የአደይ አበባ ብሔራዊ ስታዲየም የሁለተኛው ምዕራፍ ጅማሮ !

 

የአደይ አበባ ስታዲየም የሁለተኛው ዙር ምዕራፍ የግንባታ ሂደት የማስጀመር ስራ በዛሬው ዕለት የተለያዩ እንግዶች በተገኙበት በይፋ መጀመራቸውን ለማወቅ ተችሏል ። ይህ ግዙፍ ስታዲየም በቻይናው ስቴት ኮንስትራክሽን ኢንጅነሪንግ አማካሪነት እየተገነባ ይገኛል ።

በዛሬው የማስጀመሪያ ስነ – ስርዓት ላይ ትልልቅ ባለስልጣኖች የተገኙ ሲሆን ስታዲየሙ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ ለኢትዮጵያ የእግር ኳስ ተመልካች ትልቅ ብስራት እንደሚሆን ይጠበቃል ። በዝግጅቱ ላይ የተገኙት የኢፌድሪ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ኤልያስ ሽኩር በሰጡት አስተያየት በአሁን ሰዓት በሁሉም የሀገራችን ክልልሎች ከ 12 በላይ ስታዲየሞች በመገንባት ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል ። በዝግጅቱ ላይ የተገኙት የቻይና ስቴት ኮንስትራክሽን ኢንጂነሪንግ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሚስተር ሚንግ ቾ በሰጡት አስተያየት ኩባንያው ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በመስራት ከፍተኛ ልምድ ያለው መሆኑን ጠቅሰው የዓለም አቀፍ ስጋት የሆነው የኮሮና ቫይረስ በመቋቋም ስታዲየሙን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ እንደሚሰሩ ተናግረዋል ።

በስፍራው የተገኙት የኢትዮጵያ እግር ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ በሰጡት አስተያየት በአሁን ሰዓት የካፍ እና የፊፋን መስፈርት ያሟላ ኢንተርናሽናል ጨዋታዎችን ማስተናገድ የሚያስችል ስታዲየም እንደ ሌለ ጠቁመው የአደይ አበባ ስታዲየም የዓለም ዋንጫ ፍፃሜን ማስተናገድ የሚያስችል ስታዲየም እየተገነባ መሆኑን ትልቅ ደስታ እንደፈጠረላቸው የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን አስነብቧል ።

አጠቃላይ የሁለተኛው ምዕራፍ ግንባታ 900 ቀናት እንደሚፈጅ ሲጠበቅ ግንባታውን ለማጠናቀቅ ከ 5.5 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስወጣ ይጠበቃል ።

የአደይ አበባ ስታዲየም ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ ከ 62,000 በላይ ተመልካቾችን የመያዝ አቅም እንዳለው ይጠበቃል ። ይህ ውብ ስታዲየም ተገንብቶ ሲጠናቀቅ የጋዜጣዊ መግለጫ ክፍሎች (ሳውን ፕሩፍ የሆነ) ፣ 8 ቪ አይ ፒ ክፍሎች ፣ 2 ቪ ቪ አይ ፒ ክፍሎች ፣ ከ 1,000 በላይ መፀዳጃ ቤቶች (የወንድ እና የሴት ) ፣ 10 የሚዲያ ክፍሎች ፣ ከ15 በላይ ሬስቶራንቶች ( በአንድ ጊዜ ከ 2,500 ሰው በላይ ማስተናገድ የሚችሉ) እና 7 ሊፍቶች እንደሚኖሩት ይጠበቃል ።

Hatricksport website Editor

Twitter

kidus Yoftahe

Hatricksport website Editor