የብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ብቃታቸውን ጠብቀው እንዲቆዩ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን አሰልጣኝ አብርሐም መብራህቱ ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች በዚህ አስቸጋሪ ወቅት በአካልም ሆነ በሥነ-ልቦና እንዳይጎዱና ጥንካሬአቸውን ጠብቀው መቆየት እንዲችሉ ለማድረግ ከቡድኑ አባላት ጋር በጋራ እየሠሩ መሆኑን አስታወቁ፡፡ ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የቀትር የስፖርት ዜና ጋር ቆይታ ያደረጉት የብሄራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ አብራሃም መብራህቱ እንደገለጹት ተጫዋቾቹ በአካልም ሆነ በሥነልቦና ጥንካሬአቸውን ይዘው እንዲቆዩ ለማድረግ በኢንተርኔት አማካኝነት በየዕለቱ እየተገናኙ እንደሚሠሩ ተናግረዋል፤ ለዚህም የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አምበል ሽመልስ በቀለ እንዲሁም ምክትል አምበሉ አስቻለው ታመነ ፕሮግራሙን በማስተባበርና በመቆጣጠር ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አሰልጣኙ እንዳሉት እያንዳንዱ ተጫዋች የዕረፍት ጊዜውን ስፖርታዊ እንቅስቃሴ በማድረግና መጻህፍትን በማንበብ እንዲያሳልፉ በማድረግ ላይ እንደሆነና አንድ ተጫዋች በሁለት ሳምንታት ውስጥ ቢያንስ አንድ መጽሃፍ በማንበብ ሪፖርት እንዲያደረግ በማድረግ ተጫዋቾቹ በሥነ-ልቦናና በዕውቀት ራሳቸውን እንዲያሳድጉ እየረዱ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
እንደአሰልጣኙ ገለጻ ፕሮግራሙ የኮሮና በሽታ ከምድራችን ተወግዶ ተጫዋቾቹ ወደሜዳ ሲመለሱ ከነብቃታቸው እንዲመለሱ ይረዳቸዋል፡፡

Editor at Hatricksport

FacebookTwitter

Teshome Fantahun

Editor at Hatricksport