“የማህበሩ መመስረት ለተጨዋቾችም ለሀገር እግር ኳስም ትልቅ ጠቀሜታ አለው” አዳነ ግርማ

የቀድሞ የሐዋሳ የተጨዋቾች ማህበርን ለመመስረት እንቅስቃሴ ተጀምሯል

“የማህበሩ መመስረት ለተጨዋቾችም ለሀገር እግር ኳስም ትልቅ ጠቀሜታ አለው”
አዳነ ግርማ

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ማህበራት እየተበረከቱ መጥተዋል፤ቀደም ሲል የተጫዋቾች በመቀጠል የቀድሞ ተጨዋቾችና ደጋፊዎች የመረዳጃ ማህበር አሁን በቅርቡ ደግሞ የፕሮፌሽናል የእግር ኳስ ተጨዋች ማህበር ተመስርቶ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡
ከወደ ደቡብ ክልል የተሰማው ዜና እንደሚጠቁመው ደግሞ የቀድሞ የሀዋሳ ከነማ የተጨዋቾች ማህበርን ለመመስረት እንቅስቃሴ መጀመሩ ተሰምቷል፡፡ ሀዋሳ ከነማ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ወደ ክልል በመውሰድ አዲስ ታሪክ ሲያፅፉ የቡድኑ ባለውለተኞች የነበሩት ሚካኤል ወልደሩፋኤልና አንዱአለም ነጋ (ቢጣ) ሃሳብ አመንጪነት የቀድሞ የሀዋሳ ተጨዋቾች ማህበርን ለመመስረት እንቅስቃሴ መጀ መሩና ማህበሩ በህጋዊ መንገድ በክልልም ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ በይፋ ለመንቀሳቀስ የሚያስችለውን ፍቃድ ለማውጣት በመጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ ነው የተሰማው፡፡
ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ የማይ ዘነጋቸው ተጨዋቾችን ያበረከተው የሀዋሳ ከነማን ማልያ የለበሱ ተጨዋቾችን በማህበሩ ጥላ ሥር እንደሚያሰባስብ የተገለፀው አዲሱ ማህበር ማህበር ለመሆን የሚያስችለውን ሕጋዊ ሰውነት በቅርቡ ካገኘ በኋላ በይፋ በመላ ሀገሪቱ የመንቀሳቀስ ትልቅ ራዕይ ሰንቆ መነሳቱ ተነግሯል፡፡
ማህበሩን በማደራጀትና ሕጋዊ እውቅና አግኝቶ እንዲንቀሳቀስ የማደራጀት ስራውን እንዲሰሩ ስድስት አባላት የተመረጡ ሲሆን ይሄንንም ኃላፊነት ሰብስቤ ደፋር፣ ሚካኤል ወልደ ሩፋኤል እንዲሁም የክለቡ ፀሐፊ አንዱ አለም አረጋን አካቷል፡፡
የማህበሩ ፕሬዚዳንት አዳነ ግርማ ነው በሚል መነገሩን ተከትሎ ወደ ተንቀሳቃሽ ስልኩ ደውለን ያናገርነው የቀድሞ ኮከብ አዳነ ግርማ የአዲሱ ማህበር ፕሬዚዳንት ሆንክ እንዴ?ብለነው “ኧረ ገና ማህበሩ በይፋ አልተመሰረተም፤ገና የማደራጀት ስራ እየተሠራ ነው፤ እኔም ፕሬዚዳንት አይደለሁም” በማለት በሳቅ የታጀበ ምላሽ የሰጠው አዳነ ግርማ የማህበሩ መመስረት አስፈላጊነትን በተለይ ለሀትሪክ ሲገልፅ “ትክክል ነው የቀድሞ የሀዋሳ ከነማ ተጨዋቾች ማህበርን ለማቋቋም እንቅስቃሴ ብቻ ሣይሆን የማደራጀት ስራም እየተሠራ ነው፤ በዚህ ዙሪያ አነጋግረውኝ ጥሩ ጎኑ ስለታየኝና ስላመንኩበትም አስተዋፅኦ ለማድረግ ዝግጁ መሆኔን ገልጫለሁ፤ሀዋሳ ትልቅ ታሪክ ያለው ታላላቅ ተጨዋቹን በማፍራት በኢትዮጵያ እግር ኳስ የገዘፈ ስም ያለው ክለብ ነውና በዚህ ክለብ ጥላ ሥር የምንሰባሰብበት የምንረዳዳበት፣ የምንማማርበት እድልን የሚፈጥር በመሆኑ በማህበሩ መመስረት ደስተኛ ነኝ” ካለ በኋላ “አንድ አመትም ይሁን 10 አመት አሊያም አምስት ወር የክለቡን ማልያ የለበሰ የማህበሩ አባል ከመሆን የሚከለክለው የለም፤የክለቡን ባህልና ታሪክ የሚያውቁ ተጨዋቾች የሚሰባሰቡበት በመሆኑ የማህበሩ መመስረት ለሀዋሳ ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገር እግር ኳስም ትልቅ ጠቀሜታ አለው፤አሁን ያለው የማደራጀት ሥራ ተሰርቶ ሲጠናቀቅና ህጋዊ ሰውነት ስናገኝ ጋዜጣዊ መግለጫ እንሰጣለን” ብሏል የቀድሞው ኮከብ አዳነ ግርማ በተለይ ለሀትሪክ፡፡

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor.
The First Color Sport Newspaper in the country.

Yishak belay

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor. The First Color Sport Newspaper in the country.