የአበበ ቢቂላ የጤና ቡድን ለኮሮና ቫይረስ መከላከል ድጋፍ ሰጠ

 

መላው የስፖርት ቤተሰብ ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ርብርብ እያደረገ ነው፡፡ የአገርን መልካም ስም ከማስጠበቅ አንፃር ትልቅ ስራ እየሰራ ያለው የአበበ ቢቂላ የጤና ቡድን ቫይረሱ አሳሳቢ መሆኑን በመረዳት የሚጠበቅበትን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቶ ከአባላቱ የሰበሰበውን ወደ መቶ ሺህ ብር የሚጠጋ የምግብና የንጽህና ቁሳቁስ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ዛሬ አስረክቧል፡፡

የአበበ ቢቂላ የጤና ስፖርት ቡድን ማኅበር በ2006 ዓ.ም የተመሠረተ ሲሆን በምሥረታው ዓመት በሙኒክ ጀርመን፣ በ2007 በፍራንክፈርት ጀርመን፣ በ2008 በዘ ሄግ ሆላንድ፣ በ2009 በሮም ጣልያን፣ በ2010 በስቱትጋርት ጀርመን እንዲሁም ባለፈው ዓመት በዙሪክ ስዊዘርላንድ በተካሄዱ የአውሮፓ የኢትዮጵያዊያን የስፖርት ፌስቲቫሎች ላይ ተሳትፎ ጥሩ ውጤት አስመዝግቧል፡፡ በተጨማሪም እ.አ.አ. በ2007 በዴንቨር እና እንዲሁም በ2008 በቨርጂንያ አሜሪካ በተካሄዱት የኢትዮጵያዊያን የስፖርት ፌስቲቫሎች ላይ ተሳትፎ ተመልሷል፡፡

ከዚያ በተጨማሪም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ስፔን ማድሪድ እንዲሁም ወደ ቶኪዮ ጃፓን የመጀመሪያ በረራውን ሲጀምር የቡድኑ ሙሉ አባላት በቀዳሚዎቹ በረራዎች በመጓዝ የቀናት ጉብኝት አድርገዋል፡፡ የጤና ቡድኑ በተጓዘባቸው ቦታዎች ሁሉ የከተማውን ብሎም የሃገሪቱን ስም ለማስጠራት ከፍተኛ ጥረቶችን አድርጓል፡፡ በተለይ ለ15 ዓመታት በአውሮፓ ከተሞች ሲካሄድ የቆየውን በአውሮፓ የኢትዮጵያዊያን የባህልና የስፖርት ፌስቲቫል በቀጣይ ዓመታት በአዲስ አበባ እንዲከናወን ጥያቄ አቅርቦ ለማሳካት እንቅስቃሴ እያደረገ ላይ ይገኛል፡፡ ይህንንም በማሳካት በሺዎች የሚቆጠሩ በአውሮፓ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ወደ መዲናችን መጥተው የሚወዳደሩበት ግዙፍ ዝግጅት ያከናውናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport