“የተጨዋቾች ክፍያ መብራት ውሃና መንገድ ከሌላቸው ህዝቦች ተቀንሶ የሚመጣ ነው” አቶ መንግሥቱ ሳሳሞ /የሲዳማ ቡና እግር ኳስ ክለብ ፕሬዚዳንትና የሊግ ካምፓኒው የቦርድ አባል/

በፊት ለፊት ንግግራቸው ይታወቃሉ፡፡ ለረጅም ዓመታት ክለባቸውን በፕሬዚዳንትነት መርተዋል አሁንም እየመሩ ነው፡፡ በሊግ ካምፓኒው ምስረታ ወሳኝ ሚና የተወጡና የሊግ ካምፓኒው የቦርድ አባል ሆነው እየሰሩም ይገኛሉ፡፡ አቶ መንግሥቱ ሳሳሞ ይባላሉ፡፡ ከባልደረባችን ዮሴፍ ከፈለኝ ጋር በነበራቸው ቆይት ሙጂብ ቃሲምን ለማስፈረም ስለመሞከራቸው፣ የህገ ወጥ የተጨዋቾች ደመወዝ የሚከፍሉ ክለቦች ላይ መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ ስለመጠየቃቸው፣ በ2013 ውድድር ስለመኖሩ ስጋት ላይ ስለመሆቸው፣ ገቢ በሌለበት ወጪ ብቻ ማውጣት የሚችሉ ክለቦች የሉም ስለማለታቸው፣ ውድድሩ ባይካሄድ የተጨዋቾች ደመወዝ ጉዳይስ ምን ሊሆን ይችላል በሚሉና መሰል ጉዳዮች የሰጧቸው ምላሾች ይህን ይመስላል፡፡

ሀትሪክ፡- የፋሲል ከነማው ሙጂብ ቃሲምን ለማዛወር ተጨዋቹን ማነጋገራችሁን ሰማሁ… እውነት ነው?

መንግሥቱ፡- ሙጂብኮ ከገጠር አሳድጌ ያመጣሁት ተጨዋች ነው፤ወደ ቤቱ ለመመለስ ብንፈልግም የማንችለውን ጥያቄ ነው ያቀረበው… የደመወዝ ክፍያ በተመለከተ አቋማችን አንድ ነው የወጣውን ሕግ እናከብራለን ከ50 ሺ ብር በላይ ክፍያ አንፈፅምም፤ እርሱ የጠየቀን ግን ልናስበው የማንችለውን ነው ጥቅማ ጥቅሞቹን ለማስጠበቅ እንሞክራለን እንጂ ከሕጉ አንወጣም፡፡ እንደኛ ደሃ ክለብኮ የለም /ሳቅ/ የሚጠይቀው ጥቅማ ጥቅም ከኛ በላይ ነው ተወልዶ ያደገው እኛ ጋር ነው ቤተሰቡ ከኛ ጋር ናቸው ለኛ የመጫወት ፍላጎት ቢኖረውም ያቀረበው ግን የማንችለው በመሆኑ አልተስማማንም በዝውውር ዙሪያ የትኛው ክለብ ምን እያደረገ እንዳለ ስለማይገባን ይሄ ነው ማለት አልቻልንም፡፡

ሀትሪክ፡ ከህግ ውጪ የሚከፍሉ ክለቦች አሉ ማለት ይቻላል?

መንግሥቱ፡- ተጨዋቾቹማ ይህን ያህል ተሰጠን ይላሉ ሰጪው ማን ነው? በየትኛው ሕግና ደንብ ነው የሚሰጠው የሚለው ምላሽ አጥተንለታል ተቸግረናል ሕገ ወጥ አከፋፈል የሚፈፅሙ ክለቦችማ አሉ፡፡ አሁን ባሉን በራሳችን በወጣቶች የምንቀጥል ይሆናል፡፡

ሀትሪክ፡ ዜጋዎቹን በዶላር የማስፈረም ሂደቱ ምን ይመስላል… ሲዳማ ቡናስ ምን እያደረገ ነው?

መንግሥቱ፡- ዜጋዎቹማ በሀገር ውስጥ የክፍያ ስርአት ላይ እንገባለን ችግር የለም ካሉ እናስፈርማለን፡፡ ከሕጉ ዘለን ከሕጉ ውጪ የሆነ ደሞዝ አንከፍልም ጥቅሙን ማስጠበቅ ግን እንችላለን ዜጎቹም ዶላር ይጠይቃሉ ብዬ አላስብም ሲጀመርም በውጪ ዜጎች ችሎታ እምነቱም የለኝም፡፡ አሁን እየተጨነቅን ያለነው ተጨዋቹ እገሌ እንዲህ ሰጠን እያሉ የኛው የራሳችን ልጆች ከእጃችን እየወጡ ይገኛሉ… ስጋታችን ይሄ እንዴት ይቆማል የሚለው ነው… የራሣችን ቢ እና ዋናው ቡድን አሉን በእነርሱ ራሳችንን ማጠናከር ብቻ ነው የምንፈልገው…. የዛሬ 6 አመት ያሳደግነው አዲስ ግደይም ሄዶብናል ሄጃለሁ ሳይለን ሄዷል በዚህ ቅር ብሎናል፡፡ አቅም ያለው ለምን ወሰደ ብለን መጮህ መከራከር አንችልም፡፡

