆኖ
ግን በርካታ የግብ ዕድሎችን አግኝተን
አልተጠቀምንበትም፤ ከዛም ባሻገር
የሁለቱም ክለብ ደጋፊዎች በስፖርታዊ
ጨዋነት ይሰጡት የነበረው ድጋፍ በጣም
የሚያምርም ነበርና ይህንን በጨዋታው
ላይ ለመመልከት ችያለው፤ በጨዋታው
ያስመዘገብነውን ውጤት በተመለከተ በዕለቱ
አሸናፊነት እንጂ ሌላ ውጤት ፈጽሞ
አይገባንም ነበር፡፡
ሀትሪክ፡- ወልቂጤ ከተማን እንዳታሸንፉ
ምን ነበር የጎዳችሁ?
አብዱልከሪም፡- ከወልቂጤ ከተማ ጋር
ባደረግነው የእሁዱ ጨዋታ ቡድናችን
የግጥሚያው አሸናፊ ሆኖ እንዳይወጣ
ያስቻለው ዋንኛው ጉዳይ ቢኖር
ወሳኞቹ የፊት መስመር የአጥቂ
ስፍራ ተጨዋቾቻችን ሳላህዲን ሰይድ
እና ጌታነህ ከበደ በጉዳት ምክንያት
ሊሰለፉልን አለመቻላቸው ያገኘ
ናቸውን የጎል እድሎች እንዳንጠቀም
ስላደረጉን ጨዋታው በአቻ ውጤት
እንዲጠናቀቅ አድርጎታል፡፡
ሀትሪክ፡- ወልቂጤ ከተማዎችን
በጨዋታው ላይ እንዴት
ተመለከትካቸው?
አብዱልከሪም፡- ወልቂጤዎች
እኛን በተፋለሙበት የሊጉ
የመክፈቻ ጨዋታ ከእንቅስቃሴ አንጻር
እንደተመለከትኳቸው ጥሩ ተፎካካሪ የነበሩ
እንጂ እንደወረደ አይነት ቡድን ሆነው
አላገኘዋቸውም፤ ከዛ ውጪም በርካታ ደጋፊ
ያላቸው ከመሆኑ አኳያም በእነሱ በመመራት
ጠ ን ክ ረ ው
ሊጫወቱም
ችለዋል፡፡
ሀትሪክ፡- ወልቂጤን አለማሸነፋችሁ
አስቆጭቷችኋል?
አብዱልከሪም፡- በጣም እንጂ! ምክንያ
ቱም ከእነሱ ጋር ያደረግነው ጨዋታ ለሁለ
ታችንም ሜዳው አዲስ እና አምሳ አምሳ
ስለሆነም ነው፤ ብዙ ጊዜ ከሜዳ ውጪ
የምታደርጋቸውን ጨዋታዎች በአቻ ውጤት
መለያየት ምንም አይልም፤ ጥሩ ነው ብለህ
የምታልፈው ቢሆንም የእሁዱን ጨዋታ
ግን በድል አድራጊነት አለማጠናቀቃችን
እያስቆጨን ይገኛል፡፡
ሀትሪክ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ የሊጉን
የመክፈቻ ጨዋታ ነጥብ በመጣል መጀመሩ
ያዋጣዋል?
አብዱልከሪም፡- በፍጹም አያዋጣውም፤
ሊጉን በአሸናፊነት ነበር መጀመር የነበረብን፤
ከዚህ ቀደም ሊጉን ስንጀምር ተመሳሳይ ነገር
ይገጥመን ስለነበር ያንን ለማስቀረት ፈልገን
ነበር፤ ግን አልተሳካልንም፡፡
ሀትሪክ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ ከወልቂጤ
ከተማ አቻ የተለያየበት ጨዋታ ለእናንተ ምንን
አስመልክቶአችሁ አልፏል?
