የቅዱስ ጊዮርጊስ የመጀመሪያው ዙር ጉዞ ሲዳሰስ

 

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታዎች መጠናቀቃቸውን ተከትሎ የተለያዩ ክለቦችን የመጀመሪያው ዙር ጉዞ ምን ይመስል ነበር የሚለውን እየተመለከትን እንገኛለን። ዛሬ ደግሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ ጉዞ ምን ይመስል ነበር የሚለውን ተመልክተን እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

 

በአሰልጣኝ ሰርዳን ዚቪጂኖቭ እየተመሩ በ28 ነጥብ ፕሪምየር ሊጉን እየመሩ የመጀመሪያውን ዙር ያጠናቀቁት ፈረሰኞቹ፣ በአስከፊ ጉዟቸው ምክንያት በርካታ ተቃውሞችን ሲያሰተናግዱ የነበሩት አሰልጣኙ በሚገርም ጉዞ በተከታታይ ጨዋታዎች ነጥብ በመሰብሰብ በሊጉ የመጀመሪያው ዙር በአንደኝነት እንዲያጠናቅቁ ረድቷቸዋል። በተለይ ከጨዋታ ጨዋታ የአቤል ያለው፣ ጋዲሳ መብራቴ እና ጌታነህ ከበደ ጥምረት ለዚህ ውጤት 80 ከመቶ የሚወስዱ ተጫዋቾች ናቸው። ፈረሰኞቹ በመጀመሪያው ዙር በአብዛኛው ወደ ጋዲሳ መብራቴ ያዘነበለ ቀጥተኛ እና ረጃጅም ኳሶች ሲከተሉት የነበረው የአጨዋወት መንገድ ነበር።

 

ፈረሰኞቹ ካደረጓቸው 15 ጨዋታዎች 7ቱን በድል ሲወጡ በ1 ጨዋታ ብቻ ሽንፈት አስተናግደው በቀሪዎቹ 7 ጨዋታዎች በአቻ ውጤት አጠናቀዋል። በሜዳቸው ካደረጓቸው 7 ጨዋታዎች 5 ሲያሸንፉ በቀሪው 2 ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል ይህም ቅዱስ ጊዮርጊሶች ምን ያክል በሜዳቸው ጠንካራ እንደሆኑ ያስረዳል። በሜዳቸው ባደረጓቸው ጨዋታዎች በተቃራኒ ቡድን ላይ 13 ግቦችን ሲያስቆጥሩ በአንፃሩ 5 ግቦችን አስተናግደዋል። ፈረሰኞቹ ጠንካራ የመከላከል ስፍራ እና ግቦችን የሚያስቆጥሩ የፊት መስመር አጥቂዎች እንዳሉት የቁጥራዊ መረጃዎች ያሳያሉ። በሜዳቸው ጨዋታ ሲያደርጉ 1.8 በየጨዋታው ግብ የማስቆጠር አቅም ሲኖራቸው 0.7  ብቻ ግብ ይቆጠርባቸዋል።

 

 

ፈረሰኞቹ በመጀመሪያው ዙር ከሜዳቸው ውጭ 8 ጨዋታዎችን አድርገው 2ቱን አሸንፈው በ5ቱ አቻ ሲለያዩ በመጀመሪያው ዙር በጅማ አባ ጅፉር ብቻ ሽንፈትን አስተናግደዋል። ከሌሎች ቡድኖች አንፃር ፈረሰኞቹ ከሜዳቸው ውጭ ዝቅተኛ ሽንፈት ካስተናገዱ ቡድን አንዱ ነው። ከሜዳቸው ውጭ ባደረጓቸው ጨዋታዎች 9 ግብ በተጋጣሚያቸው ላይ ሲያስቆጥሩ 6 ግቦች ተቆጥሮባቸዋል። ይህ ማለት ደግሞ 1.2 ግብ ከሜዳቸው ውጭ በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ሲያስቆጥሩ 0.75 ይቆጠርባቸዋል። እንደ ቁጥራዊ መረጃ ከሆነ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሜዳው ውጭ ግቦችን የማስቆጠር ችግር ባይታይበትም በሜዳው ከሚያደርጋቸው ጨዋታዎች አንፃር ግን ደካማ የመከላከል አቅም አለው። በጥቅላላው ፈረሰኞቹ 22 ግቦችን ሲያቆጥሩ 11 ግቦች በተቃራኒው አስተናግደዋል። በየጨዋታው በአማካይ 1.4 ግብ የማግባት አቅም ሲኖራቸው በአንፃሩ 0.73 ይቆጠርባቸዋል። በመጀመሪያው ዙር መከላከል እና ግብ ማስቆጠሩ ላይ ፈረሰኞቹ ጠንካራ እንደነበሩ ከቁጥራዊ መረጃዎች መረዳት ይቻላል። ቅዱስ ጊዮርጊሶች በመጀመሪያው ዙር ካደርጓቸው ጨዋታዎች ከፍተኛ ግብ ያስቆጠሩት ሲዳማ ቡና ላይ ሲሆን ጨዋታውን 6-2 በሆነ ውጤት ነበር ያሸነፉት። በአንፃሩ ፈረሰኞቹ በሶስት ጨዋታዎች ሁለት ሁለት ግብ የተቆጠረባቸው ከፍተኛ ግብ የተቆጠሩባቸው ጨዋታዎች ናቸው። በ5 ጨዋታዎች ግብ ሳያስቆጥሩ ሲወጡ በ8 ጨዋታ ደግሞ መረባቸውን ሳያስደፍሩ ወጥተዋል። በ4 ጨዋታዎች ተከታታይ ድል ማስመዝገብ የቻሉ ሲሆን ይህም የመጀመሪያውን ዙር ሊጉን በመምራት እንዲያጠናቅቁ ከፍተኛ አበርክቶ አድርጎላቸዋል። አቤል ያለው 7 ጎሎችን አስቆጥሮ የቡድኑን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት በመምራት ላይ ይገኛል። በመጀመሪያው ዙር ኤድዊን ፍሪምፖንግ እና ሄኖክ አዱኛ ያለምንም እረፍት ለቡድናቸው አገልግሎት የሰጡ ብቸኛ ተጫዋቾች ናቸው።

 

ባለፈው አመት 26 ነጥቦችን በመሰብሰብ ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ የመጀመሪያውን ዙር ያጠናቀቁት የሊጉ መሪዎች ፈረሰኞቹ በዘንድሮው አመት ግን በሁለት ነጥብ ከፍ በማድረግ 28 ነጥብ ይዘው ሊጉን እየመሩ አጠናቀዋል።

 

ፈረሰኞቹ አሁን ላይ የሰበሰቡት ነጥብ አምና ዋንጫ ካነሳው መቐለ 70 እንደርታ ጋር የመጀመሪያው ዙር ሲያጠናቅቅ ከነበረው ነጥብ ጋር ሲነፃፀር በ7 ዝቅ ይላል። መዓም አናብስቶች 35 ነጥብ በመያዝ ነበር የመጀመሪያውን ዙር መጨረስ የቻሉት።

 

የፈረሰኞቹ ጠንካራ እና ደካማ ጎን

ምንም እንኳን በቅርብ ጨዋታዎች ላይ ቢያሻሽሉም ከሜዳ ውጭ ነጥብ ይዞ የመመለስ ችግር የሚሰተዋልባቸው ነበሩ። አስፈሪው እና ግብ አስቆጣሪው የፊት መስመራቸው እና ጠጣር የመከላከል አደረጃጃት በጠንካራ ጎኑ የሚነሳ ነው።

 

በሁለተኛ ዙር የሚጠበቅባቸው

ፈረሰኞቹ በዚህ አመት ለሻምፕዮን እንደሚጫወት ቡድን የነጥቡ መቀራረብ በጉዟቸው ላይ ችግር ሊፈጥርባቸው ስለሚችል ያላቸውን የሜዳ ጥንካሬ በማስቀጠል ከሜዳ ውጭ በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ትኩረት በማድረግ ነጥቦችን መሰብሰብ ይኖርባቸዋል።

Hatricksport website Editor

Facebook

ሚሊዮን ኃይሌ

Hatricksport website Editor