ሀትሪክ፡ በሊግ ካምፓኒው ህገ ወጥ ውሎችን ለማስቀረት ምን እየተሰራ ነው?

መንግሥቱ፡-ተነጋግረናል ትልቁ ችግር ተጨዋቾችን ከሕጉ ውጪ በሆነ ዋጋ አስፈርመው የሚመጡ ክለቦች ውል ላይኮ ከ50 ሺ ብር በታች አድርገው ያመጣሉ ይሄን እንዴት ማወቅ ይቻላል? ይሄ ጉዳይ የፌዴሬሽኑም ሆነ የሊግ ካምፓኒው ጩኸት ነው፡፡ ምክንያቱም ይሄ ነገር ያለው ከጀርባ ነው፡፡ በሕጋዊ መንገድ የመጣ ውል በሌለበት እንዴት ማስቆም ይቻላል? ተጨዋቾቹም ውል ሊዋዋሉ ሲመጡ ከጀርባ ሌላው ውል ፈርመው ነው እንዴት መስተካከል እንዳለበት አላውቅም፡፡

ሀትሪክ፡ መንግሥትስ ጣልቃ ገብቶ ቢመረምር ሕገወጡ ክለብና ተጨዋች አይደርስባቸውም?

መንግሥቱ፡- በደንብ ይደርስባቸዋል እንጂ… መንግሥትም ማግኘት ያለበት ግብርም እየቀረ በመሆኑ ለራሱ ሲል ርምጃ መውሰድ አለበት የግል ቼክ የሚሰጡ ክለቦች አሉ… ይህን መመርመር ግን ለመንግሥትም አስቸጋሪ ነው፡፡

ሀትሪክ፡ ፖሊስስ የስልክ ጠለፋ አድርጎ ምርመራ የማካሄድ እድል የለም?

መንግሥቱ፡-ከፍተኛ ኃላፊነቱ የፖሊስ አይደለም፡፡ መንግሥት ማግኘት ያለበት ግብር እያጣ ነው፡፡ ገቢዎች ናቸው በደንብ መመርመር ያለባቸው… ተጨዋች ገንዘብ አያግኝ የሚል ማንም የለም፡፡ በሳምንት ስንት ሺ ፓውንድ ሲከፍላቸው እያየን የኛ ተጨዋቾች አይከፈላቸው እያልኩ አይደለም ትልቁ ችግር ግን የኳሳችን እድገት የአውሮፓ ታላላቅ ክለቦችና ያደጉ የአፍሪካ ሊጎች ጋር አልደረሰም የህዝባችን የኑሮ ደረጃ አይመጥንም የተጨዋቾች ክፍያ መብራት ውሃና መንገድ ከሌላቸው ህዝቦች ተቀንሶ የሚመጣ ነው ይሄ ገንዘብ ሲመጣ ኳሱ ገቢ እያስገኘ አይደለም ይሄ ሁሉ ከግምት ሊገባ ይገባል፡፡

ሀትሪክ፡ ውድድሩ በ2013 ይቀጥላል ተብሎ ይገመታል?

መንግሥቱ፡-ባለፈው ሳምንት በነበረው ስብስባ የ2013 ውድድርች ይኖራል ወይስ አይኖርም በሚለው ጉዳይ ላይ ተነጋግረናል መወሰን አልቻልንም፡፡ እናም አልተረጋገጠም የዝውውር መስኮቱም ገና አልተከፈተም፡፡

ሀትሪክ፡ መስከረም 2/2013 የዝውውር መስኮት ሲከፈት የሚመጣ ውል ነው ሕጋዊ የሚሆነው ክለቦች አሁን ገና ሳይረጋገጥ እያስፈረሙ ነውኮ… ?