አብዱልከሪም፡- ከወልቂጤ ከተማ ጋር
ያደረግነው የሊጉ መክፈቻ ጨዋታ ለእኛ
አቻ መለያየታችን ያስመለከተን ነገር ቢኖር
ከወዲሁ ነጥብ የጣልንበት ያ ጨዋታ
ሊጎዳን ስለሚችል ለቀጣይ ጨዋታዎቻችን
በቂ ጥንቃቄ እና ትኩረት በማድረግ ወደ
አሸናፊነት እንድንመጣ ትምህርት ሰጥቶን
ያለፈ ነውና ያን በአግባቡ ልንጠቀምበት
ይገባል፡፡
ሀትሪክ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ ላለፉት ሁለት
ዓመታት ከዋንጫ ርቋል፤ ዘንድሮስ ያ ዕጣ
ፈንታ ይገጥመዋል?
አብዱልከሪም፡- በፍጹም፤ የሊጉን
የመክፈቻ ጨዋታ ምንም እንኳን ነጥብ
በመጣል ብንጀምርም የቀጣይ ጨዋታዎቻችን
ላይ እንደዛ ያሉት ውጤቶች በክለባችን
ውስጥ አይደገሙም፤ ከቀጣይ ግጥሚያ
አንስቶ ግን አሁን ላይ ስለዋንጫ ባለቤትነት
ብዙ ለማውራት ባንችልም ወደ አሸናፊነት
ክብራችን እንደምንመለስና አስፈሪውንና
ሻምፒዮናውን ቡድን እንደምናስመለክታችሁ
ግን በእኛ እርግጠኛ ሁኑ፡፡
ሀትሪክ፡- በአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ ጨዋታ
ላይ በኢትዮጵያ ቡና ብሎም ደግሞ በቅዱስ
ጊዮርጊስ ውስጥ በጥሩ ብቃት ላይ ይገኝ
የነበረውን አብዱልከሪምን እንደበፊቱ አሁን
ላይ ተመልክተነዋል.. ወይንስ ከዛ በተቃራኒው
መንገድ?
አብዱልከሪም፡- የኢትዮጵያ ቡና ተጨዋች
ሆኜም ሆነ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጨዋች
ሳለው እኔ ያለኝን የሜዳ ላይ አቅም ማንም
ያውቀዋል፤ በሲቲ ካፑ የጨዋታ ጅማሬዬ
ራሴን በምጠብቀው መልኩ አላገኘሁትም፤
የሚቀረኝ ነገርም አለ፤ ሲቲ ካፕ ራስህን
የምታዘጋጅበትና ለውድድርም ራስህን ብቁ
ተጨዋች ለማድረግ የምትፈተንበት ጨዋታ
ነውና የውድድሩ ተሳትፎዬ ለእኔ ብቻ
ሳይሆን ለአጠቃላይ ቡድናችንም መልካም
ስለሆነ ዘንድሮ የቀድሞ ጥሩና ውጤታማ
አቋሜን እንደማሳይ እና ቡድኔንም ለውጤት
እንደማበቃ እርግጠኛ ነኝ፡፡
ሀትሪክ፡- የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች
አሁንም ከእናንተ ጎን ሆነው እያበረቷቷችሁ
ይገኛል፤ ስለእነሱ ምን ትላለህ?
አብዱልከሪም፡- የቅዱስ ጊዮርጊስ
ደጋፊዎች ለእኛ እየሰጡን ያለው ድጋፍ
ሁሌም ቢሆን ለውጤት ያበቃናል፤ አሁን
እንኳን የሲቲ ካፑ ተሳትፎአችን ላይ
አምረውና ደምቀው በመምጣት ያበረታቱን
ሁኔታ ለእኛ ትልቅ የሞራል ስንቅ ሆኖልን
እና ውጤትም እንድናመታ ስላደረገን እነሱን
በደስታ ልናስጨፍራቸው ችለናልና ይሄ
ድጋፋቸው ለወደፊቱም ተጠናክሮ ሊቀጥል
ይገባል፡፡
ሀትሪክ፡- በመጨረሻ….?
አብዱልከሪም፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ
የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ላለፉት ሁለት
ዓመታት ባልተለመደ መልኩ ማጣቱ እኛንም
ሆነ ደጋፊዎቻችንን እንዳስቆጨ እናውቃለን፤
ኢንሽ ዓላህ ዘንድሮ የውድድሩ ሻምፒዮና
ስለምንሆን ይሄ ታሪክ ፈጽሞ አይደገምም፡፡
አስተያየት ይስጡ