የአዳማ ከተማ የመጀመሪያው ዙር ጉዞ ሲዳሰስ

ያጋጠመው የፋይናንስ ችግር ጥላ አጥልቶበት የመጀመሪያ ዙሩን ያጠናቀቀው አዳማ ከተማ የመጀመሪያው ዙር ጉዞን እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ለሚከታተሉ የእግርኳስ አፍቃሪያን አዳማ ከተማን በመጀመሪያው አጋማሽ በምን ታስታውሱታላቹ ብለን ብንጠይቃቸው የአብዛኞቹ ምላሽ በፋይናንስ ቀውስ የሚል እንደሚሆን አያጠራጥርም።

ባሳለፍነው አመት ጥሩ ብቃት ያሳዩ ተጨዋቾቻቸውን በዘንድሮው የውድድር አመትም ማቆየት የቻሉት እና የቀድሞ አሰልጣኛቸውን አሸናፊ ከበደን የሾሙት አዳማዎች በመጀመሪያው የውድድር ክፍል ጠንካራ ተፎካካሪ ይሆናሉ ተብሎ ተጠብቆ ነበር። በመጀመሪያው ሳምንት ጨዋታም አምና ከመቕለ 70 እንደርታ ጋር በዋንጫው ፉክክር እስከ መጨረሻው ሳምንት ድረስ አንገት ለአንገት ተናንቆ ሁለተኛ ሆኖ መጨረሽ የቻለውን ፋሲል ከተማን አዳማ ላይ አስተናግደው ያለምንም ግብ አቻ የወጡ ሲሆን በሳምንቱ ደግሞ አንጋፋ እና ታዳጊ ተጨዋቾችን በመቀላቀል በሊጉ የመጀመሪያ ተሳትፎውን እያደረገ የሚገኘውን ወልቂጤ ከተማን አዳማ ላይ በድንቁ ግብ አዳኛቸው ዳዋ ሁቴሳ ብቸኛ ግብ በማሸነፍ የመጀመሪያ ድላቸውን በማስመዝገብ በሁለት ጨዋታዎች 4 ነጥብ በመሰብሰብ ችለዋል ። ይህም ውጤታቸው የአሰልጣኝ አሸናፊ ስብስብ በሊጉ እንደተጠበቀው ጠንካራ ተፎካካሪ እንደሚሆን በሊጉ ተከታታዮች ዘንድ ተስፋ ተጣለበት።

ቡድኑ በመጀመሪያ ሁለት ጨዋታዎች ያሳካውን ጥሩ የሚባል ውጤት የማስጠበቅ ሀላፊነትን ተሸክሞ 3ተኛው ሳምንት መርሀ ግብር አዲስ አበባ ላይ የውበቱ አባተን ሰበታ ከተማን የገጠመ ሲሆን ሆኖም ግን በዚህ ጨዋታ በለስ ሳይቀናው ሸገር ላይ 2 ነጥብ ጥሎ በ5 ነጥብ 5ተኛ ደረጃ ላይ የሚያስቀምጠውን ውጤት አስመዝግቦ ወደ አዳማ ተጉዟል።

በመጀመሪያዎቹ ሶስት ጨዋታዎች 1 ግብ ብቻ ማስቆጠር የቻሉት አዳማ ከተማዎች ግብ የማግባት እና የግብ እድል የመፍጠር ብቃታቸው ጥያቄ ውስጥ የገባ ቢሆንም በአንፃሩ ግን የተከላካይ ክፍላቸውም በሶስቱም ጨዋታ ምንም ግብ አለማስተናገዱ ይበል የሚያስብል ጅማሮ ነበር።

በአራተኛው ሳምንት መርሀግብር ግን ከላይ የጠቀስነውን ደካማ እና ጠንካራ ጎን የሚጣረስ ውጤት ነበር ያስመዘገቡት። በሜዳቸው የወላይታ ዲቻን ያስተናገዱ ሲሆን በጨዋታውም ሁለት ግብ አስቆጥረው ጠንካራው ተከላካይ ክፍላቸው ደግሞ ሁለት ግብ ተቆጥሮበት በሳምንት ልዩነት ውስጥ ሌላ የአቻ ውጤት አስመዘገቡ። ከዚህ የአቻ ሀንጎቨር የተላቀቁ የማይመስሉት አዳማዎች በ አምስተኛ ሳማንት መርሀ ግብርም ወደ ትግራይ ተጉዘው ዱላ ሙላቱ በጨዋታው መጠናቀቂያ ደቂቃዎች ላይ ባስቆጠራት አንድ ግብ ከስሁል ሽረ ጋር አንድ አቻ በመውጣት በተጨማሪም በስድስተኛው ሳማንት መርሀግብር ከ ካችአምና ቻምፕዮኖቹ ጅማ አባጂፋር ጋር አዳማ ላይ ያለ ምንም ግብ በመለያየት በ 4 ጨዋታ ማግኘት ከነበረባቸው 12 ነጥብ 4ቱን ብቻ ማሳካት ችለዋል። ይህም ንፃሬ ቡድኑ ገና የውጤት መንገዱን እንዳልጀመረ የሚያሳይ ነበር።

በአቻ ውጤት ሲንገዳገድ የቆየው አዳም ከተማ በስተመጨረሻም በሰባተኛው ሳምንት መቐለ ላይ በ መቐለ 70 እንደርታ የ 2-0 ሽንፈትን መቅመስ ቻለ። ይህም ጨዋታ ቡድኑ በውውድር አመቱ ያጋጠመው የመጀመሪያ ሽንፈት ሆኖ ተመዝግቧል። በቀጣዩ ሳምንትም ከሀዋሳ ከተማ ጋር 1-1 በመውጣት ነጥብ መጣሉን ቀጠለ

በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ይለዋ ይሄ ነው በውጤት ማጣት ሲንገዳገድ የነበረው አዳማ ከተማ በ ፋይናንስ ቀውስም መመታቱ ከድሬዳዋው ጨዋታ በፊት ተሰማ። የቡድኑ ቁልፍ ተጨዋቾችን ጨምሮ ሌሎችም ተጨዋቾች ለበርካታ ወራት ደሞዝ እንዳልተከፈላቸው እና አድማም እንደሚመቱ መናገራቸው ታወቀ። ዛቻቸው ከልብ ነበር እና ተጨዋቾቹ ልምምድ አንሰራም በማለት ልምምድ ሳያደርጉ የጨዋታው ቀን ደረሰ እንደምንም በተፈጠረ መግባባትም ቡድኑ ጥቂት ሰዓታት ሲቀሩት ወደ ድሬ አመራ። የጨዋታ ህጉ የዘሩትን ማጨድ ሆነና ያለልምምድ የሄዱት አዳማዎች በድሬዳዋ ከተማ 2-1 ተረቱ። 9 ነጥብ ብቻ ይዘው በሊጉ ግርጌ 14ተኛ ደረጃ ላይ ተቀመጡ።

ከደረሰባቸው የፋይናንስ እና የጤት ቀውስ ለማገገም ከፊታቸው የቀረበውን ሲሳይ በአግባቡ መብላት የነበረበት አዳማ ከተማ ሌላ በውጤት ማጣት ውስጥ የሚገኘውም ሀድያ ሆሳዕናን አበበ በቂላ ሜዳ ላይ 2-1 በማሸነፍ ለጊዜው እንኳን በረጅሙ መተንፈስ ቻለ።

በሊጉ የመጀምሪያ አጋማሽ መጨረሻ ሳምንታት ላይ አዳማ በባህርዳር የ 2-1 ሽንፈትን የቀመሰ ሲሆን በካሳዬ አራጌው ኢትዮጵያ ቡና ላይ ደግሞ ያልተጠበቀ የ 3-0 ድል መቀዳጀት ቻለ በተጨማሪም በ 15ተኛው ሳምንት ከሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በአዲስ አበባ ስታድዮም በመገናኘት ያለግብ ምንም ለምንም በመለያየት የመጀመሪያውን አጋማሽ 19 ነጥቦችን በመሰብሰብ 9ኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ ማጠናቀቅ ችሏል።

የቡድኑ ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች

ወረቀት ላይ የቡድኑን ስብስብ ለተመለከተ ሰው አዳማ ከተማ ጠናካር ቡድን መሆኑን መገመት የሚያዳግት ነገር አይደለም። ሆኖም ግ ን እግርኳስ የብዙ ተለዋዋጭ ነገሮች ድምር ውጤት ነው እና በግርድፉ ይሄ ቡድን ጠንካራ ነው ደካማ ነው ማለት አይቻልም።

የእግርኳስ ዋና አላማው ግብ አስቆጥሮ ማሸነፍ ነው እና የአዳማን የፊት መስመር እንዳስሰው። አዳማ በ15 ጨዋታዎች 16 ግቦችን ያስቆጠረ ሲሆን በአማካኝ በጨዋታ 1.07 ግቦችን ያስቆጥራል ማለት ነው ይህም ቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴው ላይ በደፈናው ደካም እንደሆነ ለመገመት ይረዳናል ( በዚች አጭር ስሌት ብቻ ቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴው ደካማ ነው ብለን እርግጠኛ መሆን አንችልም። ይሄን ለማወቅ ሰፋ ያለ የ መረጃ ትንተና ወይም Data analysis መስራት ይኖርብናል)።

በአንፃሩ የተከላካይ ክፍሉ በ15 ጨዋታዎች 13 ግቦች የተቆጠሩበት ሲሆን 8 ጨዋታዎች ደግሞ ግብ ሳይቆጠርበት መውጣት ችሏል። ይህም መረጃ የቡድኑ የመከላከም ሂደት ጠንካራ እንደሆነ ያሳየናል።

ለቡድኑ ግብ የማግኘት ችግር እንደዋናነት የሚጠቀሰው ችግር በአጥቂው ዳዋ ሁቴሳ ላይ ትክሻ ላይ መንጠልጠል እና ከ ዳዋ ውጪ በተደጋጋሚ ግብ የሚያስቆጥሩ ተጫዋቾችን ማጣት ይመስላል። ይሄ በእንዲህ እንዳለ ደግሞ የመስመር ተጨዋቾቹ በረከት እና ቡላቻ በፍጥነት ኳስን ይዞ በተጋጣሚ ግብ አቅራቢያ ከመገኘት በዘለለ ፍሬያማ የሆነ የግብ እድል እንዲፈጥሩ ወይም ግብ እንዲያስቆጥሩ የመጨረሻ ኳሳቸው ላይ የሚወስኑትን ውሳኔ እጅጉኑ ማስተካከል ይጠበቅባችዋል።

ከሁለተኛው ዙር ምን እንጠብቅ

በዝውውር መስኮቱ ቁልፍ ተጫዋቾቻቸውን ያጣሉ ተብሎ ሲጠበቅ የነበረ ቢሆንም ከሰሞኑ በተሰሙ ወሬዎች ዳዋ ሁቴሳ ከንአን ማርክነህ እና ምኞት በቡድኑ እንደሚቆዩ ለማወቅ ተችሏል። የፋይናንስ ጉዳዩን መፍታቱ ቡንዱ በተረጋጋ መንፈስ ሊጉ ላይ አተኩሮ ውጤት እንዲያስመዘግብ ሊረዳው ይችላል።

በሊጉ ማን እንደሚወርድ መገመት አዳጋች በሆነበት ሰአት አዳማዎች ግብ የማስቆጠር ችግራቸውን እና ግብ የሚፈጥሩበትን ሂደት በአፋጣኝ በማረም ወደ ውጤቱ የማይመለሱ ከሆነ በወራጅ ቀጠናው የሞት ሽረት ትግል ሊያጋጥማቸው እንድውሚችል መገመት ቀላል ነው።

ሆኖም ግን ቡድኑ በመጀመሪያው አጋማሽ መጨረሻ ሳምንታት ላይ ያስመዘገባቸውን ውጤቶች እና ከሜዳ ውጪ ያለውን ችግር መፈታቱን ተመርኩዞ ቡድኑ ጥሩ የሚባል እንቅስቃስል ማሳየቱ እና በተለይ በሜዳው የቀድሞው አስፍሪነቱ ሊመለስ የሚችልባቸው ሁኔታዎች አሉ።