መንግሥቱ፡-መስከረም 2/2013 ላይም የዝውውር መስኮት ይከፈታል ገና አልተባለም፡፡ አልተወሰነምም፡፡ ለኮሮና ቫይረስ ምርመራ ለአንድ ተጨዋች 22 ዶላር ነው የሚከፈለው… ተጨዋች በ72 ሰዓት ተመርምሮ መረጃው መቅረብ አለበት… የሚሉ ሕጎች ወጥተዋል፡፡ መንግስት ለሁሉም ከፍሎ የሚያስመረምርበት አቅም ላይ አይገኝም፡፡ ህዝቡ ወደ 120 ሚሊዮን ይጠጋል 1 ሚሊዮን ኪት ነው ያለው ይሄ ደግሞ የሚያገለግለው አቅም ለሌላቸው በጣም ለተጎዱና መዳን ለሚገባቸው እንጂ ለእግር ኳስ ተጨዋቾች አይደለም ክለቦች ይህን ወጪ መቻል አለባችሁ ነው የተባለው ይሄ ችግር ባለበት ገና ፕሮቶኮሉ ባልፀደቀበት የዝውውር መስኮት ይከፈታል ማለት አይታሰብም ገና አልተወሰነም እያልኩ ነው፡፡

ሀትሪክ፡ 2013 የፕሪሚየር ሊግ የመካሄዱ ነገር ርግጠኛ መሆን ይቻላል?

መንግሥቱ፡- ይህን ርግጠኛ መሆን አይቻልም ግን ከባድ ይመስለኛል፡፡ ለኮሮና ምርመራ 780 ብር አካባቢ ለ1 ተጨዋቾች ይከፈላል ክለቦች ይህን ይችላሉ ወይ? 2 አውቶብስ የግድ ያስፈልጋል፤ አንድ ነገር ቢከሰት የማቆያ ካምፕ ያስፈልጋል፣ ተጨዋቹ የሚጠቀምባቸው ነገሮች የራሱ ብቻ ነው. ድንገት አንዱ ላይ ኮቪድ 19 ቢገኝ ሁሉም የቡድኑ አባላት ኳራቲን ይገባሉ ይሄ ራሱ ውድድሩን ሊያስቆም ይችላል የተመረጡ 6 ከተሞች መቐለ፣ ባህርዳር፣ አዲስ አበባ፣ ሀዋሳ፣ አዳማና ድሬደዋ ስታዲየሞች ብቻ ይካሄዳሉ፡፡ በአመቱ 30 ጨዋታዎች በየከተማዎቹ አምስት አምስት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ ጤና ጥበቃና መሰል ጉዳይ በሚመለከታቸው አካላት ክትትል ይደረጋል ጨዋታው በዝግ እንደመካሄዱ ወጪ እንጂ ገቢ የለውም.. ሁኔታው ከበድ ያለ በመሆኑ የመካሄዱ ነገር አጠራጥሮኛል፡፡

ሀትሪክ፡ በ2011 የሲዳማ ቡና የሜዳ ገቢ ስንት ነበር?

መንግሥቱ፡- ገንዘቡን በደንብ አላስታውስም ያኔ እኛ ጋር አመቺ ስታዲየሞች አልነበሩም… አብዛኛው በሜዳ ትክክለኛ ገቢ የሚያገኙ ክለቦች ያቀረቡት ጥያቄ ግን ነበር በአመት ከሜዳ ገቢ ከ15-18 ሚሊዮን ብር እናገኝ ነበር አሁን ይሄ በሌለበት እንዴት መግፋት እንችላለን? እንዲያውም ኢትዮጵያ ቡና በማስታወቂያ የምናገኘው በደጋፊዎቻችን ድጋፍ ነበር አሁን ይሄ ከሌለ ከካምፓኒው የምናገኘው ገቢ ስለማይኖር በምን መልኩ ነው የምንወዳደረው ሲሉ ጠይቋል፡፡ ወረርሽኙ እየሰፋ ከሄደ ውድድር ማካሄድ ይቻላል ወይ ሕጉስ ያስኬደናል? የሊግ ኮሚቴው ግን ተጠናክሮ የቲቪ የማስታወቂያ ገቢ ከሌለና ክለቦቹ ካልተደጎሙ ቀጣዩ ጊዜ ከባድ ይሆናል፡፡

ሀትሪክ፡- ሊግ ካምፓኒው ከገቢ አንፃር ራሱን ለማጠናከር ምን እየሰራ ነው?

መንግሥቱ፡ በኛ በኩል ገቢ ገቢ ለማምጣ ትና የተሻለ ነገር ለመስራት ለየተቋሙ ደብዳቤ ልከናል፡፡ ከኮሮና በፊት በርካታ ተቋማት ዝግጁ ነበሩ፡፡ ኮሮና በመምጣቱ ግን ሁሉ ነገር ባለበት ቆሟል፡፡ አሁን ስንጠይቀቸው ይቀበሉናል አይቀበሉንም የሚለው አጓጊ ነው የቦርድ ሰብሳቢው መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞና የሊግ ካምፓኒው ጽ/ቤት ይሄን ጉዳይ እንዲሰሩ ኃላፊነቱ ተሰጥቷቸዋል፡፡ የካምፓኒዎቹ አርማ በስድስቱ ስታዲየሞች እንዲለጠፍ በቲቪ እንደመተላለፉ የቲቪና የማስታወቂያ ገቢ ለማግኘት እየተሰራ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- ገቢ በሌለበት ወጪው መጨመሩ ከባድ አይሆንም?

መንግሥቱ፡- ክለቦች ውድድር ሲያካሄዱ የሚያርፉት ካምፕ ሳይሆን ሆቴል ውስጥ ነው፡፡ አንድ ቡድን ለሚቆይበት ሆቴል የሚከፍለው ክፍያ ከፍተኛ ነው ካምፕ ሲሆን ወጪ የለውም የምግቡ ወጪ የሆቴሉን ያህል አይከፋም፡፡ የነዚህ ድምር ውጤት ለክለቦቹ ሌላ ወጪ ይሆናል፡፡ ውድድሩ እንዴት ይሁን የሚለው እንግዲህ ቀጣይ ወር መጀመሪያ ላይ ስብሰባ ተካሄዶ ውሳኔያችን ለጤና ጥበቃ ሚ/ር ቀርቦ መንግሥት አይቶት ውድድሩን አካሄዱ ካለ ብቻ የሚካሄድ ይሆናል፡፡

ሀትሪክ፡- በዚህ አይነት እስከ ሕዳር ላይጀመር ነው ማለት ነው?

መንግሥቱ፡- አይጀመርጀም እንጂ… እንዴት ይጀመራል ብለህ ታስባለህ? አንደኛ ጥናቱ መስከረም መጀመሪያ ላይ ቢቀርብ እስከ መስከረም 30 ድረስ መልስ ከተሰጠ አመት ሙሉ ያለውድድር የከረሙ ተጨዋቾችን ቤት የተኛውን ተጨዋችን አሰርቶ ለግጥሚያ ዝግጁ ለማድረግ 2 ወር ተኩል ይወስዳል ብዬ አስባለው ውድድሩ እስከ ህዳር ይጀመራል ብዬ አላምንም፡፡

ሀትሪክ፡- የኮቪድ 19 ወረርሽኝ መጨመሩ ለክለቦችም ሆነ ለብሔራዊ ቡድኑ ከባድ ጊዜ አይመስሎትም?

መንግሥቱ፡- የኛ ብሔራዊ ቡድን ጨዋታ ካለው ከባዱ ሌላ ችግር ደግሞ ይሄ ነው… ለነገሩ ብዙ ችግሮችማ አሉ… በዚህ አይነት የበሽታው ቁጥር እየጨመረ መጥቷል እነዚህ ሁሉ ወጪ የሚጨምሩ በጀት ያላቸው ክለቦች አሉ ወይ? ያውም ደመወዝ መክል ያቃታቸው ክለቦች ባሉበት ሊግ ሁኔታው ከባድ ይመስለኛል፡፡ በዚህ አይነት ሁኔታ ህዝብ በማያይበት 10 ሳንቲም ገቢ ሳይኖር መካሄዱ የሚከብድ ይመስለኛል፡፡ መንግሥትኮ ት/ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎችን ዘግቶ ባለበት ለኳሱ ይህን ያህል ወጪ የሚያወጣ አካል ይኖራል ብዬ አላስብም፡፡

ሀትሪክ፡ ባይካሄድ የክለቦቹ ሰራተኞችና የቡድኖቹ አባላት ደመወዝ ጉዳይ እንዴት ይሆናል?

መንግሥቱ፡- ከዚህ በኋላ በተጨናነቀ መርሃ ግብር ሊቀጥልኮ ይችላል ሌሎች ሀገራትና አለማት ውድድሮችን ከጀመሩ የኛ የተለየ ነገር ሊኖር አይችልም፡፡ የሀገር ስምና ክብር የሚታይበት መድረክ እንደመሆኑ ውድድሩ ሙሉ በሙሉ አይኖርም ማለት አልችልም፡፡ ሰፊ ትኩረት ይሰጣቸዋል ብዬም አላስብም፡፡ ምናልባት ግን ውድድር ባይኖር ውል ያላቸው ተጨዋቾችን በውላቸው መሠረት ላይከፈላቸው ይችላል፡፡ ምክንያቱም ደመወዝ ማለት የ30 ቀን የአገልግሎት ክፍያ ማለት ነውና፡፡ ተጨዋቾችም ደግሞ ውል እያላቸው አይከፈላችሁም ማለት አይቻልም፡፡ የሚመስለኝ ክለቦችና ተጨዋቾች ቁጭ ብለው በአሰሪና ሰራተኛ ደንብ ሁለቱም ሳይጎዱ ተደራድረው የሚስማሙበትን ክፍያ ሊፈፅሙ ይችላሉ ብዬ አስባለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- አቶ መንግሥቱ አመሰግናለሁ፡፡

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport